የተፈናቀለች ፍልስጤማዊት ሴት ከሃን ዩኒስ ውስጥ ከልጆቿ ጋር በእሳት ዙሪያ ተቀምጣ የተፈናቀለች ፍልስጤማዊት ሴት ከሃን ዩኒስ ውስጥ ከልጆቿ ጋር በእሳት ዙሪያ ተቀምጣ 

ሴቭ ዘ ችልድረን 'በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሌለበት በእያንዳንዷ ሰዓት ህፃናት ይሞታሉ' አለ

በእስራኤል መንግስት እና በሃማስ መካከል የተደረገውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረስ ተከትሎ በካን ዩኒስ ከተማ የእስራኤል ምድር ጦር ወታደራዊ ዘመቻ በመጀመሩ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ህጻናት፥ ምናልባትም አጠቃላይ ህጻናትን ማለት ይቻላል፥ ጋዛ ውስጥ ለመሸሽ ምንም አይነት ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ሳይኖር አከባቢውን ለቀው እንደወጡ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የዓለም መሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጫና በመፍጠር ማረጋገጥ አለባቸው። ምክንያቱም ስምምነቱ ከሌለ በእያንዳንዷ ሰዓት ብዙ ልጆች ለዚህ ለተበላሸ ፖለቲካ ምክንያት ውድ ህይወታቸውን እና ራዕያቸውን በማጣት ዋጋ ይከፍላሉ ። ስምምነቱ እስካልተደረገ ድረስ በጋዛ ምንም ዓይነት አስተማማኝ ቦታ አይኖርም” ያሉት በእስራኤል ቁጥጥር ሥር ያለው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ የሚገኘው የህፃናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ጄሰን ሊ ናቸው።

እስራኤል በሃማስ ላይ የጀመረው ጥቃት ያለማቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፥ አሁን ደግሞ ደቡባዊ የጋዛ ሰርጥ ላይ ትኩረቱን አድርጎ እያጠቃ እንደሆነም ተነግሯል። 

ጄሰን ሊ በተፋላሚዎቹ ወገኖች መካከል የተደረገው ለአንድ ሳምንት የቆየው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረስን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ “የእኔ የሥራ ቦታ ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ለማግኘት ሲሉ መከራቸውን እያዩ ያሉበት ደቡባዊ ጋዛ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ በጋዛ ውስጥ የሚሸሽበት ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ የለም” በማለት ተናግረዋል።

“የእስራኤል ባለስልጣናት በአከባቢው ላይ ያሉትን ቤተሰቦች ያለ ምንም ደህንነት እና የመመለሻ ዋስትና ሳይሰጡ በግዳጅ ወደ ትናንሽ አካባቢዎች እንዲፈናቀሉ እና አስፈላጊው መሠረተ ልማት እና ህይወትን የሚደግፉ አገልግሎቶችን ሳያገኙ በእስራኤል ባለስልጣናት ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

አቶ ጄሰን ሊ በማስከተልም እንደተናገሩት በጋዛ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው እና ከዚህ ቀደም ሲቪሉ ህዝብ በእስራኤል ወታደሮች ለደህንነት ሲባል እንዲሸሹበት ወደተደረገችውና አሁን ግን በእስራኤል ጦር ጥቃት እየተፈፀመባት ያለችው ካን ዮኒስ የእስራኤል የምድር ጦር ወታደራዊ ዘመቻ ሲጀምር፥ ህፃናቱ በሙሉ ደህንነታቸው የተጠበቀ የሚሄዱበት ምንም ዓይነት ቦታ ሳይኖራቸው አከባቢውን ለቀው ወጥተዋል” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ በሰሜናዊ ጋዛ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ደህንነታቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ታጉረው እንደሚገኙ እንዲሁም እንደ ሆስፒታሎች እና የንፅህና አጠባበቅ ያሉ ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች ባልተሟሉበት ሁኔታ፥ ለረሃብ፣ ለበሽታ፣ ለጉዳት እና ለሞት አደጋ ተጋልጠው እንደሚገኙ ተነግሯል።

ጦርነቱ ከጀመረበት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከ16,500 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በጋዛ ተገድለዋል፥ ብዙዎቹ ደግሞ በእስራኤል ቦምቦች ተመተው በፈራረሱት ህንፃዎች ፍርስራሽ ስር ጠፍተዋል ወይም ሳይሞቱ አይቀሩም ተብሎ ተፈርቷል።
 

07 December 2023, 13:25