ስደተኞች በፓናማዋ ባጆ ቺክቶ መንደር አቅራቢያ ባለ ጫካ አቋርጠው ሲጓዙ ስደተኞች በፓናማዋ ባጆ ቺክቶ መንደር አቅራቢያ ባለ ጫካ አቋርጠው ሲጓዙ  (AFP or licensors)

ግጭቶች፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ዙሪያ ሰዎችን እያፈናቀሉ ይገኛሉ ተባለ

የተለያዩ በርካታ ምክንያቶች በብዙ የዓለማችን ክፍሎች ማለትም በአፍሪካ፣ አሜሪካ እና እስያ ከፍተኛ የስደተኞች ፍልሰትን እየፈጠሩ ይገኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እንደ አፍሪካ፣ አሜሪካ እና እስያ በመሳሰሉ በርካታ የዓለማችን ክፍሎች በሚከሰቱ የተለያዩ ምክንያቶች በርካታ የስደተኞች ፍልሰት ቁጥርን እየፈጠሩ እንደሆነ ተነግሯል። ከነዚህም ውስጥ ግጭቶች፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ዙሪያ ሰዎችን ከቀያቸው ከሚያፈናቅሉ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው።

ሜዲትራኒያንን መሻገር

በአውሮፓ ውስጥ ያለው የስደት ተጽእኖ ፥ ወደ አውሮፓ ህብረት ሃገራት የሚደረግ የሜዲትራኒያን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ማዕከል በሆነችው ላምፔዱዛ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ይገኛል። ባለፈው ሳምንት ከአፍሪካ የመጡ ወደ 7,000 የሚጠጉ ስደተኞች በዚህ አከባቢ በሚገኝ የባህር ዳርቻ ላይ መታየታቸው ተዘግቧል።
በቱኒዚያ እና በማልታ መካከል የምትገኘው የጣሊያን ደሴት በዚህ ዓመት የመጡ ሰዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ የጨመረ ሲሆን ፥ ከ 2013 ዓ.ም. ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በሶስት እጥፍ መጨመሩ ተነግሯል። የስደተኞቹ መሸጋገሪያዎች በአደጋ የተሞሉ ናቸው። በዚህ ዓመት ብቻ ወደ 2,000 የሚጠጉ ስደተኞች በባህር ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።
በስደተኞች ላይ ከተከሰቱት አስከፊ አደጋዎች አንዱ የሆነው በግሪክ የባህር ዳርቻ ላይ ስደተኞቹን ጭና የነበረቿ ጀልባ ተገልብጣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ጦርነትን ለመሸሽ ወደ ሁሉም አህጉራት መሰደድ 

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ያደረገችውን ወረራ ተከትሎ ብዛት ያላቸው ዩክሬን ስደተኞች ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት መሰደድ ጀምረዋል። በአፍሪካም በርካታ የስደተኞች ቀውስ እንደቀጠለ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ምክንያቶች እና በሰሜናዊው የአፍሪካ ቀንድ ክፍል በተነሳው የትጥቅ ግጭት ምክንያት ሰዎች መሰደዳቸውን ወይም መፈናቀላቸውን ቀጥለዋል። በሱዳን ከ 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ በተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ100,000 በላይ ሰዎች ሀገሪቱን ለቀው ወጥተዋል።

ከእስያ እስከ ደቡብ አሜሪካ ያለው እውነታ

በእስያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮሂንጊያዎች ከምያንማር ለቀው ተሰደዋል ፥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መርከቦች የአንዳማን ባህርን እና የቤንጋል ባህረ ሰላጤን ለማቋረጥ ሞክረዋል።
በሜክሲኮም እንደዚሁ አብዛኛዎቹ ከደቡብ አሜሪካ የሆኑ ስደተኞች ወደ ሰሜን ረጅም እና አድካሚ ጉዞ በሚያደርጉ ስደተኞች መብዛት ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
 

25 September 2023, 15:14