በጉባኤው ላይ ወጣቶች “ከቤተ ክርስቲያን ጋር በኅብረት መጓዝ እንፈልጋለን!” ማለታቸው ተገለጸ

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ማክሰኞ ጥቅምት 12/2017 ዓ. ም. በሰጠው 16ኛ ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ቅዳሜ ጥቅምት 16/2017 ዓ. ም. ሊፀድቅ በተዘጋጀው የሲኖዶሱ የመጨረሻ ረቂቅ ሠነድ ላይ ጉባኤው መወያየቱን አስታውቋል። ጉባኤው ከተወያየባቸው ዋና ዋና ሃሳቦች መካከል ጥቂቶቹ “የወጣቶች እና የሴቶች ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ” የሚሉ እንደ ነበር እና በዚህ ውይይት መካከል ወጣቶች፥ “ከቤተ ክርስቲያን ጋር በኅብረት መጓዝን እንፈልጋለን!” ማለታቸውን የመረጃ ኮሚሽኑ በመግለጫ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማክሰኞ ጥቅምት 12/2017 ዓ. ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተሳተፉት፥ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በካሜሩን የቤማንዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሪው ንኬ ፉአንያ፣ በጀርመን የኤሰን ጳጳስ አቡነ ፍራንዝ-ጆሴፍ ኦቨርቤክ እና ከማሌዢያ የመጡት አባ ክላሬንስ ዳቬዳሳን ናቸው።

የጉባኤው ተሳታፊዎች የሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በዚህ ወቅት ረቂቅ ሠነዱ ላይ ተወያይተው የማሻሻያ ሃሳብ ከማቅረብ በተጨማሪ በዓለም ላይ እየተከሰተ ያለውን ነገር በትኩረት በመከታተል ለጦርነት ያላቸውን ተቃውሞ በጠንካራ እና ግልጽ አቋም ገልጸዋል። የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች ተግባርን በማስመልከት ማክሰኞ ጥቅምት 12/2017 ዓ. ም. መግለጫ የሰጡት የጠቅላላ ጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ እና የኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ ናቸው።

ሂደቱ በረቂቅ ሠነዱ ውስጥ የሚጨመሩ፣ የሚቀነሱ ወይም የሚተኩ የማሻሻያ ሃሳቦች ካሉ በተጨባጭ የሚቀርብበት እነዚህ ማሻሻያዎች በግለሰቦች ወይም በሲኖዶሱ ተሳታፊ ቡድኖች በኩል ሊቀርቡ እንደሚችሉ እና በኋላም እያንዳንዳቸው በሲኖዶሱ አባላት ድምጽ እንደሚሰጥባቸው ዶ/ር ሩፊኒ አስረድተዋል። ዓላማው የቡድኑን ግንዛቤ በሚገልጹ የጋራ ማሻሻያዎች ላይ መድረስ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ሩፊኒ በመቀጠልም በዚህ መሠረት እያንዳንዱ የጉባኤው አባል የግል ሃሳቡን ለሲኖዶሱ ዋና ጽሕፈት ቤት መላክ እንደሚችል ገልጸዋል።

ረቂቅ ሠነዱ በዩክሬን እና በቻይና ቋንቋዎች ጭምር ይተረጎማል
የመጨረሻው ረቂቅ ሠነድ የጉባኤው ኦፊሴላዊ ቋንቋ በሆነው በጣሊያንኛ የሚጻፍ ቢሆንም በተቻለ መጠን ወደ ብዙ ቋንቋዎች መተርጎሙን አስታውቀዋል። ይህ እንዲሆን የተደረገበትም የተለያዩ አባላትን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሆነ አስረድተው፥ ሠነዱ ከተተረጎመባቸው ቋንቋዎች መካከል ዩክሬንኛ እና ቻይንኛ እንደሚገኙበት ዶ/ር ሩፊኒ ገልጸዋል።

ወጣቶች፥ “ከቤተ ክርስቲያን ጋር በኅብረት መጓዝ እንፈልጋለን!”
የጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ በመግለጫቸው፥ ሲኖዶሱን በተመለከተ እስካሁን በ 40 ርዕሠ ጉዳዮች ለውይይት መቅረባቸውን ገልጸው፥ ከእነዚህ ርዕሦ መካከል ወጣቶችን የሚመለከት እንደሚገኝበት እና ከአባላት የቀረበ አንድ አቤቱታ፥ “የሲኖዶስ አባቶች እና እናቶች፥ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ለመጓዝ የሚፈልጉ መሆናቸውን በመገንዘብ ከጉባኤው ማግስት ወጣቶችን ይበልጥ ማቅረብን አትዘንጉ” ማለቱን አስታውሰዋል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሚናዎች
የመረጃ ኮሚሽኑ ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ በመግለጫቸው፥ የሴቶች ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሠረታዊ ጠቀሜታእንዳለው አረጋግጠው፥ ከዚያም የምእመናን፣ የጳጳሳት ጉባኤ፣ የካህናት፣ የገዳማውያን እና ገዳማዊያት እንዲሁም አነስተኛ የክርስቲያን ማኅበራት ሚናን በተመለከተ ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

