የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ በሦስተኛ ቀን መግለጫው፥ ሁሉንም ማዳመጥ እንደሚገባ አሳሰበ

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ 351 አባላት በተገኙበት ሁለተኛ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ዓርብ መስከረም 24/2017 ዓ. ም. መግለጫ ሰጥቷል። በአምስት ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተመድበው ውይይቶችን ያካሄዱት የጉባኤው ቡድኖች በጋራ ጭብጦቻቸው ሲኖዶሳዊነትን እንደ ብልሃት ሳይሆን እንደ ዘይቤ የተመለከቱበትን፣ “ሴቶች እና ሌሎች ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ሚና፣ የቤተ ክርስቲያን ትዕዛዝ ባለማክበራቸው እንደተገለሉ የሚሰማቸውን ማዳመጥ” በሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የመልካም ምግባር ስጦታዎች ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሆን አይጠበቅባቸውም
መግለጫው ላይ በተለይም የኢየሱስ አካል ተደርጋ በምትታይ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ አገልግሎቶች እና የመልካም ምግባራት ስጦታዎች መኖራቸው በተደጋጋሚ የተነሳ ሲሆን፥ በዚህ መሠረት የምዕመናን በተለይ የሴቶች ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚለው ርዕሥ ትንተና ተጥቶበታል። ሪፖርት አቅራቢዎቹ በሙሉ በመልካም ምግባር ስጦታዎች ጠቃሚነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ሁሉም የመልካም ምግባር ስጦታዎች እንደ ቤተ ክኅነት አገልግሎት ተደርገው መወሰድ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የሴቶች ሚና እና አስተዋፅኦ
የውይይት ቡድኖቹ አንዳንድ ርዕሠ ጉዳዮች በእውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ማስተዋል እንጂ በልማዳዊ እና ርዕዮተ ዓለማዊ አዝማሚያ በጭፍን የተነሱ አለመሆናቸውን እንዲያስቡበት መጠየቃቸውን ተናጋሪዎች ገልጸዋል። በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ተናጋሪዎቹ፥ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሴቶች የሚሰጥ ክብር በጥምቀት ለሚያምኑ ሁሉ የሚሰጥ ክብር ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሴቶች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጋር በተያይዘ የሚሰጡ ቅዱሳት ምስጢራትን በተመለከተ አንዳንድ የሲኖዶሱ አባላት እንደ “የማጽናናት አገልግሎት” ያሉ የአገልግሎት ዘርፎች መኖር ስለሚችሉበት ሁኔታ ጠለቅ ያለ ጥናት ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመው፥ ይህም ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያበረከቱትን ጠቃሚ አስተዋጽኦ በማስታወስ እና በቀጣይነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የሲኖዶሱ አባላት በተጨማሪም የተጠመቁት ሁሉ እኩል ክብር እና የጋራ ኃላፊነት እንዳላባቸው አጽንኦት የተሰጠ ሲሆን፥ ይህ በተለይም ሴቶች እና ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ሕይወት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እንዲካተቱ ለማሰላሰል መሠረታዊ ነው ተብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጉባኤው ተሳታፊዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ

ምእመናን፣ ቋንቋ እና የድሆች ገጽታ
የሲኖዶሱ የተግባር መርሃ ግብር በየአገራቱ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ምእመናንን እና ቤተሰቦችን እምብዛም እንደማይጠቅስ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን እራሱን በባሕል የገነባ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናት እና በባሕሎች መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ መታየት እንደሚገባ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ የቋንቋ ጉዳይም የተነሳ ሲሆን፥ “አንዳንድ የአውሮጳ እና የምዕራቡ ዓለም አመለካከት ውጤት የሆኑ የአሠራር መንገዶች ተቀይረው ቀላል እንዲሆኑ ተጠይቋል። እንደ መጨረሻ ነጥብም ከሐዋርያዊ አገልግሎት ልምዶች እና እውነታዎች አኳያ የሰው ሕይወት ከንድፈ ሃሳብ የላቀ በመሆኑ ሁለት ግብዣዎችን በማቅረብ በጦርነት እና በዓመፅ በደል የደረሰባቸውን ድሆች መመልከት አስፈላጊ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ከጣልቃ ገብነት የተለየ ነው!
ለጠቅላላ ጉባኤው አምስት ሪፖርቶች ከቀረቡለት በኋላ ሌሎችም ሃሳባቸውን እንዲገልጹ ዕድል የተሰጣቸው ሲሆን፥ ሰላሳ ስድስት ዋና ተናጋሪዎች በንግግራቸው የምእመናን አስፈላጊነት፣ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ሚና እና የሴቶች መንፈሳዊ አገልግሎት “የማጽናናት አገልግሎት” ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ስብከቶችን ማቅረብ እና የቤተ ክርስቲያን ተቋማት መሪዎች መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም በዓለም መላውን ማኅበረሰብ የሚመሩትን ምእመናንን ጨምሮ፣ የሚስዮናውያንን ምሳሌ በማስታወስ፣ አንዳንድ ሴቶች በእግዚአብሔር የተጠሩ እና ከቤተ ክርስቲያን በኩልም ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ጠቁመዋል። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች እና በመልካም ምግባር በጥናት ቡድኑ እንዲሳተፉ እና የዚህ ቡድን ሥራ ውጤት በሲኖዶሳነት ሥፍራ ውይይት በማድረግ ምክር እና ማስተዋል እንዲሰጥም ጥያቄ ቀርቧል።

