የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሲኖዶስ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሲኖዶስ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት 

የሲኖዶስ አመራሮች ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለተነሱ ፈታኝ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጡ

ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች የተውጣጡ ተማሪዎች ከሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አመራር አባላት ጋር ለመነጋገር በሮም መሰብሰባቸው ታውቋል። ከሰሜን አሜሪካ የመጡ 140 የሚሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዓርብ ጥቅምት 8/2017 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ከሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አመራሮች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሲኖዶስ መሪዎች ጋር መወያየት” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በተማሪዎች በኩል ተከታታይ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፥ የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፣ የሲኖዶሱ ጉባኤ ጠቅላይ መሪ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ የሳን በርናርዲኖ ሀገረ ስብከት ቻንስለር ሌቲሲያ ሳላዛር እና በደቡብ ቴክሳስ የብራውንስቪል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዳንኤል ፍሎሬስ ለጥያቄዎቹ በየተራ ምላሽ ሰጥተዋል።

በሲኖዶሳዊነት ላይ እየተካሄደ ያለው 2ኛ ጉባኤ ላይ የቀረቡ ርዕሦችን የሚያንጸባርቀው የክብ ጠረጴዛ ውይይቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአንድነት የመደማመጥ እና የመተሳሰብ ጉዞ ለማድረግ ያላቸውን ራዕይ የሚያሳይ እንደነበር ተመልክቷል።

የመደማመጥ ችግርን መፍታት
ከትሪኒዳድ እና ቶቤጎ የመጣች ተማሪ እስያ ቻን ያቀረበችው የመጀመርያው ጥያቄ፥ እምነቷን በተለያዩ ባሕሎች ውስጥ ለመግለጽ ችግር እንዳለባት በመግለጽ፥ ብዙ ድምፆች እንዲሰሙ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን የወደፊት ውይይቶችን እንዴት ማሻሻል እንደምትችል ጠይቃለች።

የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ለዚህ ጥያቄ ምላሻቸውን የሰጡ ሲሆን፥ ፈተናውን አምነው የቤተ ክርስቲያኒቱ የወቅቱ ሲኖዶሳዊ ሂደት በማዳመጥ አድማስ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ገልጸው፥ አሁንም ገና መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ቢኖሩም ይህ ሲኖዶስ ከቀደሙት ጉባኤዎች የበለጠ ብዙ ሰዎችን ያሳተፈ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ካርዲናሉ እንደተናገሩት፥ በቤተሰብ ላይ በተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ከ114 የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች መካከል ጉባኤውን የተሳተፉት 80 ብቻ እንደ ነበሩ አስታውሰው፥ “በዚህ ጉባኤ ግን ከ114ቱ መካከል 112ቱ ሪፖርታቸውን ማቅረባቸውን እና ይህም ማለት ብዙ ድምጾች ተሰሚነት ማግኘታቸውን ይገልጻል” ብለዋል።

በተጨማሪም በዚህ ወቅት ከ20,000 የሚበልጡ ሰዎች በዲጂታል መድረክ መሳተፋቸውን ጠቁመው፥ ተሳትፏቸው እጅግ ጥሩ እንደ ነበር እና ወደፊትም የተሻለ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

“መደማመጥ መሠረታዊ ነገር ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ አስተያየቶችን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስን መመሪያ ማዳመጥ “ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ሲኖዶሳዊት እንድትሆን በማድረግ እግዚአብሔርንም ሆነ እያንዳንዱን ሰው በማዳመጥ ላይ የተመሠረተ የግንኙነት ባሕል እንዲፈጠር ይረዳል” ብለዋል።

