ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ሶርያ ውስጥ ሁሉም ሰው የወደፊት ተስፋ እንዳለው ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ጠንካራ የሚመስለው አገዛዝ ተገርስሶ ነገሮች በፍጥነት መለወጣቸው ያሳደረባቸውን ስጋት” ገልጸው፥ ስልጣኑን የሚይዙት ሁሉንም ሰው የሚያከብር ሥርዓት መፍጠር እንደሚችሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህን የተናገሩት፥ ፕሬዝደንት አሳድ በአማፂያን እጅ ከወደቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሲሆን ደማስቆ ውስጥ ያለው የአገሪቱ ቤተ መንግሥት አዲስ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት የሚደረጉ ስብሰባዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ወደ ሰሜን ጣሊያን ከተማ ሚላን የተጓዙት የ “ሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ “ለጋራ ውይይት የሚረዱ ጥናቶች” በሚል ርዕሥ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንደሆነ ታውቋል። በሚላን ከተማ የሚገኘው ይህ የአል ኢሳ የምርምር ሽልማት አዘጋጅ ተቋም በካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ በኩል በአረብ እና በእስልምና ባሕሎች ላይ ጥናት ለሚያደርጉ ወጣት ተመራማሪዎች ሽልማቶችን የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።
ፈጣን ለውጦች
ካርዲናል ፓሮሊን በሶርያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊው ሁኔታ መሠረት በማድረግ እንደ ተናገሩት፥ “በሶርያ እየታየ ያለው ፈጣን ዕድገት ከሙስሊሙ ዓለም ጋር ግንኙነትን ለመፍጠር ጥሩ ዕድል ይሰጣል” ሲሉ ተናግረዋል። ካርዲናል ፓሮሊን ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰጡት አስተያየት፥ “በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ ባለፉት አጭር ሰዓታት ውስጥ በሶርያ የተፈጠረው ሁኔታ ነው” ብለው፥ በተለይም ሁኔታዎች በፍጥነት መከሰታቸው ሁላችንንም ያሳስበናል” ሲሉ ተናግረዋል። “አሁን በሶርያ ምን እየሆነ እንዳለ መረዳት አስቸጋሪ ነው” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ይህን የመሰለ ጠንካራ አገዛዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መውደቁ በጣም ገርሞኛል” ብለዋል።
ለግጽነት ያለው ተስፋ
“ለሁሉም ሰው ግልጽ እና ሁሉንም ሰው የሚያከብር ሥርዓት እንደሚመሠረት ተስፋዎች አሉ” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ወደ ፊት ምን እንደሚሆን ለመገመት ጊዜው ገና ነው” ሲሉ ተናግረው፥ “ለክርስቲያን ማኅበረሰቦች አክብሮት እንዳለ የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ ወደፊት እርስ በርስ በመከባበር በሰላም ለመኖር ይቻላል” ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። “ወደ ስልጣን የሚመጡት ለሁሉም ግልጽ እና አክብሮት ያለውን አገዛዝ ለመፍጠር ይጥራሉ” የሚለው የሁሉም ሰው ተስፋ እንደሆነ ተናግረዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን “ቅድስት መንበር ምንም እንኳን ሶርያ ውስጥ መደበኛ የሆነ ሚና ባይኖሩትም ነገር ግን የውይይት እና የዲፕሎማሲ ሥራዋን ትቀጥላለች” ሲሉ አስረድተዋል። “በዩክሬን ምንም ዓይነት መደበኛ ድርድር አልተጀመረም፤ ነገር ግን ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ መንገዶችን በመፈለግ እንደ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ታጋቾች እንዲለቀቁ ማድረግ እና ሰብዓዊ ዕርዳታን ማቅረብ በመሳሰሉ ጥረቶች ቅድስት መንበር በንቃት እንደምትሳተፍ አስረድተዋል።
የውይይት አስፈላጊነት
“እንደ ሁል ጊዜው ውይይት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው” ያሉት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ የሚገኝው የ “ሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የዘመኑ ማኅበረሰብ በሚጋሩ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ባሕሎች መካከል ያለውን ግንኝነት ለማጠናከር ዕድል እንደሚሰጥ አጽንዖት ሰጥተዋል። “እንደ ‘ሳክሮ ኩዎሬ’ ያለ ካቶሊካዊ የትምህርት ተቋም በዚህ ተነሳሽነት ግንባር ቀደም ሆኖ በመሥራቱ፣ የጋራ መግባባትን፣ ጥልቅ እውቀትን እና ትብብርን በማጎልበቱ እጅግ ተደስቻለሁ” ብለው፥ ዛሬ ፈተና የሆነው ዓለማችንን ለሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት መተባበር እንደሆነ ገልጸው፥ “ወደ ትብብርን እና አንድነት መመለስ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን በስብሰባው ላይ ያላቸው ተሳትፎ
በሰሜን ጣሊያን ሚላን ከተማ የሚገኘው የ “ሳክሮ ኩዎሬ” ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ባስተባበረው ዝግጅት ላይ የተገኙት ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የዩኒቨርሲቲው አስተዳዳሪ ከሆኑት ወ/ሮ ኤሌና ቤካሊ፣ የአረብኛ ቋንቋ እና ሥነ-ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር ከሆኑት መሐመድ አል ኢሳ እና ዋኤል ፋሩክ ጋር በመሆን ስብሰባውን ከተካፈሉ በኋላ ለአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዝግጅት የሚሆን የመስዋዕተ ቅዳሴን ማክሰኞ ታኅሣሥ 1/2017 ማለዳ ላይ አሳርገዋል።
ከሰዓት በኋላ በነበረው ዝግጅትም “አዲስ ኢኮኖሚ” በሚል አርዕስት፥ አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስንነት የሚዳስስ፣ በሥነ-ምግባር፣ በመተማመን እና በትብብር ላይ የተመሠረተ አዲስ ሞዴልን በሚያቀርብ በዶ/ር ቤካሊ የመጽሐፍ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሚላን ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርዮ ዴልፒኒ ለስብሰባው ተሳታፊዎች ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ዴ ሊንቼይ የተሰኘ የትምህርት ማዕከል የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልቤርቶ ኳድሪዮ ኩርዚዮ እና ሌሎች እንግዶችም በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።