ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር፥ “የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ በችግር ጊዜ የሚደርስ ነው” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ለስብሰባው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ ቅድስት መንበር በዩክሬን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በምያንማር፣ በኢትዮጵያ እና በየመን የሚካሄዱ ግጭቶችን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ተናግረው፥ ሰላምን በማስፈን፣ ሰብዓዊ መብቶችን እና የእምነት ነፃነትን በማሳደግ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በመንከባከብ፣ የመናናቅ ባሕልን በመቃወም ስደተኞችን መደገፍ እና የጤና እንክብካቤ ተደራሽነትን ማስተዋወቅ የማይናወጥ አቋሟ መሆኑን አስረድተዋል።
ቅድስት መንበር በተጨማሪም መልካም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በመደገፍ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት፣ ወንድማማችነትን እና ብዝሃነትን እንደምታበረታታ የገለጹት አቡነ ፖል ሪቻርድ፥ “የችግር ጊዜ ደራሽ” ተብላ የምትገለጸው ቅድስት መንበር ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዓለም አቀፋዊ ውይይቶች ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንደምትጫውት ገልጸው፥ ዋና ዋና የተባሉ የዓለም ኃያላን መንግሥታት ብዙ ጊዜ ውጤቱን ብቻቸውን ለመውሰድ እንደሚጥሩ አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በማከልም በአሁኑ ወቅት ከ184 ሀገራት ጋር ግንኙነት ያለውን እና ከዓለም አቀፍ የአስተዳደር ተቋማት ጋር ጥልቅ ትስስር ያለውን የቫቲካን ዲፕሎማሲ ጥሪ እና መንገዶችን በማስመልከት ገለፃ አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር “የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ በዘመናዊው ዓለም” በሚል ርዕስ ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የዲፕሎማሲ ጥናት ማዕከል ያዘጋጀው ጉባኤ አካል እንደ ነበር ታውቋል።
ውይይት፣ ትህትና እና የሰላም ግንባታ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ከታሪካዊ ዕይታ ጀምሮ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ያለበትን ደረጃ ሲገልጹ፥ ለአሥርተ ዓመታት የተካሄደውን የመገናኛ መንገድ ግንባታ፣ ውይይት፣ ትዕግስት እና ትህትና የተሞላበት አካሄድ በማሳየት ሊታረሙ የማይችሉ የሚመስሉ ግጭቶችን ለመፍታት እና በተፋላሚ ወገኖች መካከል የመልካም ፈቃድ ምልክቶችን በማጎልበት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በመሠረቱ ይህ “የምሕረት ዲፕሎማሲ” ለአብሮነት እና ለጋራ ጥቅም እውነተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚያሳይ፥ እንደ ረቂቅ ግብ ሳይሆን የውጭ ዕዳ መሰረዝን፣ ትብብርን እና የልማት ፖሊሲዎችን በማራመድ እንደ ሞት ቅጣት ያሉ ከባድ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን በማውገዝ የሰውን ልጅ ክብር ለማሳደግ እንደሚጥር አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ዋና ዲፕሎማትነት
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ በፖላንድ በሚገኝ የሉብሊን ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ “KUL” ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ የቫቲካን ዲፕሎማሲ አወቃቀሮችን እና ቁልፍ አካላትን እንደ ሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት የመሳሰሉት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ መገኘትን እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ባልነበሩባቸው አካባቢዎች ቅድስት መንበርን የሚወክሉ የሐዋርያዊ ልኡካን ሚናን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ይህን ሰፊ እና በደንብ የተገለጸውን መዋቅር በሚመሩበት ወቅት የመጀመሪያው ዲፕሎማት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መሆናቸውን አስረድተዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ አስተዳደር እና ምሥራቅ አውሮፓን የሚመለከቱ ጥያቄዎች እነዚህን ርዕሠ ጉዳዮች በበቂ ሁኔታ እንደሚያነሱ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ዛሬም ቢሆን “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተፅዕኖ መመልከት እንችላለን” ብለዋል።
“የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃን የሚያበረታቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ንግግዮች እና ተግባሮች ናቸው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሥነ-ምግባራዊ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሳይታክቱ በሐዋርያዊ ምክር፣ በጸሎት፣ በስብሰባ፣ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን ይፋ በማድረግ እና በዓለም ዙሪያ በሚደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በኩል የተረሱትን እየጎበኙ፣ ወደፊት ዓለማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ጎጂ ልማዶችን በማስጠንቀቅ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን በመጋፈጥ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በግጭት አፈታት ውስጥ የተደረጉ ጥረቶች
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ በዩክሬን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ ውስጥ በሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ ቫቲካን ከትዕይንቱ በስተጀርባ ግጭቶችን ለመፍታት በምታደርገው ጥረት ላይ ትኩረት በማድረግ ቅድስት መንበር በገለልተኝነት በመንቀሳቀስ እና የሰላም ሃሳብን በመደገፍ ፍትሃዊ ግንኙነትን እና ዓለም አቀፍ ደንቦችን በማክበር እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን በመጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።
የሰብዓዊነት መርህን ከወታደራዊ ፍላጎት ጋር በማድረግ ፈጽሞ መደራደር እንደማይገባ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በተለይም ብዙውን ጊዜ የተረሱ ክልሎችን ማደስ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ሕይወት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ለምሳሌ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እስረኞችን መለዋወጥ እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ማመቻቸት ከቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መካከል እንደሆኑ ተናግረዋል።
በሕይወት የመኖር መብት
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በማከልም ቅድስት መንበር ለሰብዓዊ መብቶች ያላትን ቁርጠኝነት በማጉላት የመኖር መብት እና የሞራል ደረጃዎችን በመጠበቅ ማንኛውም ሰው እንደ እግዚአብሔር ልጅ በማይገረሰስ ቅድስናው ከፅንስ ጀምሮ እስከ ተፈጥሯዊ ሞት ድረስ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደሚገባ አስረድተዋል።
አንዳንድ አገራት ወይም ጥምረቶች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በተለየ መንገድ በሰብዓዊ መብቶች እና ክብር ላይ ልዩ ሃሳቦችን በመጫን ሰብዓዊ እና የልማት ዕርዳታዎችን ለመስጠት ፍቃደኞች አለመሆናቸው ቅድስት መንበርን እንደሚያሳስባት ተናግረዋል። ቫቲካን ለዓለም አቀፍ የጤና አጠባበቅ ያላትን ቁርጠኝነት በመጥቀስ እንደተናገሩትም፥ ወደ ዓለም አቀፋዊ ርዕዮተ ዓለም አጀንዳ ከተሸጋገሩ አንዳንድ አጨቃጫቂ ጽንሰ-ሐሳቦች መካከል ለምሳሌ “ፅንስን የማቋረጥ መብት” እየተባለ የሚጠራውን አስታውሰዋል።
የሃይማኖት ነፃነት
“የሃይማኖት ነፃነት ሌላው ማዕከላዊ ጭብጥ ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሃሳብ ላይ በማሰላሰል፥ ሃይማኖትን ለፖለቲካዊ አለመግባባቶች መሣሪያነት መጠቀምን መቃወም እንደሚያስፈልግ ደጋግመው ተናግረው፥ ይህም አድልዎን፣ ብጥብጥን አልፎ ተርፎም ጦርነትን እንደሚያስከትል ቅድስት መንበር ሳታቋርጥ አጽንኦት መስጠቷን ተናግረዋል። ቅድስት መንበር ለሃይማኖት ነፃነት ሕዝባዊ ገጽታ የመንግሥትን ሕጋዊ የራስ ገዝ አስተዳደርን በማክበር በመንግሥት እና በሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች መካከል ጤናማ ውይይቶች እንዲካሄዱ ማድረጓንም ገልጸዋል።