ወጣ ብለው ያሉ ወጣቶችን ማሳተፍ
ዕድገቱን በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረገ የቬንዙዌላ ተማሪ አሌክሳንድራ በበኩሏ፥ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ጋር የማይገናኙት ለምንድነው? ስለ ሲኖዶሳዊነት ግድ እንደሚላቸው እና ቤተ ክርስቲያን በዚህ ለተጎዱት ሰዎች እንዴት ቦታን ማዘጋጀት እንደምትችል በማለት ላቀረበችው ጥያቄ ብፁዕ ካርዲናል ሆለሪች ምላሽ ሲሰጡ፥ ተቃርኖ በበዛበት በዛሬው ዓለማችን ውስጥ የሰዎችን አስተያየት የማዳመጥን አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ ሕዝቦች መለያ የሆነውን የአመለካከት ግጭት ጠቁመው፥ “የአመለካከት መቃረን ከሲኖዶሳዊነት በጣም የራቀ የአስተሳሰብ መንገድ እንደሆነ እና እንደ ዲጂታሉ ዓለም ተመሳሳይ አስተያየት ያላቸውን ሰዎች ብቻ የሚከተሉበት እና በሃሳብ የማይስማሙ ከሆነ ተቃዋሚ ይሆናሉ” ብለዋል። “የተለየ አመለካከት ያለው ሰው ጠላት አይደለም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ “የአንድ ቤተሰብ አካል በመሆናችን የጋራ መፍትሄዎችን መፈለግ አለብን” ብለው፥ ተመሳሳይ ጥምቀት የምንካፈል በመሆናችን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እህቶች እና ወንድሞች መሆን ለእኛ አይከብደንም ብለዋል።

“ዓለም ከዚህ የሚማር ይመስለኛል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሆሌሪች፥ ሲኖዶስ ሰዎች ወደ አንድነት የሚመጡበትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑን በመገንዘብ እና ለሌሎች እምነቶች እና ሃይማኖቶች ክፍት በመሆን በጋራ ሰብአዊነታችን በመታገዝ በዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ላይ መወያየት መልካም እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሆለሪች እንደተናገሩት፥ ቤተ ክርስቲያን በምትከተለው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ በተለይም እንደ ሰላም፣ ፍትህ እና ሥነ-ምህዳር ለመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ክፍት የውይይት መድረክ መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል።

ሲኖዶሳዊ ለውጥ ለሚያመጣ ትውፊት ታማኝ መሆን
ከሳን ፍራንሲስኮ የመጣች ተማሪ ሶንድራ፣ የሲኖዶሳዊነት ሂደት ለባሕል እና ለእውነት ያላትን ታማኝነት እንዴት ሊጎዳ እንደሚችል ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቡነ ፍሎሬስ ሲኖዶሳዊነት የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል ምስክርነት ተልዕኮን እንደማይጎዳ በማስረዳት፥ የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ማዳመጥ ፈታኝ መሆኑን አምነዋል ነገር ግን ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ነባራዊ ሁኔታዎች መረዳት አስፈላጊ መሆኑን አረጋግጠዋል።

“ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት የተመሰቃቀለች ስትሆን እንዴት በታማኝነት ቀጥላችኋል?” ብለው የጠየቁት አቡነ ፍሎሬስ፥ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን አንድ እንዳደረጋት፣ እርስ በርሳችን የምንደማመጥ ከሆነ እምነት እንደሚያስማማ እና የሲኖዶሳዊነት ጉዞ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዎች ለመረዳት የበለጠ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ከውይይት ወደ ተግባር መሸጋገር
በወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ የተሰማራው የኒው ኦርሊንስ ተማሪ ጆሴፍ በበኩሉ፥ ሲኖዶሱ ውይይቶችን ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዴት ሊለውጠው እንደሚችል ለጠየቀው ጥያቄ እህት ሌቲሲያ ሳላዛር ሲመልሱ፥ የሲኖዶሱን ሂደት የለውጥ ባህሪ አጽንዖት በመስጠት፥ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመለማመድ በትእይንቱ ውስጥ ራስና ማስገባት እንደሚገባ የሎዮላው ቅዱስ ኢግናጢዮስ ያቀረበውን ግብዣ በማስታወስ ከሲኖዶስ ተሳታፊዎች ጋር በአንድ ጠረጴዛ ላይ መቀመጥ ኅብረትን እና ለውጥን የሚያጎለብት ጠንካራ ተሞክሮ እንደሆነ አስረድተዋል።

