ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በድሃ አገራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንደገለጸው 30% የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ለሞት የሚዳርግ የሙቀት ማዕበል በየዓመቱ ከ20 ቀናት በላይ እንደሚያጠቃው አስታውቋል።
በቅድስት መንበር የኩባ፣ የቦሊቪያ እና የቬንዙዌላ ኤምባሲዎች ኅዳር 19/2017 ዓ. ም. ባዘጋጁት ጥናታዊ ጉባኤ ላይ በርካታ ካርዲናሎች እና የነዚህ አገራት ተወካዮች ተገኝተው እየተከሰቱ ባሉት የአካባቢ ቀውሶች ዓለም አቀፍ ተፅእኖ ላይ ተወያይተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለተሳታፊዎቹ በላኩት መልዕክት፥ የአየር ንብረት ለውጡ በማደግ ላይ የሚገኙ ድሃ አገራትን እየጎዳ እንደሚገኝ እና ምልክቶቹም ሊደበቁ የማይችሉ መሆናቸውን በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
ሰው አምባገነናዊ መሆን የለበትም
የላቲን አሜሪካ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝደንት እና የጳጳሳት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ፕሬቮስት በዓለም ላይ እየተባባሰ ያለውን የአካባቢ ቀውስ አስመልክተው ባደረጉት ንግግር “ከቃላት ወደ ተግባር የምንሸጋገርበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ አሳስበዋል። ለዚህ ተግዳሮት የሚሰጠው መልስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበትም ብለዋል።
“በተፈጥሮ ላይ የበላይነትን መቀዳጀት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠው ሃላፊነት ነው” በማለት ያስረዱት ካርዲናል ሮበርት፥ ይሁን እንጂ ጨካኝ መሆን የለበትም ብለው፥ ከአካባቢው ጋር የተዛመደ ግንኙነት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። የቴክኖሎጅ ዕድገት ጎጂ ውጤቶች ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቀቁት ካርዲናል ሮበርት፥ ቅድስት መንበር አካባቢን ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፥ ቫቲካን እንደ የፀሐይ ፓነሎችን በመትከል እና በኤሌክትሪክ ወደሚሽከረከሩ መኪኖች መሸጋገሯን በምሳሌነት ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩ አይካድም!
የጳጳሳዊ ሳይንስ አካዳሚ ቻንስለር ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፥ የሰው ልጅ አካባቢን የመንከባከብ ጥሪ ላይ አጽንኦት ሰጥተው፥ “ዓለም የተፈጠረው በአጋጣሚ ሳይሆን እግዚአብሔር ሆን ብሎ የፈጠረው እና ሁሉም ሰው አብሮት ፈጣሪ እንዲሆን ተጠርቷል” ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ በጣም የተጎዱት በማደግ ላይ የሚገኙ ድሃ አገራት መሆናቸውን አጽንኦት የሰጡት ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፥ አካባቢው የተስተናገደበት መንገድ አሳዛኝ እና ገላጭ የመዋቅራዊ ኃጢአት ምሳሌ ነው” ሲሉ አስረተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩን የሚክዱ እንቅስቃሴዎችን የጠቀሱት ካርዲናል ፒተር ታርክሰን፥ የአየር ንብረት ድንገተኛ አደጋ ግምታዊ ሳይሆን የሰው ልጅ በራሱ ላይ የሚያመጣው አደጋ ስለሆነ ፈጣን እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ገልጸዋል።
ከካርዲናል ፒተር ታርክሰን መልዕክት ጋር የሚስማሙት፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ “የአየር ንብረት ቀውስ መኖሩ የማይካድ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን አስታውሰዋል።
“ድሆች ብንሆንም ሁላችንም መብት አለን!”
የላቲን አሜሪካ የጳጳሳት ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ወ/ሮ ኤሚልስ ኩዳ በብራዚል መላውን ማኅበረሰቦች ያጠፋው የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በስፔን በተከሰተው አደጋ ያህል በዋና ዋና ዜናዎች እንዳልተነገረ ጠቁመው፥ ሁሉም የላቲን አሜሪካ አገራት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክተው ባወጡት አጀንዳዎች ላይ እንዲያተኩሩ ጠይቀዋል።
“በድህነት ውስጥ ያለ አህጉር ሕዝቦች ነን” ያሉት ጸሃፊዋ፥ “ነገር ግን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ስንቀመጥ ሁላችንም አንድ ዓይነት ቦታ እና ነፃነት የማግኘት መብት አለን” ብለው፥ “ደሃ ነን ማለት ሙያዊ ብቃት የለንም ማለት አይደለም” ሲሉ አበክረው ተናግረዋል።
ወደፊት የሚመጣውን አደጋ እንዴት መቋቋም ይቻላል?
ለአየር ንብረት ቀውስ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ለመደገፍ በሚል ዓላማ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” መርሆዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ድርጅቶች እየሠሩ መሆናቸው ታውቋል። በቬንዙዌላ ኤኮሶሻሊስታዊ የሕዝብ ኃይል ሚኒስትር አቶ ሆሴ አሌሃንድሮ ሎርካ ቪጋ ወጣቶች አካባቢያዊ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ የሚያስፈልጓቸው መሣሪያዎችን እና ትምህርቶችን እንዴት መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቅርቡ የተጠናቀቀውን 29ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባን ተከትሎ በኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ሕግ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፔድሮ ሉዊስ ፔድሮሶ፥ ለአየር ንብረት ቀውሱ የሚሰጠው ምላሽ የተከፋፈለ በመሆኑ በታዳጊ አገራት ውስጥ ችግሩን ለመቅረፍ የዕርዳታ መጠን በበቂ ደረጃ አለመመደቡን ገልጸዋል።
ምክትል ዳይሬክተሩ በማከልም፥ የኩባ አብዮተኞች የአየር ንብረት ለውጥን በማስመልከት የተናገሩትን ሐረግ በመጥቀስ፥ “ከረጅም ጊዜ በፊት ማድረግ የነበረብንን ለነገ ማሳደሩ በጣም ይዘገያል” ብለው ለችግሩ ፈጣን መፍትሄ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።