በቫቲካን ዲፕሎማሲ ውስጥ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረገውን እንክብካቤ፣ የመናቅ ባህልን ማስወገድን፣ ቴክኖሎጂን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመሳሰሉ ጉዳዮችን የዘረዘሩት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ሰዎችን በአገልግሎታቸው እና በቴክኖሎጂ ዕድገት ብቻ መመልከት፣ ግሎባላይዜሽን በሰው ኃይል ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖን እና አሳሳቢ ጉዳዮችን በመገምገም ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎድል የንቀት ባህልን መቃወም እንደሚገባ ተናግረዋል። በስደት፣ በጦርነት፣ በግጭት እና በድህነት የተፈናቀሉ ወደ 120 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች መፍትሔን ማግኘት የቅድስት መንበር ጥረት እንደሆነ ደግመው ተናግረዋል። ድህነትን ለማጥፋት ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እና ጥረቶች በማድረግ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተው፥ ዓላማውም የሰው ልጅ ወንድማማችነትን ከግዴለሽነት ባሕል ለመከላከል እንደሆነ አስረድተዋል።
“መርዛማ መቅሰፍት” የተባለው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር
ቅድስት መንበር ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን እና ሌሎች ዘመናዊ ባርነትን ለማጥፋት በትጋት እንደምትሠራ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግንባር ቀደም የሥነ ምግባር ድምጾች በማሰማት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመዋጋት ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቁ ተናግረው፥
አስከፊ ድህነት፣ ሙስና፣ ኢፍትሃዊነት እና ኢኮኖሚያዊ መገለል፥ ብዙውን ጊዜ ለተለያዩ ዓላማዎች ለሚሸጡ፣ ለሚታለሉት፣ ለሚደበደቡት፥ በመጨረሻም ለሚገደሉት ወይም በማንኛውም ሁኔታ የአካል እና የአእምሮ ጉዳት ለሚደርስባቸው ቀጣይነት ያለው የፍትህ ጥያቄ እንደሚያስፈልግ፥ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን መንግሥታት እንዲዋጉ ቅድስት መንበር ማሳሰቧን ተናግረዋል።
የተስፋ ምልክት መሆን
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” ብለው ከገለጹት የዓለም ዳራ አንጻር፣ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ የተስፋ ምልክት ለመሆን ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው፥ “የቫቲካን ዲፕሎማሲ በዚህ መንገድ የጋራ ጥቅምን በማስቀደም ለመረጋጋት፣ ለደህንነት እና ለሰላም የጋራ ምኞትን የሚያረጋግጥ ድምጽ ሆኖ ይሠራል” ብለዋል።
መግባባቶች እና ስምምነቶች
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ቅድስት መንበር ከተለያዩ ሀገራት ጋር በመግባባት እና በስምምነት የምታደርጋቸውን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ አብራርተው፥ “በአንድ በኩል በየአገራቱ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት እና በቤተ ክህነት ጉዳዮች ላይ የመንግሥት ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነትን ለመከላከል እንዲሁም በሌላ በኩል በማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ዘርፎች ውስጥ ያለውን ውጤታማ ትብብርን ለማረጋገጥ የጋራ ጥቅምን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር መወያየት፣ ከቻይና ጋር በጳጳሳት ሹመት እና መሰል ጉዳዮች ላይ የተደረሰውን ጊዜያዊ ስምምነት በዋቢነት በመጥቀስ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እየጎለበቱ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
“ድጋፍ መስጫ ያልተወሳሰበ ኃይል”
ቅድስት መንበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1949 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ቋሚ ታዛቢነት፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዋናነት እንደ የሥነ-ምግባር አመራር ኃይል ሆና በመሥራት ከፖለቲካ አጋርነት እና ከቡድን ነፃ በመሆን ትብብር እና ውይይት እንዲኖር ማድረጓን አስገንዝበው፥ ግጭቶችን በመፍታት እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውይይትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት ታማኝ አስታራቂ በመሆን የእርቅ እና የእርስ በርስ መገናኛ ድልድይ መገንባት እንደምትችል አስረድተዋል።