የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች ከጋዛ ሰርጥ ድንበር አጠገብ ሰፍረዋል የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች ከጋዛ ሰርጥ ድንበር አጠገብ ሰፍረዋል  (AFP or licensors)

የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ 100 ቀናትን እንዳስቆጠረ ተነገረ

እስራኤል እ.አ.አ. በ 1948 እንደ ሃገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ካካሄደቻቸው ጦርነቶች ረጅም፣ ደም አፋሳሽ እና አውዳሚ የተባለው የእስራኤል ሃማስ ጦርነት ምንም የመቆም ተስፋ ሳይታይበት ባለፈው ጥር 5 ቀን 2016 ዓ.ም. 100ኛ ቀኑን መያዙ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሃማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ደቡባዊ እስራኤል ሳይጠበቅ ገብቶ ጥቃት በመፈፀም በአብዛኛው ሲቪል የሆኑ 1,300 ሰዎችን ከገደለ እና 240 የሚሆኑ እስራኤላውያንንና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም መቋጫ እንዳላገኘ ተዘግቧል።

2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሰርጡ ነዋሪዎችን ቢያንስ ለአንድ ጊዜ እንዲፈናቀሉ፤ ከግማሽ በላዩ የጋዛ ሆስፒታል ስራ እንዲያቆምና ረሃብ እንዲስፋፋ ያደረገው ጦርነት ያደረሰው ውድመት ከፍተኛ ነው።

እስራኤል በእነዚህ መቶ ቀናቶች ውስጥ በአየር እና በምድር ጦሮቿ ያካሄደቻቸው ጥቃቶች በርካታ የሰው ልጅ ህይወትን የቀጠፈ እና ብዙ ውድመቶች ያደረሰ፥ ብሎም ክልላዊ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ጫና ያደረሰ ቢሆንም የሃገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የጋዛ ሰርጥን ለመያዝ እና ለመቆጣጠር እንደማትፈልግ ተናግረዋል።

በሃማስ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስከባለፈው ቅዳሜ ድረስ በግጭቱ ከ23,300 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል።

ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች መሆኑን እንድታውጅ እና ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምታቀርብ ያነሳሳት እነዚህ ከፍተኛ የሰው ጉዳት የሚያሳዩ ቁጥሮች እንደሆኑም ተገልጿል።

በጋዛ የጀመረው ጦርነት አድማሱን በማስፋት ወደ ቤሩት እና ሰንአ ተሻግሯል፤ ወላፈኑ ደማስቆ እና ባግዳድንም ነካክቷል፥ አልፎም የመን እና ቀይ ባህር ላይ የደረሰ ሲሆን፥ በአከባቢው የሚገኙ የሃውቲ አማፂያን በንግድ መርከቦች ላይ ተከታታይ አደገኛ ጥቃቶችን እንዲፈፅሙም መነሻ መሆኑ ተነግሯል። በዚህም የሃውቲ ታጣቂዎች ይሄንን ጥቃት የሚያካሂዱት እስራኤል በሃማስ ላይ ለጀመረችው ጦርነት ምላሽ ነው ሲሉ አጥብቀው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።

ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ ብሪታንያ እና አሜሪካ በቀጠናው በሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦች ላይ የሚደርሱትን ጥቃቶች ለመቀነስ በሚል የሃውቲ ታጣቂዎች ይገኙባቸዋል ባሉት ሥፍራዎች የተቀናጀ ድብደባዎችን እያደረጉ እንደሚገኝም ተነግሯል።

ለእስራኤል ድጋፏን ያሳየችው አሜሪካ፤ ሃማስን የምታግዘው ኢራን እና ሌሎች ሀገራትም 100ኛ ቀኑን የያዘው ጦርነት ከመቆም ይልቅ አድማሱን እንዲያሰፋ ያበረታቱ ይመስላል ተብሏል።

መስከረም 26 ሃማስ በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃት በኋላ፣ የእስራኤል ጎረቤት በሆነችው ሊባኖስ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት እና በኢራን የሚደገፉት የሂዝቦላህ ተዋጊዎች እስራኤልን ማጥቃት በመጀመራቸው ምክንያት የእስራኤልን የአጸፋ ጥቃት ማስከተሉንም ዘገባዎች ያሳያሉ።
 

16 January 2024, 12:43