ሃንስ ዚመር፥ “እኛ አርቲስቶች በፈጠራ ሥራዎቻችን ሰዎችን የማንቃት ግዴታ አለብን” ሲል ገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከንጉሣዊ የሙዚቃ ባንድ እስከ ጎርጎሮሳዊ ዝማሬዎች፣ ከሞንጎሊያውያን የጉሮሮ ድምጽ እስከ የሴኔጋል ከበሮ ክበቦች ምቶች ድረስ ሙዚቃ ማለቂያ የሌለውን የሰው ልጅ ገጽታን እንደሚያካትት ገልጾ፥ ሙዚቃ የሰውን ልጅ የሕይወት ጉዞን እስከ ድል እንደሚያጅብ አስረድቷል።
ለአቀናባሪ ሃንስ ዚመር ሙዚቃ የዘመናችንን ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ እና ብዙውን ጊዜ ስቃያቸውን ሳይስተዋሉ ለሚኖሩ ሰዎች ድምጽ የመስጠት ኃይል እንዳለው አስረድቷል። የሙዚቃ አቀናባሪው ሃንስ ዚመር በቫቲካን ከድሆች ጋር በመሆን ቅዳሜ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ. ም. ካቀረበው ኮንሰርት ቀደም ብሎ እንደገለጸው፥ እንዲህ ያለው ክስተት ለድሆች መጽናኛ ብቻ ሳይሆን በይበልጥም በዝግጅቱ ላልተገኙት የድጋፍ ድምጽ እንደሆነ ተናግሯል።
ሃንስ ዚመር የኮንሴርቱን ትኩረት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ የኮንሴርቱ ርዕሥ ሁሉንም እንደሚያጠቃልል በማብራራት ስለ ድሆች ሳይሆን ነገር ግን ከድሆች ጋር መሆኑን በመግለጽ፥ “ድሆችን በዓይናችን ስናያቸው እንደ ሰው ልንመለከታቸው ይገባል” ሲል አሳስቧል።
የሙዚቃ ኃይል
የራሱን የሙዚቃ ሥራዎች ወደ ቫቲካን ይዞ የመጣበት ጊዜ አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸው ዚመር፥ ቤተ ክርስቲያን ለመንፈሳዊ ሙዚቃ ያላትን ቁርጠኝነት እንደገና እንዲያንሰራራ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።
ሆሊውድ በጉድለቶች የተሞላ መሆኑን የሚገነዘበው ዚመር፥ ቤተ ክርስቲያን ትሰራው የነበረውን ወደ ተግባር በመመለስ አንዳችን ለሌላው በመሆን ሙዚቃን ለማቆየት የሚያስችል መንገድ መፈለግ አለብን” ብሏል። ቅዳሜ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ. ም. በቫቲካን በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሴርት ላይ 3,000 ድሃ ማኅበረሰቦች የተሳተፉ ሲሆን፥ ዳሪዮ ቬሮ እና ሞንሲኞር ማርኮ ፍሪሲና ባዘጋጁት እና ምርጥ የግራሚ ሽልማት አሸናፊ ሴሊስት ቲና ጉዋኦ የተሳተፈችበት አዲስ ሙዚቃ ቤተ ክርስቲያኑ አዲስ ሙዚቃ እያመጣች መሆኑን ዚመር ገልጾ፥ በዚህ መንገድም እርስ በርስ መደጋገፍ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድቷል።
ሙዚቃ ለማኅበራዊ ፍትህ
በአስደናቂ የፊልም ሥራዎቹ የሚታወቀው ዚመር፣ አርቲስቶች እና ሙዚቀኞች በማኅበራዊ ፍትህ ላይ አቋም ሊይዙ እንደሚገባ እንደሚያምን በመግለጽ፥ ሙዚቀኞች ለረዥም ዓመታት እንደ እውነተኛ ሰዎች የማይቆጠሩ መሆኑን በማስታወስ “ዛሬ ግን እውነተኛ ማንነታቸውን መመለስ መልካም ነው” ሲል ተናግሯል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1985 ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ታላላቅ ሙዚቀኞች በለንደን በሚገኝ ዌምብሌይ መድረክ ላይ ለበጎ አድራጎት የሚሆኑ ታሪካዊ ኮንሴርቶችን ማቅረባቸውን በማስታወስ፥ ከእነዚህም መካከል “ላይቭ ኤይድ”ን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ያ የሙዚቃ ዝግጅት ጊዜያዊ ቢሆንም ነገር ግን መልካም ተግባርን በማነሳሳት ረገድ ኃይለኛ ምሳሌ እንደ ነበር ዚመር አስረድቷል።
