እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በምትገኘው አል-ሆሽ ከተማ ላይ ያደረሰችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ የታየው ጭስ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በምትገኘው አል-ሆሽ ከተማ ላይ ያደረሰችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ የታየው ጭስ  (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር የሊባኖስን ህዝብ ‘መከራ እጋራለሁ’ አለች

ቅድስት መንበር በሊባኖስ እየተካሄደ ያለውን ቀውስ አስመልክቶ በተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሀገሪቱን የመደገፍ ሃላፊነት እንዳለበት አሳስባለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቅድስት መንበር የውጪ ሀገራት ግንኙነት ቢሮ ምክትል ዋና ጸሃፊ የሆኑት ሞንሲኞር ሚሮስሎው ስታኒስሎው ዋካውስኪ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሊባኖስን “ነጻነት፣ አንድነት እና የግዛት ሉአላዊነትን” እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

ሞንሲኞር አባ ዋካውስኪ ይሄንን አስተያየት የሰጡት ሀሙስ ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ሊባኖስን ለመደገፍ ታስቦ በፈረንሳይ መንግስት በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ ከ70 የተለያዩ መንግስታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በተገናኙበት ወቅት ነው።

ሊባኖስን መደገፍ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ግዴታው” ነው
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሊባኖስ በአስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፥ ከዚህ ችግር ሳትላቀቅ ከጥቅምት ወር ጀምሮ የእስራኤል ኃይሎች የሀገሪቱን ደቡባዊ ክፍሎች መውረራቸው ይታወቃል።

ሞንሲኞር ዋካውስኪ ንግግራቸውን የጀመሩት ቅድስት መንበር “የሊባኖስን ሕዝብ ስቃይ እንደምትጋራ” በመግለጽ ሲሆን፥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ በተለይም በሁሉም አቅጣጫ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ግፊት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት አልባ ሃገር
ሞንሲኞር ንግግራቸውን በመቀጠል ሊባኖስ ‘የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ህዝቦች ተስማምተው በጋራ የሚኖሩባት ሃገር’ መሆኗን እና ለሌላው ሃገራት ተምሳሌት እንደሆነች ጠቅሰው፥ በአብዛኛዎቹ ግምቶች መሠረት ከሊባኖስ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው የሚሆነው ክርስቲያን እንደሆነ ገልጸዋል።

በፖለቲካዊ አለመስማማት የተነሳ ሀገሪቱ ለሁለት ዓመታት ያህል ፕሬዝዳንት ያልነበራት ሲሆን፥ በዚህ ረገድ ሞንሲኞር ዋካውስኪ ቅድስት መንበር ሊባኖስ ፕረዚዳንት አልባ ሆና መቀጠሏ እንደሚያሳስባት በመግለጽ፥ ቦታው ሁል ጊዜ በማሮናዊት ካቶሊክ ሚና ስር እንደሆነ አስታውሰዋል።

ሞንሲኞር የፕሬዝዳንት ሹመት የሊባኖስን ነፃነት፣ አንድነት እና የግዛት ሉአላዊነት ለመጠበቅ አማራጭ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ጭምር በመሆኑ በአስቸኳይ ሊተገበር የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል።

የሰብአዊነት ህግን ማክበር
ደቡባዊ የሀገሪቱን ክፍል እየናጠ ያለውን ግጭት ያነሱት ሞንሲኞር ዋካውስኪ፥ ቅድስት መንበር የሆስፒታሎችን፣ ክሊኒኮችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እና የአምልኮ ቦታዎችን መጠበቅን ጨምሮ ለዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግጋት ‘ከምንም በላይ ክብር’ መስጠት እንደሚገባ ጥሪ ታደርጋለች ብለዋል።

በደቡባዊ ሊባኖስ ለሚገኙት እና በተደጋጋሚ በእስራኤል ሃይሎች ጥቃት የሚደርስባቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ቅድስት መንበር ያላትን ድጋፍ የገለጹት ሞንሲኞር ዋካውስኪ፥ በ 2013 ዓ.ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቫቲካን ለሊባኖስ ባደረጉት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ “ከእንግዲህ ሊባኖስን እና መካከለኛው ምስራቅን ለውጭ ሃይላት መጠቀሚያ ማድረግ አያስፈልግም! ሊባኖሳውያን በራሳቸው ምድር ያለአንዳች ጣልቃ ገብነት ለመጪው ጊዜ የተሻለ ህይወት ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ እድል ሊሰጣቸው ይገባል” ብለው የተናገሩትን ቃል በመጥቀስ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።
 

25 October 2024, 13:45