የመረጃ ኮሚሽኑ ጸሐፊ ዶ/ር ሺላ ፒሬስ በማጠቃለያቸው፥ ወደ ሲኖዶሱ የሚደርሱ አንዳንድ የዓለም ዜናዎችን መሠረት በማድረግ እንደተናገሩት፥ ቤተ ክርስቲያን ጦርነትን እንደምትቃወም፣ በጠንካራ እና ግልጽ አቋሙ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንዲቆሙ ጉባኤው መማጸኑን፥ “ያለዚያ ይህንን ሠነድ የሚያነብ ሰው በሕይወት አይኖርም” ማለቱን ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን የሚሆኑበ አዲስ መንገድ
ከተወያዮቹ መካከል የመጀመሪያውን ንግግር ያሰሙት በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ፥ ‘ጉባኤው የተጠራው የተወሰኑ ችግሮችን ለመፍታት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን የመሆን አዲስ መንገድ ለመፈልግ ነው” ብለው፥ “ሲኖዶሱ ራሱ ላስቀመጠው ዓላማ መሠረት ጥሏል እንጂ አላፈነገጠም” ብለዋል። በማከልም፥ “ከጉባኤው በኋላ እያንዳንዳችን ወደ ገዛ አገራችን ተመልሰን በዓለማቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚነሱ ችግሮችን ለማቃለል የሲኖዶሳዊነትን መንፈስ ተግባራዊ ማድረግ አለብን” ብለው በሲኖዶሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

“አሁን በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሲኖዶሳዊነት በግልጽ እየታየ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል አምቦንጎ፥ አፍሪካ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመሆን ወደዚህ አዲስ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመግባት እና ከቀድሞው በተለየ መንገድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን እንደሚሞክሩ ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።

አፍሪካ ለሲኖዶሳዊነት “ለም መሬት” ናት
በካሜሩን የቤማንዳ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሪው ንኬ ፉአንያ በበኩላቸው፥ ከቁምስና ምዕመናን እና የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች ጀምሮ አፍሪካውያን ለሲኖዶሱ ያበረከቱትን የሃሳብ አስተዋጽኦ በማስታወስ “ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተለያየ ሃሳብ ይዘን ለመጣን በሙሉ ሲኖዶሳዊነት ዋና ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ሲኖዶሳዊነት የመጪው ጊዜ ተስፋ እንደ ሆነ አምናለሁ” ብለዋል። በአፍሪካ አውድ ቤተ ክርስቲያናት በምዕመናን ቁጥር ተጠቃሽ ብትሆንም ሲኖዶሳዊነትን እንዴት መጠበቅ ይቻላል?” በማለት ጠይቀዋል።

በመቀጠልም ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚናን በማስታወስ፥ አፍሪካ ሲኖዶሳዊነትን በተግባር ለመግለጽ ምቹ ቦታ በመሆኗ በምዕመናን መንፈሳዊ ማኅበራት ውስጥ ችግሮችን ለመፍታት እና ሰላምን ለመፍጠር እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

እስያ በውይይት ላይ የምትገኝ የሕያው እምነት አኅጉር
በማሌዢያ መዲና ኩዋላ ላምፑር የሚገኝ የካቶሊካዊ የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አባ ክላሬንስ ሳንዳራጅ የቤተ ክርስቲያናቸውን ሕያው የሲኖዶሳዊነት ልምድ በማስመልከት ሲናገሩ፥ ሲኖዶሳዊነትን በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ እና ከቤተ ክርስቲያናቸው ውጭ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋርም በተጨባጭ እንደሚኖሩት አስረድተዋል።

በአገራቸው የካቶሊክ እምነት ሕያው ቢሆንም ይህ ማለት ዓለማዊነት እና ሌሎች ችግሮች የሉም ማለት እንዳልሆነ ገልጸው፥ በብዙ ቦታዎች እምነት የሚገለጽባቸው ሥፍራዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ቢያንስ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ባሉባቸው አካባቢዎች በውይይት ወደ መስማማት መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል። ውይይት አዲስ ሳይሆን በብዝሃ-ባህል ውስጥ በየቀኑ በተጨባጭ የሚኖሩት በመሆኑ ሲኖዶሳዊነት ለዚህ ሁሉ መሠረት በመሆን ከቤተሰብ ጀምሮ በየቦታው ፍሬ ማፍራቱን ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

 

 

23 October 2024, 17:41