አቡነ ዮሐንስ ጋይድ “የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በተግባር ለመግለጽ የወጣቶች ሚና ሰፊ ነው”።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ከግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም ከሆኑት ከአህመድ አል ጣይብ ጋር ያደረጉትን የ“ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ስምምነት ተግባራዊነት የሚከታተል ከፍተኛ ምክር ቤት አባላት፣ ትናንት በአቡ ዳቢ ከተማ ሰነዱ በፊርማ የጸደቀበትን ቀን አንደኛ ዓመት አስታውሰዋል። የምክር ቤቱ ከፍተኛ ኮሚቴ አባላት ትናንት ሰኞ ጥር 25/2012 ዓ. ም. በአቡ ዳቢ ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ማውጣታቸው ታውቋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለከፍተኛ የኮሚቴ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት “በዓለማችን ክፋት፣ ጥላቻ እና መለያየት ተጋንኖ የሚነገር ቢሆንም ተደብቀው የሚገኙ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የፍቅር፣ የወንድማማችነት እና የሕብረት ጎዳናዎች፣ በመልካም ውይይቶች ሊገኝ የሚችል የአንድነት ተስፋ፣ አንዱ ሌላውን ይበልጥ በማወቅ እና በመረዳት የወንድማማችነት መንፈስ የሚገኝበት ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት የሚያስችል መልካም ፈቃድ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ አለ” ማለታቸው ይታወሳል።
የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ምሳሌነት፣
በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት የአህመድ አል ጣይብ የቀድሞ የሕግ አማካሪ አሁን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የሆኑት መሐመድ አብደል ሳላም ትናንት በአቡዳቢ ከተማ የተደረገውን ስብሰባ በንግግር ስከፍቱ እንዳስታወቁት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኘውን የሰው ዘር በሙሉ በማነሳሳት ለወንድማማችነት ፍቅር የቀሰቀሳቸው መሆኑን አስታውቀው በማከልም ኮሚቴውን የማዋቀር ሥራ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም በሆኑት አል ጣይብ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአቡ ዳቢ ልዑል በሆኑት በሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን የታገዘ ቢሆንም ለአንድ ዓመት ሥራውን ያለ ማንም ተጽዕኖ ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል። የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ፣ መሐመድ አብደል ሳላም በንግግራቸው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ መልካም ውጤቶችን ማስገኘት የሚችለው የመንግሥታት እና የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ውሳኔ ሰጭ አካላት፣ እንዲሁም የብዙሃን መገናኛዎች እገዛ ሲታከልበት ነው ብለዋል። ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ የተለያዩ ዜግነት እና የእምነት ባሕል ላላቸውን ስደተኛ ቤተሰቦች ያደረጉት መልካም አቀባበል የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በተግባር ለመለወጥ ቀዳሚ ምሳሌ ሆኖ መገኘቱን መሐመድ አብደል ሳላም መስክረዋል።
የሰው ልጅ ወንድማማችነት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፣
ከኮሚቴው አባላት አንዱ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ላዚ ጋይድ በንግግራቸው እንዳስታወቁት የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በተግባር ለመግለጽ የወጣቶች ሚና ሰፊ መሆኑን አስረድተዋል። ሰነዱ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ ጋይድ ይህም የሆነበት የሚያምኑት በሙሉ መሠረታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ስላደረጉ ነው ብለው የሰውን ልጆች በሙሉ በፍቅር እና በወንድማማችነት መንገድ የሚመራው እግዚአብሔር ነው ብለዋል። በመሆኑም የሁሉም እምነቶች ተከታዮች በእግዚአብሔር ስም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች ናቸው ብለዋል። ልዩ ልዩ እምነቶችን የሚከተሉ ወጣቶች እርስ በእርስ በመተጋገዝ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ ሰላም እና ወንድማማችነት እንዲያድግ በማድረግ፣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድን በተግባር ለመግለጽ የሚችሉት ተሳትፎአቸውን ሲያሳድጉ ነው ብለዋል።
