በእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን ደቡብ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል በእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ፍልስጤማውያን ደቡብ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል   (ANSA)

የጋዛ ጦርነት በጤና አጠባበቅ ላይ 'አስከፊ ተጽእኖ' እያሳደረ እንደሚገኝ ተነገረ

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ እንደተናገሩት በጋዛ እየተደረገ ያለው ጦርነት በአከባቢው በሚገኝ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ላይ አስከፊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ገብረኢየሱስ እንደገለፁት የጤና ባለሙያዎች በአከባቢው እየተደረገ ባለው ጦርነት ምክንያት በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው እየሰሩ እንደሆነ በመግለፅ፥ ጦርነቱ እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር ሲቪሎች የደቡባዊ ጋዛ ዋና ከተማ የሆነችውን ካን ዩኒስ ከተማን ለቀው እንዲወጡ አዟል። የእስራኤል ጦር መሪም ሃማስን ለማሸነፍ ወታደሮቻቸው የበለጠ ግፊት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ይህ ሁሉ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በእስራኤል እየደረሰ ባለው ጥቃት ምክንያት ግማሽ ያህሉ የጋዛ ዜጎች በረሃብ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ እና አብዛኞቹ ሰዎች በየቀኑ መብላት እንደማይችሉ አስጠንቅቋል።

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ቅዳሜ እለት አሜሪካ በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔን ውድቅ ካደረገች በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ የጦር ወንጀሎች ተባባሪ ናት ሲሉ ከሰዋታል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃላፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው የፀጥታው ምክር ቤት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ባለመቻሉ መፀፀታቸውን በመግለፅ፥ ድርጅቱ ሽባ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ ቀውስ የጀመረው በመስከረም ወር የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ የሃማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ድንበር ጥሰው በመግባት 1,200 ሰዎችን በመግደል በርካታ ሴቶችን እና ህጻናትን ጨምሮ 240 የሚሆኑ ሰዎችን አግተው በመውሰዳቸው እንደሆነ ይታወቃል።

ሃማስ እንደገለፀው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በአጸፋ ዘመቻው ከ17,000 በላይ ሰዎችን ገድላለች ብሏል።
 

11 December 2023, 15:21