ለአፍሪካ አህጉር እውቅና እና ክብር ሊሰጠው ይገባል ተባለ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ቀን ግንቦት 17 ዕለት እንዲከበር እ. አ. አ ግንቦት 25/1963 ዓ. ም ከ32 ነጻ የአፍሪካ መንግሥታት መካከል የ30 አገራት መሪዎች በኢትዮጵያ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል። ዓላማውም በአገራቱ መካከል ያለውን ሕብረት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ታስቦ የተደረገ መሆኑ ይታወሳል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ. አ. አ ከ 2009 ዓ. ም ጀምሮ የአፍሪካ ኅብረት በሚል ስያሜ የሚጠራ መሆኑ ይታወሳል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ አገራት በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት እና የኤኮኖሚ አቅምን በማሳደግ ከዓለም አቀፍ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ለመወዳደር የሚያስችል አቅምን ለማግኘት እና አንዳንድ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ እንዲያስችላቸው ታልሞ የተመሠረተ መሆኑ ይታወሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት መርህን፣ ሰላምን፣ ጸጥታን፣ ሰብዓዊ መብትን ለማረጋገጥ መሆኑ ይታወሳል። ባሁኑ ጊዜ በዚህ ሕብረት ውስጥ የሚገኙ የአፍሪካ መንግሥታት ቁጥር 54 መድረሱ ታውቋል።
እምቅ ሃብት ቢኖረውም የኢኮኖሚ ድቀት ያለበት አህጉር
የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ዘንድር የተከበረውን የጴንጠቆስጤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክታቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰው ሕይወት ላይ እያስከተለ ባለው ጥፋት መጨነቃቸውን ገልጸው፣ በአህጉርቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት እና የምግብ እጥረት መኖሩን ገልጸው ምዕመናን የቸርነት እጃቸውን እንዲዘረጉ እና በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በአፍሪካ አህጉር ላይ ሰፊ ጥናቶችን ሲያካሂዱ የቆዩት አባ ጁሊዮ አልባኔዘ፣ አህጉሩ በተፈጥሮ ሃብት እጅግ ሃብታም፣ በርካታ ባሕላዊ እሴቶች ያሉበት እና እድገትን ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን “ሎዜርቫቶረ ሮማኖ” ለተባለ የቅድስት መንበር ጋዜጣ አብራርተውተዋል።
በአፍሪካ አህጉር ውስጥ በሶማሊያ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፣ በናይጄሪያ እና በቅርቡም በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሚታዩ ግጭቶችን የጠቀሱት ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ፣ በአፍሪካ ውስጥ ግጭቶች የሚታዩባቸው አካባቢዎች ዝርዝር ረጅም መሆኑን ገልጸው እስላማዊ አሸባሪዎችም አንዳንድ ክፍተቶችን በማግኘት ወደ አህጉሩ እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪቃ ሕብረት ሲዋቀር የአህጉሩ ሕልም ብዙ የነበር ቢሆንም ተግባራዊ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ጥቂት እንደሆነ ያስታወሱት ክቡር አባ ጁሊዮ ከሕብረቱ መመስረት ወዲህ የተደረጉት ጥረቶች በጣም ዝቅተኛ ለውጦችን ማምጣታቸውን ገልጸዋል። በእያንዳንዱ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባትን ሳይቀበል የቆየው የአፍሪካ ሕብረት ዛሬ በአንድ አገር ውስጥ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ቢካሄድ ውና ጽሕፈት ቤቱ በሚገኝበት በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ በመሰብሰብ ያንን አገር ከሕብረቱ የማስናበት እርምጃን የሚወስድ መሆኑን ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ ገልጸዋል።