በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ  

የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ መትጋት አለባቸው ተባለ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በኒውዮርክ በተካሄደው የአባል አገራት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤል ካቻ ኅዳር 4/2017 ዓ. ም. በኒውዮርክ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ ግጭት በተከሰተባቸው ክልሎች ሰላም እንዲሰፍን መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው፥ አባል አገራት ወደ ተረጋጋ እና ደህንነታቸው የተጠበቀ ማኅበረሰብ የሚደርሱባቸውን መንገዶች እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል በ79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አራተኛ ዙር የኮሚቴ ስብሰባ አጀንዳ ቁጥር 51 ላይ በቀረበው ሰላምን የማስከበር ሥራዎች ግምገማ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕዝቦችን መጠበቅ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ በሰላም ማስከበር ስኬቶች እና ተግዳሮቶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ሰላም በእውነት የሚያብብበትን ሁኔታ ለመፍጠር አዲስ ቁርጠኝነትን የሚያነሳሳ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ሰላምን ለማስከበር ለሚደረጉት ጥረቶች የማያቋርጥ ድጋፍ ያስፈልጋል

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል በመቀጠልም፥ ሰላምን ለማስከበር የሚደረጉ ጥረቶች ያላቸውን ዘላቂ ጠቀሜታ በማረጋገጥ በግጭት የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም እገዛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ዜጎችን በመጠበቅ፣ የፖለቲካ ሂደቶችን በመደገፍ እና ሰብዓዊ መብቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች፣ በአካባቢ ቀውሶች እና በሰብዓዊ መብት ረገጣዎች መጨመር የሰላም ማስከበር ሥራዎች አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ጋብርኤል ካቻ አክለውም፥ “እነዚህ ተልዕኮዎች ከአባል አገራት ወጥ እና የተቀናጀ ድጋፍን በማግኘት ረገድ ችግሮች እንደሚገጥማቸው ማስተዋል እጅግ ያሳዝናል” ብለዋል።

ሰላምን ለመጠበቅ የሚያግዝ የአባል ሀገራት አንድነት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል በቅርቡ በሠላም አስከባሪ አባላት ላይ የደረሰው ጥቃት ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት ገልጸው፥ አባል አገራት የሰላም አስከባሪ ሠራተኞችን ሕይወት ከአደጋ ለመጠበቅ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋገጥ፥ “በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረጉ ወሳኝ ተግባራትን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በንግግራቸው መደምደሚያ፥ “ሰላም ትልቅና ውድ ዋጋ ያለው፣ የተስፋችን ዓላማ እና መላው የሰው ልጅ ምኞት ነው” ብለው፥ ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ትጋት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

15 November 2024, 14:13