“የዲቁና ጥሪ፣ መሠረታዊ የክርስትና እምነት አስተምህሮ እና ለአቅመ ደካማ ቤተ ክርስቲያናት የሚሰጥ ድጋፍ"

የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ መስከረም 28 እና 29/2017 ዓ. ም. ባደረገው ጠቅላላ ስብሰባ በቤተ ክርስቲያን የአስተዋይነት ሚና እና መሠረታዊ የክርስቲያና እምነት ትምህርት በሚሉት ርዕሦች ላይ ባደረገው ውይይት መሠረት በቀናቱ ንግግር ያደረጉት የስብሰባው ተሳታፊዎች በዕለታዊ የመገለጫ ጊዜ፥ የዲቁና አገልግሎት ጥሪ፣ የክርስቲያናዊ ትምህርት ተነሳሽነት እና አቅመ ደካማ የሆኑ ቤተ ክርስቲያናትን የማገዝ አስፈላጊነትን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ከተሳታፊዎች መካከል ከቀረቡ ሃሳቦች መካከል ከፍተኛ ትኩረት የተቸረለት ከአንዲት ወ/ሮ የቀረበ ምስክርነት ሲሆን፥ ይህም “ለአዳጊ ልጆች የሚስጥ መሠረታዊ ክርስትና እምነት ትምህርት በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል” የሚል እንደ ነበር እና ይህች ወ/ሮ አዳጊ ልጆችን በክርስትና እምነት ለማሳደግ የሚያግዙ መንገዶችን ጠይቀዋል።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ከኮሚሽኑ ጸሐፊ ሺላ ፒሬስ ጋር በመግለጫ ወቅት የአምስተኛ እና የስድስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሥራን በማስመልከት ሪፖርት አቅርበዋል።

እጅግ አስፈላጊ የምእመናን ሚና
ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች በነጻ የውይይት ጊዜ ባነሷቸው ነጥቦች፥ በቤተ ክርስቲያን የአስተዋይነት ጭብጥ እና መመዘኛዎቹ፣ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን የኃላፊነት ደረጃዎች እና የተቀቡ አገልጋዮች ሚናን ባተኮሩ ርዕሦች ላይ ተወያይተዋል።

የኮሚሽኑ ጸሐፊ ሺላ ፒሬስ በመግለጫቸው፥ ማክሰኞ መስከረም 28/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ 35 ንግግሮች መቅረባቸውን እና ረቡዕ ጠዋት 21 ተጨማሪ ንግግሮች መቅረባቸውን ተናግረው፥ በጠቅላላ ጉባኤው መካከልም ጎልተው ከወጡት መሪ ሃሳቦች መካከል የምእመናን ሚና፣ ከጳጳሳት እና ከካኅናት ጋር ያላቸው ትብብር እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ያላቸው ተሳትፎ የሚሉ እንደ ነበሩ ጸሐፊዋ ገልጸዋል።

ጠቅላላ ጉባኤው በካኅናት እና በምእመናን መካከል ያለውን ትብብር በማበረታታት አስፈላጊነት አጽንዖት መስጠቱን ፒሬስ ተናግረዋል። እንዲሁም ወንድ እና ሴት ምእመናን በአመራር ሚናዎች ላይ የበለጠ መሳተፍ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት የሰጡ ሲሆን፥ “የምዕመናን ትብብር ለቤተ ክርስቲያን ድጋፍ በመሆኑ በአመራር ሚና መሳተፋቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጉባኤው እንዳሰመረበት ገልጸዋል።

አንድ አስተያየት ሰጭ በተጨማሪም፥ “ለክኅነት እና ለጵጵስና እጩነት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማማከር አስፈላጊ ነው” ብለው፥ የመጨረሻ ላይ ውሳኔ የጳጳስ ቢሆንም በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ በውሳኔው ላይ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል” ብለዋል። እንዲሁም “ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚታጩት ሊኖራቸው የሚገባቸውን የሰብዓዊ እና መንፈሳዊ መገለጫ መስፈርቶች ምዕመኑ ማወቅ ይገባል” ብለዋል።

ሴቶች እና የማዳመጥ አገልግሎት
የኮሚሽኑ ጸሐፊ ሺላ ፒሬስ ጠቀሱት ሌላው አስተያየት፥ ብዙ ካኅናት በቁምስና መሪነት ለማገልግል ያላቸው ተነሳሽነ ዝቅተኛ በመሆኑ ምእመናን በሐዋርያዊ ሥራዎች ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና በጥልቀት ማጤን አስፈላጊ እንደሆነ፥ በሰላማዊ ትዳር የቤተሰብ ሕይወት የሚኖሩ በርካታ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ ልዩ ልዩ ተግባራትን ማከናወን እንደሚችሉ መነገሩን ጠቅሰዋል።

