የእስራኤልን የአየር ጥቃት ተከትሎ በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ሰማይ ላይ የሚታይ ጭስ - ከደቡብ እስራኤል እንደታየው የእስራኤልን የአየር ጥቃት ተከትሎ በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ሰማይ ላይ የሚታይ ጭስ - ከደቡብ እስራኤል እንደታየው 

ተጨማሪ እርዳታ ከግብፅ ወደ ጋዛ እየገባ እንደሆነ ተነገረ

የሐማስ መሪ ድርጅታቸው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን ሊያመጣ በሚችል በማንኛውም ተነሳሽነት ከእስራኤል ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ኢስማኤል ሃኒዬ የተባሉት የሐማስ መሪ አንጃቸው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን ሊያመጣ በሚችል በማንኛውም ተነሳሽነት ከእስራኤል ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

መሪው በጋዛ እየደረሰ ያለውን የቦምብ ጥቃት ሊያስቆም የሚችል ማንኛውንም ዝግጅት ወይም ተነሳሽነት ላይ ለመወያየት ዝግጁ ነኝ ማለታቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ኢስማኤል ሃኒዬ በአረብኛ የዜና ማሰራጫ አውታሮች ባደረጉት ንግግር ሃማስ ያልተሳተፈበት ማንኛውም የጋዛን የወደፊት ሁኔታ በተመለከተ የሚዘጋጅ ዝግጅት ሊሳካ እንደማይችል ተናግረዋል ። ሃኒዬ በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ የሚጠይቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔን በደስታ መቀበላቸውንም ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በርካታ የሃማስ ተዋጊዎች በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል እጃቸውን ሰጥተው እንደነበር ገልፃለች።

ሰብአዊ እርዳታ እና ነዳጅ

በሌላ ዜና ግብፅ በየቀኑ ወደ ጋዛ ሰርጥ የሚላከውን የነዳጅ መጠን ከ129,000 ወደ 189,000 ሊትር እንደሚጨምር ተናግራለች። ከጥቅምት 10/2016 ዓ.ም. ጀምሮ 4,057 የሰብአዊ እርዳታ መኪኖች ከግብፅ ተነስተው በራፋ ማቋረጫ በኩል ወደ ክልሉ መግባታቸውም ተነግሯል።

እነዚህ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች የህክምና አቅርቦቶች፣ ምግብ፣ ውሃ፣ እንዲሁም 2,678 ቶን ነዳጅ፣ 48 አምቡላንሶች እና ድንኳኖችን እንደሚያጠቃልል ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በብሪታንያ የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ፍልስጤማውያን ‘ከእስራኤል አጠገብ አገር እንዲኖራቸው ፈጽሞ አልፈለጉም’ በማለት በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል እንዲካሄድ የተነሳውን የሁለትዮሽ ውይይት ሃሳብ ውድቅ አድርገዋል።
 

15 December 2023, 15:21