የውይይት እና የመደማመጥ አስፈላጊነት
የሲኖዶሳዊነት መንፈስ ማዳበር አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸው ስብሰባው፥ በንቃት ማዳመጥ፣ ልዩነትን ከሚያራምዱ እና ምቾት ከሚነሱ ጋርም ያለ አድልዎ ይበልጥ መቀራረብ እና መደጋገፍ እንደሚገባ ተነግሯል። አንዳንድ የጉባኤው ተናጋሪዎች ከሌሎች ባህሎች፣ ፍልስፍናዎች እና ሃይማኖቶች ጋር ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው፥ ሌላውን ማክበር የእግዚአብሔርን ሕዝቦች አንድ ስለሚያደርጋቸው እውቅና መስጠት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

“የድንኳኑን ሥፍራ እናስፋ!” ከሚል መሪ ሃሳብ በመነሳት ማዳመጥን በተመለከተ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በድህነት እና በስቃይ ውስጥ ያሉትን እና ከማህበረሰብ እና ከቤተ ክርስቲያን እንደተገለሉ የሚሰማቸውን የተፋቱትን፣ የተገለሉትን እና ወደ ተመሳሳይ ጾታ የመቅረብ ባሕርይ አለባቸው የሚባሉትን ቀርቦ ከልብ ማዳመጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የሥርዓተ አምልኮ ቦታን ማስፋት
ቤተ ክኅነትነትን አስመልክቶ በተነሳው ርዕሠ ጉዳይ ላይ “በክርስቲያኖች መካከል ጌታ እና አገልጋይ የለም” ያሉት የጉባኤው ተናጋሪዎች፥ አንዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ ሁላችንም ወንድማማች ነን” ሲሉ ገልጸዋል። በተደጋጋሚ የቀረበውን የሥርዓተ አምልኮ ጭብጥ ያነሱት የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ እና የጠቅላላ ጉባኤው የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ፥ “ሥርዓተ አምልኮ የሲኖዶሳዊነት መስታወት ሊሆን ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ በመካሄድ ላይ
የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ በመካሄድ ላይ

የዲጂታል ተልዕኮ አስፈላጊነት
እህት ሲስኪያ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ተግዳሮቶችን በተጋፈጠው በዲጂታል ተልዕኮ ውስጥ የመሥራትን አጣዳፊነት አፅንዖት ሰጥተው፥ 65 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ዲጂታል የመገናኛ መሣሪያዎችን አዘውትሮ እንደሚጠቀም ተናግረው፥ ሲኖዶሳዊ ጉዞ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጳጳሳት ጉባኤዎች ውስጥ ጽ/ቤቶች እየተቋቋሙ እንደሚገኙ፣ ከሚስዮናውያን ጋርም ስብሰባዎች እየተካሄዱ እና መነኮሳቱ የዲጂታል ሚሲዮናዊነት ልምዶቻቸውን እየተካፈሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የጋዜጣዊ መግለጫ ተሳታፊዎች
የጋዜጣዊ መግለጫ ተሳታፊዎች

ሚስዮናውያን በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ወደ ተለያዩ ሰዎች ዘንድ በመቅረብ እውነትን የሚፈልጉት እና በዓለም የቆሰሉ፥ አንዳንዴም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሉታዊ ተሞክሮ ያጋጠማቸውን እንደሚያጽናኑ እህት ሲስኪያ አስረተው፥ “ሳምራዊ” የወንጌል እሴቶችን እንደገና ማግኘት የሚፈልጉትን እና ስለ ኢየሱስ ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁትን ለመድረስ የዲጂታል መንገድ ጥሩ እንደሆነ እና በዚህ ዙሪያ ሲኖዶሳዊነት ትልቅ ተስፋ እንዳለው ተናግረዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ ስለ ሲኖዶሳዊነት ጸጋ ሲናገሩ፥ የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ እንደሚያበለጽጋት እና ቤተ ክርስቲያን ዛሬም የአውሮፓውያን ወይም የምዕራባውያን እንደሆነች ገልጸው ይህንን ጉዞ እርስ በርሳችን በመረዳዳት የምንኖር ከሆነ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ካቶሊካዊ እና ሁሉን አቀፍ ትሆናለች ብለዋል።

“እርግጥ ነው እኛ አውሮፓውያን ትሁት መሆንን መማር አለብን፣ አፍሪካውያን ግን መኩራራት የለባቸውም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሎፔዝ ሮሜሮ፥ “ስኬት በቁጥር ብዛት የሚመካ አይደለም” ብለው፥ በወንጌል በመኖር እርስ በርሳችን መረዳዳት አለብን ብለዋል።

የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ የሦስተኛ ቀን መግለጫ፥

 

05 October 2024, 17:44