የራትዚንገር ሽልማት በጨለማ ወቅት የተስፋ መምህርነት ትሩፋትን የሚያከብር መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በቫቲካን ሐዋርያዊ ሕንጻ ውስጥ ዓርብ ኅዳር 13/2017 ዓ. ም. በተካሄደው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2024 የራትዚንገር ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ያከናወኗቸውን ዘላቂ ትሩፋቶችን አብራርተዋል። የዘንድሮው የራትዚንገር ሽልማት አሸናፊዎች አይርላንዳዊው የነገረ-መለኮት ምሁር ሲርል ኦሬጋን እና ጃፓናዊው የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ኤትሱሮ ሶቶ መሆናቸው ታውቋል።
“ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክት 16ኛ የተስፋ ድምፅ ናቸው!”
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ “የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ አስተምህሮዎች በዘመናችን የጥላቻ እና የክፋት ትግሎች ውስጥ እምነት እና ተስፋ እንዲኖረን ያሳስቡናል” ሲሉ ገልጸዋል።
“ተስፋ እና ድነት” የሚለው እና በተስፋ ላይ ያተኮረው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ሙሉ በሙሉ በሰው ልጅ እና በክርስቲያናዊ ተስፋ ላይ የሚያጠነጥን መሆኑን ተናግረው፥ ሁለቱ የሽልማቱ አሸናፊዎች፥ ለሥነ-መለኮት፣ ለሰብዓዊ እና ክርስቲያናዊ ምስክርነት ሰጥተው እውነትን በሁሉ አቅጣጫ ከፈለገው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሴፍ ራትዚንገር ሕይወት ጋር አንድ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የሽልማቱ አሸናፊዎች
ካርዲናል ፓሮሊን ቀጥለውም በአሜሪካ በሚገኘው የኖትር ዳም ዩኒቨርሲቲ የነገረ-መለኮት መምህር የሆነውን አይርላንዳዊ የነገረ-መለኮት ምሁር ሲርል ኦሬጋንን በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ ተሸላሚው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ትህትና እና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት እግዚአብሔርን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት በማሰቡ ምስጋናን አቅርበዋል።
የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ ጃፓናዊውን ኤትሱሮ ሶቶን ያስታወሱት ካርዲናል ፓሮሊን፥ በባርሴሎና በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቴድራል በሠራቸው ሥራዎች እንደሚታወቅ ገልጸው፥ የጥበብ ባለሞያው መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተላለፍ ጥበብን በመጠቀም የጋኡዲ ራዕይ እንዲቀጥል ማድረጉን አስረድተው፥ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከታት ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ በውበት እና በእምነት ውህደት ላይ ያላቸውን እምነት በማስተጋባት እና መጽሐፍ ቅዱስን በድንጋይ በማስመሰል መሆኑን ተናግረዋል።
የራትዚንገር ሁሉ አቀፍ ቅርስ
የራትዚንገር ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ሥራ ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፥ በሚኒሶታ በሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ዩኒቨርስቲ የተጀመረው አዲሱ የ “ቤነዲክቶስ 16ኛ መንበር” ተነሳሽነት፥ እንቅስቃሴው በዘርፉ እና በባህሎች ላይ ያለውን ዘላቂ ተጽእኖ ያሳያል ብለዋል።