በጋዛ የሚገኘው 'ሆሊ ፋሚሊ' የሚባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጋዛ የሚገኘው 'ሆሊ ፋሚሊ' የሚባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 

የእስራኤል ጦር ጋዛ በሚገኘው ‘ሆሊ ፋሚሊ’ ደብር ላይ ባደረሰው ጥቃት ሁለት ሴቶች ተገድለዋል ተባለ

የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ጋዛ በሚገኘው የሆሊ ፋሚሊ ካቶሊካዊ ሰበካ ግቢ ውስጥ በመግባት ከቤተክርስቲያኑ በሚወጣ በማንኛውም ሰው ላይ ሲተኩስ እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን፥ ሰለባዎቹም አዛውንት እናቷን ለማዳን ከህንጻው በፍጥነት ስትወጣ የነበረች ሴት እና አዛውንት እናቷ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። እስራኤል በደብሩ ውስጥ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ መኖሩን በመግለጽ ጥቃቱ ትክክል እንደሆነ በመግለጽ አስተባብላለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እስራኤላውያን በጋዛ ክርስቲያኖች ላይ ተኩስ እንደከፈቱ እና በጋዛ ከተማ በሚገኘው የላቲን ሥርዓት ተከታይ በሆነችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የሆሊ ፋሚሊ ደብር አካባቢ ሌሊት ላይ ከባድ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ እንደዘገበው በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን ለረጅም ሰዓታት የእስራኤላውያኑ አልሞ ተኳሾች ተኩስ ቀጥሎ እንደነበር ዘገባዎች አሳይተዋል።

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ ቤተክርስቲያን የተለቀቀው መግለጫ እንዳረጋገጠው ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአብዛኛው ክርስቲያን የሆኑ ቤተሰቦች በተጠለሉበት የሆሊ ፋሚሊ ሰበካ ውስጥ አንድ እስራኤላዊ አልሞ ተኳሽ ሁለት ክርስቲያን ሴቶችን መግደሉን አረጋግጧል።

በጭካኔ ተገለዋል

ሟቾቹ ናሂዳ እና ልጇ ሰማር ወደ ሲስተሮች መኖሪያ እየሄዱ እያለ በጭካኔ በጥይት ተመተው እንደተገደሉ የተገለፀ ሲሆን፥ “አንደኛዋ በጥይት ተመታ የተገደለችው እናቷን ለማዳን እየሞከረች ባለበት ሰዓት ነው” ሲል መግለጫው ገልጿል።

በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉትን ለመጠበቅ ሲሞክሩ ተጨማሪ ሰባት ሰዎች በጥይት ተመተው ቆስለዋል ተብሏል። የመንበረ ፓትርያርኩ መግለጫ “ምንም ማስጠንቀቂያ ሆነ ማሳሰቢያ እንዳልተሰጠ እና፤ በሰበካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት የታጠቀ ሰው በሌለበት ሁኔታ ሁለቱ ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በጥይት ተመትተዋል” ብሏል።

በ ‘ሚሽነሪስ ኦፍ ቻሪቲ’ ገዳም ላይ የደረሰው ጥቃት

መግለጫው በተጨማሪም ጠዋት ላይ ከእስራኤል መከላከያ ሃይል ታንክ የተተኮሰው ሮኬት የእማሆይ ተሬዛ እህቶች ገዳም ላይ ኢላማ በማድረግ እና በመምታቱ ብቸኛው የመብራት ምንጭ የሆነውን የሕንፃውን ጀነሬተር ማውደሙን እንደዚሁም ከፍተኛ የእሳት አደጋም በማስነሳት በቤቱ ላይ ጉዳት ማድረሱን መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው በመቀጠል “ገዳሙ ከ54 በላይ አካል ጉዳተኞች የሚገኙበት ሲሆን፥ ከጦርነቱ መጀመሪያ ጀምሮ የአምልኮ ስፍራ ሆኖ ሲገለጽ የነበረው የቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ አካል ነው” ብሏል።

በመቀጠልም ለአካል ጉዳተኞች መጠለያ እንዲሆን የተደረገው ሕንፃው ላይ ኢላማ በማድረግ ሁለት ተጨማሪ ሮኬቶች በተከታታይ በመተኮሱ ምክንያት “54ቱ አካል ጉዳተኞች በአሁኑ ጊዜ ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ በመግለጽ፥ አንዳንዶቹም በሕይወት ለመትረፍ የሚያስፈልጋቸውን የመተንፈሻ መሣሪያ አያገኙም” ይላል መግለጫው።

በአካባቢው ከባድ የቦምብ ጥቃት ደርሷል

በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሌሊት በደረሰ ጥቃት ሌሎች ሶስት ሰዎች እንደቆሰሉ፣ ለህብረተሰቡ ህልውና አስፈላጊ የሆኑት የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፓኔሎች እና የውሃ ጋኖችም እንደወደሙ ተነግሯል።

የእስራኤል መንግስት የሮኬት ማስወንጨፊያ የቤተክርስቲያኑ ሰበካ ውስጥ መኖሩን በመግለጽ እየተካሄደ ያለው ጥቃት ትክክል እንደሆነ ገልጿል። መንበረ ፓትርያርኩ በጉዳዩ ጣልቃ ቢገባም ኦፕሬሽኑ ቶሎ እንዳልቆመ እና የእስራኤል ወታደሮች ወደ ሰበካው ግቢ እና በህንፃው ውስጥ ወደተጠለሉት ሲቪሎች መተኮሳቸው ተዘግቧል።

ትርጉም የለሽ አሳዛኝ ክስተት

የእየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት ተከታይ ቤተክርስቲያን “በዚህ ትርጉም የለሽ አደጋ ለተጎዱ ቤተሰቦች” ያለውን ቅርበት እና የተሰማትን ሀዘን በመግለጽ፥ ከመላው የክርስቲያን ማህበረሰብ ጋር በጸሎት እንደሚሆን እና በተመሳሳይ ጊዜ “መላው ቤተክርስቲያን ለገና በዓል እየተዝጋጀ እያለ እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ” ግንዛቤ እንደሌለው ገልጿል።
 

18 December 2023, 15:15