ፍልስጤማውያን በራፋ ውስጥ የምግብ አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ የዕርዳታ ምግብ ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ፍልስጤማውያን በራፋ ውስጥ የምግብ አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ የዕርዳታ ምግብ ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ 

የተ.መ. ኤጀንሲዎች ወደ ጋዛ የነፍስ አድን ዕርዳታን ለማድረስ ከአሁኑ የተሻለ መንገድ እንዲኖር ጠየቁ

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ረድኤት ኤጀንሲዎች የተጎዱትን ለመርዳት ብሎም ረሃብን እና በሽታን ለመከላከል የአደጋ ጊዜ መድሃኒት እና ምግብ ወደሚፈልጉት የጋዛ ህዝብ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል ተጨማሪ መንገዶች እንዲከፈቱ ተማጽነዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ኃላፊዎች፣ ዩኒሴፍ እና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ በመሆን ጋዛ ውስጥ ላሉ ሰዎች እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን እና መድኃኒቶችን ለማድረስ እንዲቻል ወደ ጋዛ የሚወስዱ መንገዶችን ከአሁኑ በበለጠ ሁኔታ ክፍት ማድረግ እንደሚገባ ተማጽነዋል።

አሁን ያሉት የመግቢያ መንገዶች እና ገደቦች የቆሰሉትን፣ የታመሙትን እና የተራቡትን ለመርዳት አነስተኛውን አቅርቦት እንኳን ለማድረስ ብቁ ስላልሆኑ መዘግየቶችን እያደረሱ እንደሆነም አመላክተዋል።

የሰብአዊ ኤጀንሲዎቹ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋራ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ “ደህንነቱ የተጠበቀ የእርዳታ አቅርቦት እና ተጨማሪ የአቅርቦት መስመሮች” አስፈላጊነትን፥ እንዲሁም በጋዛ ረሃብን እና ገዳይ በሽታን ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቷል።

የተመጣጠነ ምግብ እጦት መስፋፋቱን እና “በተለይ በሰሜናዊ አካባቢዎች የምግብ፣ የንጹህ ውሃ እና የህክምና ዕርዳታ እጥረት ከባድ መሆኑን” እንዲሁም “ለችግረኞች አገልግሎት መስጫ ቦታዎችን ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በቦምብ ድብደባ እና በየጊዜው በሚቀያየር የጦር ግንባሮች እንዴት እንደሚደናቀፍ” አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። 

መግለጫው በጋዛ 335,000 የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ለሕይወት አስጊ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው ካለ በኋላ፥ በጦርነቱ መሠረተ ልማቶች በመውደማቸው ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ምግብ ማምረት ባለመቻሉ በውጭ ዕርዳታ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ለመሆን እንደተገደዱም ያብራራል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እና አጋሮች በጋዛ ውስጥ ያለውን የጤና ስርዓት፣ የሕክምና መሳሪያዎች እና ቁሳቁሶች፣ መድሃኒቶች፣ ነዳጅ እና የድንገተኛ ህክምና ቡድኖችን በማስተባበር ለመርዳት ሞክረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች “ይህን እጅግ በጣም አስፈላጊ እና በርካታ ኤጀንሲዎችን ያቀፈ ሰብአዊ ተግባር እንዲጀመር ለማስቻል ሰብአዊ የተኩስ አቁም” ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።

የዓለም ጤና ድርጅት ቃል አቀባይ የሆኑት ታሪክ ጃሻሬቪች በጋዛ ስላለው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እና እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑት አስቸኳይ የዕርዳታ አቅርቦቶችን አስመልክተው ከቫቲካን ዜና ጋር ቆይታ አድርገዋል እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ጥያቄ፦ አሁን በጋዛ ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ ሊነግሩን ይችላሉ?

