የፋይል ፎቶ -FILES-AGRICULTURE-FOOD-UN-SUMMIT የፋይል ፎቶ -FILES-AGRICULTURE-FOOD-UN-SUMMIT  (AFP or licensors)

በኮፕ28 ስብሰባ ዘላቂነት ያለው ግብርና ለአየር ንብረት ለውጥ ጥሩ መከላከያ እንደሆነ ተገለፀ

በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ኅብረት (AFSA) የፕሮግራሞች አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ብሪጄት ሙጋቤ በዱባይ የአየር ንብረት ድርድር ላይ የአፍሪካ ትናንሽ የባህላዊ ግብርና አምራቾችን ድምፅ ለማሰማት ስለሚሰራው ስራ ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ በማድረግ አብራርተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ ግብርና ነው። ሞቃታማ ወቅቶች፣ የዝናብ እጥረቶች፣ ተደጋጋሚ እና ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በብዙ አገሮች የግብርና ምርት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሲሆን ይህም በተለይም በደቡቡ ንፍቀ ዓለም የምግብን ዋጋ ተለዋዋጭ በማድረግ እንዲሁም በምግብ ዋስትና ላይ ትልቅ ተፅእኖ አሳድረዋል ተብሏል። ይህ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ 17 በመቶ የሚሆነውን ለግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት አስተዋፅኦ በማበርከት የችግሩ አካል እንደሆነም ተገልጿል።  

ግብርናን ከአየር ንብረት እርምጃ ጋር ማቀናጀት

እ.አ.አ. ከ2011 ጀምሮ የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ኅብረት የትናንሽ ገበሬዎችን እና እረኞችን ፣ አዳኞችን እና የሃገሬው ተወላጆችን የሚወክሉ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ተዋናዮችን እንዲሁም የሃይማኖት ድርጅቶችን እና ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎችን በመሰብሰብ በአህጉሪቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ባህላዊ ዘላቂነት ያለው ግብርና የሚተገበርባቸው መንገዶች ላይ ሲመክር ቆይቷል።

ይህ ተቋም ከአራት ዓመታት በፊት ግብርናውን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የማዋሃድ ዘመቻ እንደጀመረ ተገልጿል። የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ኅብረት ፕሮግራሞች አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ብሪጄት ሙጋቤ የአፍሪካን አነስተኛ ባህላዊ አምራቾች ድምጽ በአየር ንብረት ድርድር ላይ ለማሰማት በዱባይ እየተካሄደ ባለው የኮፕ28 ስብሰባ ላይ ከተሳተፉት በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ልዑካን መካከል አንዱ ናቸው።

በምግብ ራስን የመቻል ወሳኝ ጉዳይ

አስተባባሪዋ በጉባዔው ወቅት ስለነበረው የቅስቀሳ ሥራ ከቫቲካን ዜና ባልደረባ ማሪን ሄንሪዮት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፥ “ይህ ጉባኤ ግብርናን በኮፕ28 የመጨረሻ ሰነድ ውስጥ መካተቱን ለማረጋገጥ የእኛን አጀንዳዎች አፅንዖት ሰጥተን ለማንሳት ከምንሳተፍባቸው ክስተቶች ውስጥ አንዱ ነው” ሲሉ ወይዘሮ ብሪጄት ሙጋቤ አብራርተዋል። በማከልም “ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የምግብ ሉዓላዊነት እና የምግብ ምርትን እንዲሁም ከአየር ንብረት እርምጃዎች ጋር የተያያዙ የገበያ ሁኔታዎችን የመሳሰሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ከፖሊሲ አውጪዎቻችን ጋር ለመፍታት የሚያስችል ቦታ ነው ብለዋል። ዓላማውም በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች ድምጽ ማሰማት እንደሆነ ጨምረው አስረድተዋል።

የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ኅብረት ከኮፕ28 ጉባኤ ጎን ለጎን በርካታ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት መግለጫዎችን እንዳወጣ እና የአየር ንብረት እርምጃ ለግብርናው ዘርፍ ያለውን ወሳኝ ጠቀሜታ እና ዘላቂ የሆነ ግብርና በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለውን ድርሻ ለማጉላት እና የተደራዳሪዎችን ትኩረት ለመሳብ ከበርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በመገናኘት እንደተወያየ ተገልጿል።

ወይዘሮ ብሪጄት ሙጋቤ በመላው አፍሪካ የሲቪል ማህበረሰብ እና የሃይማኖት ተዋናዮችን ማሳተፍ እና ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል። ይሁን እንጂ የአፍሪካ ተሟጋቾች ጥምረት በድርድሩ ውጤት ላይ የተወሰነ ተጽእኖ ማሳደር ይችል እንደሆነ እርግጠኛ እንዳልሆኑም ገልፀዋል።
 

06 December 2023, 14:05