እህት ሌቲሲያ ተማሪዎቹ ይህንን ልምድ ወደ ማኅበረሰባቸው በመውሰድ ሲኖዶሳዊነትን የሕይወት እውነታ እንደሚያደርጉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ አክለውም ሂደቱ በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን በጋራ የመገንባት መንገድ ነው ብለዋል።

ሲኖዶሳዊነት በነገረ-መለኮት እና በአገልግሎት ምስረታ ላይ
ከኤል ሳልቫዶር የመጣው የነገረ መለኮት ምሁር ወጣት ፋቢዮ፥ የዘርዓ-ክህነት ተማሪዎች እና የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች ሲኖዶሳዊነትን እንዴት እንደሚያሳድጉ ለጠየቀው ጥያቄ መላሽ የሰጡት አቡነ ፍሎሬስ፥ የነገረ መለኮት ሊቃውንትን እና የዘርዓ-ክኅነት ተማሪዎች በእውነታው እንዲሳተፉ በማበረታታት ከአካዳሚው ዓለም ውጣ በማለት በማኅበርሰቡ የተገለሉ ሰዎች ሕይወት መለማመድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘርዓ-ክህነት እና የነገረ መለኮት መርሃ ግብሮች በሲኖዶሳዊ ዕይታ እንደገና መገምገም አለባቸው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ የዘርዓ-ክኅነት ተምህርት ቤተ ተማሪዎች እና የነገረ መለኮት ሊቃውንት ለዚህ ቀጣይ ውይይት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ በመጋበዝ፥ ሲኖዶሳዊነት በሁሉም የቤተ ክርስቲያን ምሥረታ ደረጃዎች ውስጥ መመላለስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሃይማኖቶች ውይይት እና ዓለም አቀፍ ሲኖዶሳዊነት
6ኛውን እና የመጨረሻውን ጥያቄ ያቀረበችው የሲንሲናቲ ተማሪ ወጣት ሚካ፥ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይትን በማስተዋወቅ ምእመናንን እንዴት መደገፍ እንደምትችል እና ሲኖዶሳዊነት ከሌሎች የእምነት ወጎች ምን ትምህርት እንደሚወስድ ለጠየቀችው ጥያቄ መልስ የሰጡት

ብፁዕ ካርዲናል ሆሌሪች፥ ጃፓን ውስጥ ከልዩ ልዩ ሃይማኖቶች የመጡ ተማሪዎችን ከማስተማር ያገኙትን ልምድ በማስታወስ፥ ይህ አጋጣሚ እግዚአብሔር በሁሉም ባህሎች እና ሃይማኖቶች ውስጥ መኖሩን ለመገንዘብ እንደረዳቸው ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሆሌሪች በማከልም፥ ሲኖዶሳዊነት ለሃይማኖቶች የግጭት ምንጭ ሳይሆን ታላቅ የወንድማማችነት መንገድ በመሆን ዓለምን ማስተማር እንደሚችል ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች የእምነት ትውፊቶች ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን እንደ ማኅበራዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ፍትህ ለማምጣት ወንድሞች እና እህቶች ለጋራ ተልዕኮ አንድ የሚሆኑበት ነው በማለት አስረድተዋል።

"መናገር ብቻ ሳይሆን አንድ ላይ በመሥራት፣ በመገናኘት፣ እርስ በርስ በከባበር በፍቅር እና በጓደኝነት ማደግ እና ለሰው ልጅ የሚጠቅም እርምጃ መውሰድ የተልዕኮ አካል እንደሆነ እና የዚህ ተልዕኮ አካል ደግሞ እግዚአብሔርን ለዓለም ማወጅ ነው” ብለዋል።

የጸሎት እና የጥያቄዎች “ሞዛይክ”
በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ተማሪዎቹ በሮም በቆዩባቸው ጊዜያት ያቀረቧቸውን ጸሎቶች እና ጥያቄዎች የሚወክል የጥበብ ሥራ ያሳዩ ሲሆን፥ እያንዳንዳቸው በተራ ጸሎት እንዲደርሱ ተጋብዘው፥ ይህም ለበለጠ ሲኖዶሳዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና የአድማጭ ቤተ ክርስቲያን የጋራ ተስፋን የሚያሳይ መሆኑ ተነግሯል።

 

19 October 2024, 16:41