ዓለም ጠባብ ናት፣
በግብጽ የአል አዛር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሁሴን ማራሳዊ በበኩላቸው ባሰሙት ንግግር የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድን በአቡ ዳቢ ከተማ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ. ም. ፈርመው ያጸደቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በግብጽ የአል አዛር ታላቁ መስጊድ ኢማም የሆኑት አህመድ አል ጣይብ የመጡት ከአውሮፓ እና ከአፍሪካ፣ ሰነዱ የተፈረመውም በእስያ አህጉር መሆኑን አስታውሰው፣ ተራርቀን የምንኖር ቢመስለንም ዓለም ጠባብ መሆኗን አስረድተዋል። የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ወቅቱን የጠበቀ ነው ያሉት ፕሮፌሰር መሐመድ ሁሴን ማራሳዊ፣ ምክንያቱን ሲገልጹ የዓለም ሕዝቦች በሰላም እና በወንድማማችነት መንፈስ በመቀራረብ አብረው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ሃስብ እና ምክር ስለሚሰጥ ነው ብለዋል። ፕሮፌሰር መሐመድ ሁሴን ማራሳዊ በማከልም በግብጽ የሚገኘው የአል አዛር ዩኒቨርሲቲ፣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለተማሪዎች እያቀረበ መሆኑን ገልጸው፣ ዘርፉን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተጨማሪ ድጋፎችም የሚደረግለት መሆኑን አስረድተዋል።
የመሠረታዊ ሥነ ምግባር ሰነድ፣
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዳይሬክተር የነበሩ እና አሁን የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ አስፈጻሚ ከፍተኛ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኢሪና ቦኮቫ በበኩላቸው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰንዱ እንደ ዘመናችን መሠረታዊ ሥነ ምግባር ሰነድ ሆኖ መቅረቡ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተው፣ ይህን ሰነድ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለሚያቀርባቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ ያገኝበታል ብለዋል። ከዚህም ከዚህ በተጨማሪ ሰነዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተግባራዊ ለማድረግ ካቀዳቸው የዘላቂ የልማት ግቦች መካከል አራተኛ ከሆነው የትምህርት ግብ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አስረድተዋል።
ከግል አስተሳሰብ ወደ ጋራ አስተሳሰብ መመለስ፣
በዋሽንግተን በሚገኝ የአይሁድ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ መምህር የሆኑት ብሩስ ላስቲግ በበኩላቸው፣ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ መላው ዓለም ባሁኑ ጊዜ እጅግ በመፈለግ ላይ የሚገኘው እና የዓለማችን የሐይማኖት ተቋማት በአንድነት እንዲጓዙ የሚያሳስብ ሃሳብ ያካተተ መሆኑን ገልጸው፣ እኛ ሁላችን በአንድ ቤት ውስጥ የምንኖር የአንድ ቤተሰብ አባል ነን ብለዋል። በመሆኑም እያንዳንዳችን አንዱ የሌላውን ክብር በመጠበቅ ረገድ ሃላፊነት የሚሰማን ሊሆን ይገባል ብለዋል። ክቡር ብሩስ ላስቲግ በማከልም ሰነዱ ከግለኝነት አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ጋራ አስተሳሰብ እንዳናዘነብል ያሳስበናል ብለዋል።
ወደ አቡ ዳቢ ልዑል ዘንድ የሚደረግ ጉብኝት፣
የሰብዓዊ ወንድማማችነት ምክር ቤት ከፍተኛ ኮሚቴ አባላት ትናንት ጥር 25/2012 ዓ. ም. በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአቡ ዳቢ ልዑል የሆኑትን ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያንን በጎበኟቸው ጊዜ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን በበኩላቸ ከፍተኛ ኮሚቴ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እና ተግባራት የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠውላቸውል። ልኡል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ኣል ናያን በማከልም ኮሚቴው በማበርከት ላይ ያለው ተግባር ለመጭው ትውልድ እጅግ ጠቃሚ መሆኑንም አስታውቀዋል።