ቫቲካን ዩክሬናዊያን ታዳጊዎችን እና እስረኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በትጋት እንደምትሰራ አስታወቀች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የካናዳ ከተማ በሆነችው ሞንትሪያል በተካሄደው በዚህ የሰላም ጉባኤ ላይ ቫቲካን በሩሲያ ሃይሎች በምርኮ የተወሰዱትን የዩክሬን ታዳጊዎች፣ ወታደራዊ ሰራተኞች እና ሲቪሎች እንዲፈቱ የሰብአዊ ስራዋን ለመቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ሪቻርድ ጋላገር፥ “በሚያሳዝን ሁኔታ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ውጤት የሚጠበቀውን ያክል እንዳልሆነ ገልጸው፥ ምክንያቱም ደግሞ እንዲተገበሩ የታቀዱት ጉዳዮች “በጣም የተወሳሰቡ ናቸው” ብለዋል።
ይህ ኮንፈረንስ በዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የቀረበ የሰላም ዕቅድ ላይ ለመወያየት የተዘጋጀ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሲሆን፥ የመጀመሪያው የሰላም ጉባኤ የተካሄደው ባለፈው ሰኔ ወር በስዊዘርላንድ እንደነበር ይታወሳል።
ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እንዲቆም በሚል በስዊዘርላንድ አስተናጋጅነት በርካታ የዓለማችን ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት የሰላም ጉባኤ ከአራት ወራት በፊት ተካሂዷል።
የዚህ ቀጣይ የሆነው ጥቅምት 20 እና 21 2017 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሰላም ውይይት እቅዶች ውስጥ ከተካተቱት አስር ነጥቦች፣ ጉባኤው “ፕሮፖዛል ቁጥር 4” በተባለው አንቀጽ ላይ ትኩረት አድርጎ የተወያየ ሲሆን፥ ይህ አንቀጽ በስሩ ከያዛቸው ዋና ሃሳቦች ውስጥ “ሁሉም እስረኞች እና ተፈናቃዮች ይፈቱ” የሚል ጭብጥ እንደነበረውም ሊቀ ጳጳሱ አስታውሰዋል።
‘ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረች ወዲህ፣ ይህ የቅድስት መንበር ልዩ ተልእኮ ነው’ ያሉት የቫቲካን የሃገራት ግንኙነት ቢሮ ዋና ጸሐፊው፣ “የዩክሬን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ያቀረቡትን ጥያቄዎች በአወንታዊ መልኩ እንቀበላለን” ብለዋል።
የዘለንስኪ ጥያቄ እና የዙፒ ተልእኮ
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በመጀመሪያ በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱት ከ19,000 በላይ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ዩክሬናውያን መለቀቅ እና የእስረኞችን ልውውጥ በተመለከተ ለቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ጥሪያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ሂደቱ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስገኘት፥ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ሁለት የዩክሬን ታጋቾች መለቀቃቸው እና የተወሰኑ የታዳጊዎች ቡድን ወደ ሃገራቸው መመለስ ችለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄደው ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ወቅት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቫቲካን ሦስተኛውን የድጋፍ ጥያቄያቸውን በድጋሚ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይሄንን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ በ 2015 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ የጣሊያን ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት የሆኑት ብጹእ ካርዲናል ዙፒ “ፍትሃዊ ሰላም” ማምጣት የሚቻልባቸውን መንገዶችን ለመፈለግ፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ልዩ መልዕክተኛ በመሆን እና ሰብዓዊ እገዛዎችን ለማድረግ ወደ ኪየቭ እና ሞስኮ መጓዛቸውን ያስታወሱት የቫቲካን የሃገራት ግንኙነት ቢሮ ዋና ጸሐፊ፥ ይህ “የብፁዕ ካርዲናሉ ተልእኮ ዋና ዓላማ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ በያዝነው ዓመት ጥቅምት 4 እና 5 በድጋሚ ወደ ሞስኮ መጓዛቸውን ያነሱት ብጹእነታቸው፥ ‘ይህ ተልእኮ ሕጻናትን ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ማዕቀፍ እንዲፈጠር እና በሁለቱ ወገኖች መካከል መደበኛ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር አድርጓል’ በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
እነዚህ የቅድስት መንበር የሰላም ጥረቶች በሁለቱም አገሮች የሚገኙ ሐዋርያዊ ተወካዮች ማለትም የዩክሬኑ ሊቀ ጳጳስ ቫስ-ቫልዳስ ኩልቦካስ እና የሩሲያው ሊቀ ጳጳስ ጆቫኒ ዲ አኒሎ የተሳተፉበት የበይነ-መረብ ስብሰባዎችንም እንደሚያካትት ገልጸዋል።
የሁለቱ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ተወካዮች እገዛ
የቫቲካን የሃገራት ግንኙነት ቢሮ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር እንዳሉት፣ ‘በተለይም ሁለቱ ሐዋርያዊ ተወካዮች የተገኙበት፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ቀጥተኛ ግንኙነት የሰላም ውይይቱን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ’ ገልጸው፥ ‘በተለይም ሊቀ ጳጳስ ኩልቦካስ ወደ አገራቸው የሚመለሱትን ህፃናን ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ የካቶሊክ ተቋማትን ለይተው ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ‘ቅድስት መንበር አዲስ የዩክሬናዊያን ሕጻናት ስም ዝርዝር በድጋሚ እንዳቀረበች’ ያነሱት ብጹእነታቸው፥ “ቫቲካን ከበፊቶቹ በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ስም በማስተላለፍ የእስረኛ ልውውጥ እንዲደረግ እና እንዲፈቱ ጥሪ አቅርባለች” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ከባድ የጤና ችግር ላለባቸው እስረኞች የጋራ የሕክምና ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ሀሳብ እና የታሳሪዎቹ ዩክሬናዊያን ቤተሰቦች ለእስረኞቹ እንዲደርሱ ያቀረቡትን የሰብአዊ እርዳታ ጥያቄ ቅድስት መንበር እንደምትደግፍ በመግለጽ፥ በማከልም ሩሲያ የሟች ዩክሬናዊያን ወታደሮች አስከሬን እንድትመልስ ጥሪ አቅርበዋል።
በዩክሬን ውስጥ ያሉ የሩሲያ እስረኞች ሁኔታ
በተጨማሪም በኪየቭ የሚገኘው የቅድስት መንበር ሃዋሪያዊ ተወካይ ጽ/ቤት ለሊቀ ጳጳስ ጋላገር ባቀረበው ሪፖርት ‘በዩክሬን ከሚገኙት የሩሲያ እስረኞች መካከል አንዳንዶቹን እንደጎበኘ እና በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን’ የገለጸ ሲሆን፥ የዩክሬን እስረኞች ሁኔታን በሚመለከት በይፋ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሆነው በተሾሙት፣ በሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ መብቶች ተሟጋች እና የሩሲያ ፌዴሬሽን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ሃላፊ በሆኑት ግለሰብ ተመሳሳይ ማረጋገጫ የተሰጠ ቢሆንም፥ “ቅድስት መንበር እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አልቻለችም” ብለዋል።
መጠቀሚያ አለመሆን
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመጨረሻም ‘ሁለቱ ተደራዳሪ ሃገራት ማንኛውንም ሰብአዊ ጉዳዮችን እንደመገልገያነት ከመጠቀም እንዲታቀቡ’ በማሳሰብ፥ “ለሰብአዊ ድንገተኛ አደጋዎች መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።