የ “ላይቭ ኤይድ” የሙዚቃ ኮንሴርትን አዘጋጆችን ሃርቪ እና ቦብ ጌልፎድን በቅርብ እንደሚያውቃቸው የገለጸው ዚመር፥ ከሙዚቃ ኮንሴርቱ አዘጋጆች ጋር ስላለፉት ታሪኮች ማውራት መልካም እንደ ሆነ በማስረዳት፥ “ላይቭ ኤይድ” የሙዚቃ ዝግጅት አስገራሚ እንደ ነበረ በማስታወስ፣ እየደበዘዘ የመጣ ቢሆንም ነገር ግን ወደ መድረክ መልሶ ለማምጣት እየተነጋገሩ መሆኑ ትሩፋቱን እንደሚያረጋግጥ እና በአጭር ጊዜ ውስጥም አንድ ነገር ሊያመጣ እንደሚችል አረጋግጧል።
ከዓመታት በኋላም ቀውሱ አልቀነሰም
የ “ላይቭ ኤይድ” ውርስ እነዚህን ጥረቶች የመጠበቅ አስፈላጊነትን ለማስታወስ እንደሚያገለግል ዚመር ተናግሮ፥ ዕርዳታን በማስመልከት “ላይቭ ኤይድ” ርዕሠ ጉዳዮች እንደ ቀድሞው ዛሬም ቢሆን አንገብጋቢ እንደሆኑ ገልጾ፥ የ “‘ቢቢሲ’ ምስሎችን እየተመለከትን ከዚያን ጊዜ የበለጠ መደንገጥ አለብን” ብሏል።
የሙዚቃ ቴራፒ
የሙዚቀኞች ኃላፊነት ከመዝናኛ አቅራቢነት በላይ እንደሆነ የሚናገረው ዚመር፥ ሙዚቃ የለውጥ መሣሪያ እና አስደናቂ የሕክምና ባህሪ እና የመፈውስ አቅም እንዳለውም አስረድቷል። የራሱን ተሞክሮ ሲገልጽም፥ ፒያኖ ሲጫወት በተወሰነ ጊዜ በክፍሉ ውስጥ ሌላ ማንም ሰው እንደሌለ እንደሚሰማው እና በቦታው ሕመሞቹ በሙሉ እንደሚጠፉ ገልጿል።
በዚህ ጥልቅ ግላዊ ልምዱ ሙዚቃ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የፍትህ መጓደል ሰለባዎችን ለመፈወስ ጠንካራ አስተዋጽዖ እንዳለው እና ሙዚቃ እንደ ሕክምና ዓይነት ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ እንደሚፈውስ እና እንደሚያድንም በማብራራት ሙዚቃ ለብዙዎች መሸሸጊያ ሊሆናቸው እንደሚችል፥ ለአፍታ ብቻ ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ከጨለማ ኃይሎች ለማረፍ ዕድል እንደሚሰጥ አስረቷል።
እንደ ሙዚቀኛ ፣ እንደ አርቲስት እና እንደ ሰዎች፥ እኛ ጥሩ የሚሆኑበትን ምናብ የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው የተናገረው ዚመር፥ ዘፈኖች ተቀናብረው፣ ፊልሞችም ተሠርተው፣ መጽሐፎችም ተጽፈው የሰዎችን መንፈስ የሚቀሰቅሱ እና የሚያሳትፉ መሆን እንዳለባቸው አሳስቧል።
የጦርነት ሙዚቃ እና የሰላም መዝሙር
ሙዚቃ ሁለት ባህሪ እንዳለው የተገነዘበ ዚመር፥ የቦብ ዲላን እና የጆአን ቤዝ ዘፈኖች የጦርነትን ከንቱነት በማስረዳት የመላውን ትውልድ ዕይታን እና ግንዛቤን በመቅረጽ ረገድ የፀረ-ጦርነት አቋም እንዳላቸው አስረድቷል።
የሰላም መዝሙሮች እና የጦርነት ሰልፎች መኖራቸውን የገለጸው ዚመር፥ ቤቶቨን ወይም ባክ ሙዚቃ የሰውን ልጅ ጨለማ ጎኖቹን ጨምሮ ጥልቀቱንም የሚያሳይ እና ከእርሱ ጋርም እንድንታገል የሚያደርጉ መልካም ምሳሌዎች መሆናቸውን አስረድቷል።
ወጣት ሙዚቀኞች በጥበብ ሥራዎቻቸው በኩል ስሜታቸውን ይግለጹ!
ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ከማጠቃለሉ በፊት ለወጣት ሙዚቀኞች ባስተላለፈው ግልጽ መልዕክቱ፥ ወጣት ሙዚቀኞች በጥበብ ሥራዎቻቸው በኩል ስሜታቸውን እንዲገልጹ እና ልዩ ልዩ የሙዚቃ ድምጾችን እንዲያሰሙ አሳስቧል።