ሴቶችን በተመለከተ ፒሬስ እንዳሉት፥ ማንኛውንም ዓይነት ጾታዊ መድልዎን በማስወገድ፣ ለሴቶች አስተዋጽዖ እውቅናን በመስጠት እና እንዲሁም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በማሳትፍ፥ የሴቶች የማዳመጥ አገልግሎት የቁምስናውን ካኅን፣ ዲያቆንን ወይም የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪን በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ተጨማሪ እና ተስማሚ አገልግሎት ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው፥ “ሴቶች ማዳመጥ ማለት ምን እንደሆነ በልዩ መንገድ ይረዱታል ያለው ጉባኤው፥ ይህን አገልግሎታቸውን ሊያከናውኑ የሚችሉት ከንስሐ አገልግሎት ፈጽሞ በተለየ መንገድ እንደሆነ ገልጸው፥ በተከፋፈለ እና በጦርነት ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ ሴቶችን በዲፕሎማሲ ሥራ ይበልጥ ማሳተፍ ያስፈልጋል ብሏል።

ዲጂታል ሚዲያን ለወጣቶች አገልግሎት እንዲውል በአደራ መስጠት
የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመቀጠል፥ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች አዲሱን ትውልድ ከዲጂታል ሐዋርያዊ እንክብካቤ አገልግሎት ጋር ማገናኘት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ጠቁመዋል። በርካታ ወጣቶች በአዲሱ ዘመን ፋይዳ ቢስ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ከሚገኙ እኩዮቻቸው ጋር ለመወያየት የሚረዳቸው፥ ለወጣቶች የሚሆን የሐዋርያዊ እንክብካቤ አገልግሎት በአደራ እንዲሰጣቸው የሚል ሐሳብ ቀርቧል።

ለጉባኤው በተደረግ ንግግር እንደተገለጸው፥ “በዓለም ዙሪያ ብዙ ልጆችን ከሚያጋጥማቸው ጉዳዮች መካከል በቤተሰብ ምክንያት በልጅነት ዕድሜያቸው ወደ ጋብቻው ዓለም እንዲገቡ የሚገደዱ ልጆች መኖራቸው እንደ ምሳሌነት የቀረበ ሲሆን፥ ልጃገረዶች ለሴተኛ አዳሪነት፣ ሕጻናት ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል መጋለጣቸው እና በተጨማሪም ክርስቲያን ካልሆኑ ቤተሰቦች የሚወለዱ ልጆች ወደ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት የሚገቡት ሁኔታ የሚፈጥረውን ስጋት በማስመልከት አስተያየት መቅረቡን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

አንዲት ወ/ሮ ያቀረቡት “የወላጆች የጋራ ኃላፊነት”
ቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማው የተቋጩ ሠነዶችን ለማውጣት ሳይሆን ለድርጊት መርሃ ግብር መነሳሻ የሚሆኑ መንገዶችን ለመጠቆም ያለመ መሆኑን ተናጋሪዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ንግግር በማስታወስ መናገራቸውን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል። ክርስቲያናዊ እና ከቁምስና አካባቢዎች የሚወጡትን ድምጾች ማዳመጥ ብቻውን በቂ እንደማይሆነ ነገር ግን ሰዎች ወደ ፊት ለማቅረብ እና አስተማማኝ ቦታን ለመፍጠር ከውጪ የሚመጡ ድምጾችንም ማዳመጥ አስፈላጊ እንደሆነ በተደጋጋሚ መነገሩን አስታውሰዋል።

በመቀጠልም አንዲት ወ/ሮ፥ “ሕጻናት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እንዲሄዱ በማስተማር ማሳደግ አለብን” የሚለውን ምስክርነት በማስታወስ፥ “ጉባኤው ወላጆች፣ አያቶች እና የክርስትና እናቶች እና አባቶች ለሕጻናት ከልጅነታቸው ጀምሮ በሚሰጡት የማዳመጥ እና የማስተዋል ሚና ለሲኖዶሳዊነት የሚሰጠው አስተዋፅዖ ምን ይመስላል?” የሚለውን ጥያቄ ጉባኤው በማድመጥ ማድነቁን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመግለጫቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ቀጥለውም “የክኅነት ሕንጸትን ጨምሮ ለድሆች ሊሰጥ የሚገባውን ትኩረት በማስመልከት ይቀረበውን ጥሪ በማስታወስ፥ “በተለይም ድሆች ለእግዚአብሔር ልብ ቅርብ እንደሆኑ እና ሥልጣንም እንዳላቸው ብናውቅም፤ የሐዋርያዊ አገልግሎት እና ተልዕኮ መሣሪያዎች አድርገን ብንመለከታቸውም ነገር ግን በአገልግሎት ተሰማርተው አናያቸውም” መባሉን ጠቅሰዋል።

የጉባኤ ተሳታፊዎች፥ ካኅናት አንዳንድ ጊዜ ያለ ረዳት ብቻቸውን እንደሚለፉ እና ከሥራ ብዛት የተነሳ ድካማቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ አንፃር ካኅናት ከሲኖዶሳዊነት ዓላማ በተወሰነ ርቀት እንደሚገኙ እና ብዙዎቹ በከባድ የሥራ ጫና በርካታ አስተዳደራዊ ሸክሞች እንዳለባቸው አጽንዖት ተሰጥቶበታል።