መልስ፦ ሁኔታው ለጋዛ ህዝብ አስከፊ ነው። ወደ ጤና አገልግሎት ስንመጣ የጤና አገልግሎት እየቀነሰ ሲሄድ እናያለን፥ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው በርካታ ሰዎች እነዚህ የጤና አገልግሎቶች የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ስለዚህ የቦምብ ጥቃቱ በቀጠለ ቁጥር የቁስለኞች እና የሚሞቱ ሰዎችም እየበዙ ይሄዳሉ። እስካሁን ድረስ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ 24,000 በላይ ሆኗል፥ ከነዚህም ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት ናቸው፥ ይሄም አሃዝ በአጠቃላይ ሲታይ 1% በላይ የጋዛ ህዝብን ይወክላል።

አሁን የተጎዱት በሆስፒታል ውስጥ መታከም አለባቸው፥ ነገር ግን በጋዛ ውስጥ ከ 36 ሆስፒታሎች ውስጥ 15 ቱ ብቻ በከፊል የሚሰሩ ናቸው፥ እናም በእውነቱ ከዚህ በፊት ከነበሩት የጤና ባለሙያዎች መሃከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው እየታገሉ ያሉት።

በነዳጅ፣ በመብራት፣ በንፁህ ውሃ፣ በሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ጋር እየታገሉ ይገኛሉ፥ ብዙ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሰላማዊ ዜጎችም ሆስፒታሎች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ አይዘነጋም። ስለዚህ እነዚህን ሆስፒታሎች ለማየት ስንሄድ ባልደረባዎቻችን ምንም አይነት የምግብ አቅርቦት ሳይኖራቸው ወለል ላይ ተኝተው ህክምና ስለሚጠባበቁ ሰዎች ሲነግሩን ከፍተኛ የሆነ ሃዘን ተሰምቶናል፥ አሁን የሚወራው ስለቆሰሉ ሰዎች ብቻ ነው፥ ነገር ግን ከዚህ በላይ በጋዛ ውስጥ 50,000 ነፍሰ ጡር እናቶች አሉን፣ ከ 300,000 በላይ ሥር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ሰዎች፣ የኩላሊት እጥበት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች፣ ካንሰር፣ የስኳር በሽታ፣ የደም ግፊት እና ሌሎች በሽታዎች የሚሰቃዩ ህመምተኞች አሉን። እነዚህ ሁሉ የጤና አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ስለሌሉ እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን የጤና አገልግሎት ማግኘት አይችሉም።

ከዚህ ሁሉ በላይ ሰዎች ወደ ትናንሽ የጋዛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲሰደዱ በሚገደዱበት ጊዜ ለተላላፊ በሽታ መስፋፋት ይጋለጣሉ። 90% የጋዛ ህዝብ ቤታቸውን ለቀው መውጣት ነበረባቸው። አሁን ደግሞ የንፅህና መጠበቂያ፣ የመጸዳጃ ቤት፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦት በሌላቸው እና የሙቀት መጠኑ አነስተኛ በሆነባቸው ትናንሽ ቦታዎች ላይ እየኖሩ ይገኛሉ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ ቫይረሶች ይሰራጫሉ።

በንፁህ ውሃ እጦት የተቅማጥ በሽታ እንደተከሰተ እየተነገረን ነው። በንፁህ ውሃ እጦት ምክንያት የቆዳ በሽታ እየተስፋፋ እንደሆነ እየተነገረን ነው። በንጽህና መጠበቂያ እጦት ምክንያት የተለያዩ በሽታዎች እንደተከሰቱ ተነግሮናል። ስለዚህ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ነው ያለው፥ በቂ ተደራሽነት ስለሌለን የጤና ስርዓቶችን ተግባራዊነት ለመጠበቅ እየታገልን ነው።

እኛ በእውነት የምንፈልገው ሁሉንም ለመድረስ ነው። ተጨማሪ የዕርዳታ አቅርቦቶች እንዲገቡ እንፈልጋለን። ወደ ጋዛ ተጨማሪ የመግቢያ መስመሮች እንዲኖሩ እንፈልጋለን። በጋዛ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ለመስራት የበለጠ ደህንነት እንፈልጋለን። የደህንነት ዋስትናዎች እንፈልጋለን። ወደ ጋዛ ሊገቡ በሚችሉ የዕርዳታ ቁሶች እና በእርዳታ ሰራተኞች እንቅስቃሴ ላይ አነስተኛ ገደብ እንዲኖር እንፈልጋለን።

በእርግጥም በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባቀረባችሁት ጥሪ ላይ ይህን አንስተዋል...

