በእስራኤል ጥቃት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በካሃን ዮኒስ በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት በሚተዳደር ትምህርት ቤት ተጠልለው በእስራኤል ጥቃት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በካሃን ዮኒስ በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት በሚተዳደር ትምህርት ቤት ተጠልለው 

እስራኤል በሃማስ ላይ የምታካሂደውን ጦርነት በማስፋት ወደ ደቡብ ጋዛ እየተንቀሳቀሰች ነው ተባለ

የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ በሁሉም የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎች የምድር ዘመቻውን እያስፋፋ እንደሆነ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የእስራኤል ጦር አዛዥ እንደገለፁት በሰሜናዊ ጋዛ የተካሄደው የሰራዊቱ የምድር ጥቃት ዓላማዎች ከሞላ ጎደል የተሳኩ በመሆናቸው፥ አሁን ላይ ጦሩ ወደ ደቡብ በማቅናት ኦፕሬሽን ጀምሯል ብለዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የተጀመረው ጦርነት እነሆ ዛሬ ኀዳር 26/2016 ዓ.ም. ሁለተኛ ወሩን የደፈነ ሲሆን፣ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር አስታውቃለች።

እስራኤል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከደቡብ ጋዛ ወደ ሰሜን እንዲንቀሳቀሱ ትእዛዝ ሰጥታለች። የእስራኤል መንግስት ቃል አቀባይ ግን እስራኤል ህዝቡን ከጋዛ በዘላቂነት ለማባረር እየሞከረች መሆኑን አስተባብለዋል። ይህንንም በማስመልከት በአከባቢው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን የሆኑት ጄምስ ኤልደር ፍልስጤማውያን የሚሄዱበት ቦታ አጥተው ነበር በማለት ስለችግሩ አሳሳቢነት ተናግረዋል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ደጋግመው ቢናገሩም ወታደሮቿ ሲቪሎችን መጠበቅ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እያካሄደች ያለውን ጥቃት ተከትሎ በመጨረሻ በጦር ወንጀለኛነት ለፍርድ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል። እንደሚታወቀው ቱርክዬ ከአብዛኞቹ የምዕራባውያን አጋሮቿ በተለየ ሃማስን እንደ አሸባሪ እንደማትመለከት በአንዳንድ አቋሞቿ ይፋ እያደረገች መጥታለች።

በኳታር አደራዳሪነት ሁለቱ ኃይሎች ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ተስማምተው ስምምነቱ ለሰባት ቀናት ተፈጻሚ ሆኖ በቆየበት ወቅት የበርካታ እስረኞች እና ታጋቾች ልውውጥ ቢደርግም አሁንም እስራኤል ሙሉ በሙሉ ታጋቾቿን አስለቅቃ አልጨረሰችም።

በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሃማስ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት 1,200 ሰዎችን ሲገድል፥ ሌሎች 240 የሚጠጉትን ደግሞ አግቶ እንደነበር ይታወሳል። በሃማስ የሚመራው የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ ዘመቻ ከ15,500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
 

06 December 2023, 14:26