ሲኖዶሱ በካኅናት ጥሪ ማደግ ላይ መሥራት እንደሚገባ፥ ለእያንዳንዱ ሰበካ የፋይናንስ ምክር ቤት እና ምናልባትም በርካታ ቁምስናዎችን ያካተተ ኅብረት እንዲኖር በማድረግ የሰበካ ካኅናትን በአገልግሎታቸው መርዳት ይገባል” የሚል ሃሳብ ከጉባኤው መቅረቡ ተመልክቷል።

የጥናት ቡድኑ የቤተ ክርስቲያን ሴቶችን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ በመጨረሻም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በጥናት ቡድን ቁጥር 5 የቀረቡ ሃሳቦችን መሠረት በማድረግ የተወሰኑ ሥነ-መለኮታዊ እና ሕገ ቀኖናዊ ጥያቄዎች በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ በብጹዕ ካርዲናል ቪክቶር ማኑኤል ፈርናንዴዝ የተሰጠ መግለጫን ያነበቡ ሲሆን፥ በተለይም የሴቶች ተሳትፎ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና አመራር የሚለውን በተመለከተ ጳጳሳዊ ምክር ቤቱ ከሲኖዶሱ ቀደም ብሎ ጥያቄውን በአደራ መቀበሉን ገልጸዋል።

የጳጳሳዊ ምክር ቤቱ መግለጫ እንዳለው፥ ሥራው አግባብ ያለውን ሠነድ ለማዘጋጀት በእራሱ ደንቦች ውስጥ የተቋቋመ የምክር ቤቱን የአሠራር ደንብ መከተል እንዳለበት አስታውቋል። ከጳጳሳዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በኩል የሚቀርበው ሠነድ በብጹዓን ጳጳሳት እና ካርዲናሎች ከተጠና በኋላ ይፋ እንደሚደረግ እና ርዕሡ በአሁኑ ወቅት በምክክር ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፥ ሁሉም የሲኖዶሱ አባላት እና የስነ መለኮት ምሁራን በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ አስተያየቶችን እና ድጋፋቸውን መላክ እንደሚችሉ እና በጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ የሚገኙ ሁለት የነገረ-መለኮት ምሁራን በርዕሱ ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦችን በጽሁፍ ወይም በቃል ለመቀበል መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

ቺሊ ውስጥ ቋሚ ዲያቆናትን ማዘጋጀት በተመለከተ
የላቲን አሜሪካ አገር በሆነች ቺሊ ውስጥ የፖርቶ ሞንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊስ ፈርናንዶ ራሞስ ፔሬዝ በአገራቸው ስላለው የቋሚ ዲያቆናት ሕንጸት ተጠይቀው ሲመልሱ፥ ይህ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሠነድን መሠረት በማድረግ በርካታ ቋሚ ዲያቆናት መሾማቸውን ገልጸው፥ ዛሬ በአገራቸው የሚገኙ ቋሚ ዲያቆናት ከሰበካ ካህናት እና ገዳማውያን በቁጥር እንደሚበልጡ ተናግረው፥ በየቁምስናዎች አስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ ካኅናት ጋር በመተባበር የሚያበረክቱት አገልግሎት ይበል የሚያሰኝ እና የሚመሰገን እንደሆነ አስረድተዋል።

በቤተ ክርስቲያን እና ከኅብረተሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጥራት
የቤተ ክርስቲያኒቱን አካሄድ የሚያሳድግ የሲኖዶሳዊ መንፈሳዊነት በማስመልከት የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊስ ፈርናንዶ ራሞስ ፔሬዝ በተጨማሪም፥ ሲኖዶሳዊነት የግለሰቦችን እና የኅብረተሰቡን ሐዋርያዊ ለወጥ የሚያነሳሳ መንፈሳዊነት መኖሩን ገልጸው፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ማኅበራዊ ግንኙነት መስተካከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በማከልም “ዛሬ በሰዎች መካከል ያሉ አንዳንድ ግንኙነቶች አንዱን ሊያሳድግ ሌላውን ሊበድል እንደሚችል ገልጸው፥ የሚቀጥለው መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ የሚከተል የቸርነት መንገድ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ራሞስ ፔሬዝ በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች በአንድ ነገር ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የሲኖዶሳዊነት መስፈርት በመጠቀም ከሥር ካሉት ምዕመናን ጋር በመመካከር መሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው፥ በዚህም መሠረት ሲኖዶሳዊ ማስተዋል የተቀቡ አገልጋዮችን ብቻ ሳይሆን ምእመናን ወንዶችን እና ሴቶችን የሚያካትት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።

መስከረም 28 እና 29/2017 ዓ. ም. በተደረገ ጠቅላላ ስብሰባን በማስመልከተ የተሰጠ መግለጫ

 

10 October 2024, 18:27