አዎ፣ በመግለጫው ልክ እንደዚህ ነበር ያልነው፥ አሁን ባለው ተደራሽነት ወደ አስከፊ የረሃብ ሁኔታ፣ ወደ ገዳይ የረሃብ እና የበሽታ ክስተት እየሮጥን ነው። ስለዚህ የጋዛን ህዝብን ለመድረስ ተጨማሪ መንገዶችን መፈለግ አለብን።

ሆኖም ግን በመጨረሻ ብቸኛው እና ትክክለኛ መፍትሄው አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ነው፥ ምክንያቱም በጋዛ ላይ የቦምብ ናዳ እስከቀጠለ ድረስ የተጎዱ ሰዎች ይኖራሉ፥ ብዙ ሰዎችም ይሞታሉ።

ጥያቄ፦ ህይወትን ለማዳን መደረግ ይገባሉ ለሚሉት ነገሮች የጊዜ ገደብዎ ምን ያህል አስቸኳይ ነው ብለው ያስባሉ?

መልስ፦ ወዲያውኑ መፈፀም አለበት፥ ምክንያቱም በጋዛ በየቀኑ ሰዎች እየሞቱ፣ ሕፃናት እና ሴቶች እየተገደሉ ነው። ይህ መቆም አለበት። ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊኖር ይገባል። በጋዛ ውስጥ የንጹሃንን ሞት ለማቆም እና ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ እንዲሁም እኛ እና ሌሎች አጋሮች በጋዛ ውስጥ ያሉትን የጤና አገልግሎቶች ተግባራዊነት ለማረጋገጥ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ ወደሚፈለጉበት ቦታዎች ለመድረስ እና መፍትሄ ለመፈለግ ከሁሉም ሰው በቂ ግፊት ሊኖር ይገባል።

ጥያቄ፦ ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን የምናየው በዋነኛነት የአማካይ ጊዜ እና የረዥም ጊዜ መፍትሄዎች ላይ የተኮሩ ናቸው፥ ነገር ግን የእርስዎ አስቸኳይ የሰብአዊ ዕርዳታ መልእክትዎ እየተሰማ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶችን አይተዋል?

መልስ፦ ደህና፥ እኛ እንደ ሰብአዊነት ማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን፥ እያደረግን ያለነው የተቸገሩትን ለመደገፍ እና ያየነውን ለመግለጽ መሞከር ነው። ከእስራኤል የተወሰዱ ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ስንጠይቅ ከጅምሩ ጀምሮ እያደረግን ያለነው ይህንኑ እንደሆነ ነው። ያኔ በጋዛ ያለው ሰብአዊ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተን ልንጠነቀቅበት የሚገባ ጉዳይ ነበር፥ እና በእውነቱ በስቃይ ውስጥ ካሉት ጎን ልንሆን ይገባናል እናም አሁን በችግር ውስጥ ያለው የጋዛ ህዝብ እንደሆነ ግልፅ ነው።

ጥያቄ፦ ከአደጋው መጠን አንፃር ማነፃፀር እንደሚከብድ አውቃለሁ፥ ነገር ግን በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ አይተው ያውቃሉ?

መልስ፦ አንተ እንዳልከው ድንገተኛ ሁኔታዎችን ማነፃፀር በጣም ከባድ ነው፥ እናም የሰው ስቃይ በዬትኛውም ስፍራ ይከሰት የት ያው የሰው ስቃይ ነው። ግን በእውነቱ በጋዛ የተከሰተው የመሰረተ ልማት ውድመት፣ የግድያው መጠን፣ ከአጠቃላይ ጋዛ ህዝብ ብዛት አንድ ከመቶ የሚሆነው ህዝብ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ መገደሉን ስታስበው አእምሮን የሚረብሽ ነገር ነው።
 

18 January 2024, 14:22