ጋውንዳል የሚገኘው የሴቶች ማሰልጠኛ ማዕከል ጋውንዳል የሚገኘው የሴቶች ማሰልጠኛ ማዕከል 

ካሜሩን ውስጥ ድህነትን እና ሴተኛ አዳሪነትን በመዋጋት ላይ ያሉ የካቶሊክ ገዳማዊያን

የካሜሩን ከተማ በሆነችው ጋኦውንዳል የሚገኙ የቅድስት ጃኔ አንቲዳ ቱሬት መነኮሳት የሴቶች ማሰልጠኛ ማዕከልን እና ሁለት ክሊኒኮችን የሚመሩ ሲሆን፥ ማዕከሎችን የሚያስተዳድሩት ሲስተር ክላውዲን ቦሉም እንደገለጹት “ወደ እዚህ መጥተን ይሄንን ሥራ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በሴቶች ህይወት ላይ መሻሻሎች ታይተዋል” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ያለዕድሜ ጋብቻን ሆነ የጎዳና ላይ ሕይወት ሸሽተው፥ ማዕከላዊ ካሜሩን የሆነው በአዳማውዋ ክልል ውስጥ በሚገኘው ጋኦውንዳል ከተማ ወዳለው የሴቶች ማሰልጠኛ ማዕከል የሚመጡ ልጃገረዶች በሙሉ ማለት ይቻላል፥ ከባድ የህይወት ጎዳና ውስጥ እንደነበሩ እና ያንን ሸሽተው እንደመጡ ይታወቃል።

እ.አ.አ. ከ1987 ጀምሮ በአፍሪካ ሀገር መስራት የጀመሩት የቅድስት ጃን አንቲዳ ቱሬት ‘ሲስተርስ ኦፍ ቻሪቲ’ ገዳማዊያን ፕሮጀክቱን ያቋቋሙት በ12 ዓመታቸው በወላጆቻቸው ግፊት ወይም በአከባቢው ተጽዕኖ ጋብቻ ውስጥ ገብተው፥ መጨረሻቸውም በሴተኛ አዳሪነት ሥራ ውስጥ የገቡትን ወጣት ልጃገረዶች ለመደገፍ ነው።

“ነገር ግን” ይላሉ ሲስተር ክላውዲን፥ “ሴቶቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ከተደረጉ በኋላ ወደዚህ ሥራ ተመልሰው አይገቡም” ብለዋል። በካሜሩን ለአራት ዓመታት የቆዩት የቻድ ተወላጅ የሆኑት መነኩሲት አክለውም እንደተናገሩት “ትምህርት ቤቱ እንደ አዲስ ማሰብ የሚጀምሩትን የእነዚህን ልጃገረዶች ዓይን ይከፍታል” በማለት ገልጸዋል።

የአርብቶ አደር ቡድኖች

መነኮሳቱ ባቋቋሙት ማእከል ውስጥ፣ ከፎልቤ ወይም ቦሮሮ ብሄረሰብ የመጡ የአርብቶ አደር ልጆች የሆኑ ሙስሊም ልጃገረዶች ይገኛሉ። ሲስተር ክላውዲን ይህንን በማስመልከት እንደተናገሩት “እነዚህ ሰዎች ኑርዋቸውን እና ሥራቸውን ከምንም በላይ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ከእንሣት ጋር ያደረጉ አርብቶ አደሮች ናቸው፥ በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ ሴቶች ዋጋ አይሰጣቸውም፥ ወንዶች ከአንድ በላይ ሚስት አላቸው፥ ሆኖም ምንም ስራ የላቸውም፥ ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸውን እንኳን መመገብ አይችሉም” ብለዋል።

ሲስተር ክላውዲን በመቀጠል፥ “ባለፉት ዓመታት መነኮሳቱ ቤተሰቡን ለመርዳት ጥረት አድርገዋል፤ አንዳንድ ማሻሻያዎችም ታይተዋል” ካሉ በኋላ፥ “አሁን ሴቶቹ ሥራ መሥራት ይፈልጋሉ፤ ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ተረድተው ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጀምረዋል” ብለዋል።

እነዚህ ወጣት ሴቶች በማዕከሉ ውስጥ የልብስ ቅድ እና ስፌት ትምህርት ይማራሉ፥ ይህ ብቻ ሳይሆን የሂሳብ አያያዝ፣ እንዲሁም በስልጠናቸው መጨረሻ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ሀሳባቸውን መግለጽ ይችላሉ።

ኢና እና ናድያ

ወደ ማዕከሉ ገብተው ከሚማሩ ደፋር ወጣት ሴቶች መካከል እንደ ምሳሌ የምትታየው፥ ባለትዳር የሆነችው ኢና ስትሆን፥ ከቤት ወጥታ ሥራ መስራት እንድትችል ወደ ማዕከሉ ትምህርት ለመማር ወስና ገብታለች። ይህ ከባሏ እና ከወላጆቿ ፍቃድ ውጭ የማይሞከር ነበር።

ሌላኛዋ ደግሞ ናዲያ ስትሆን የእሷ ታሪክ የተለየ ነው። ከትምህርት ቤቱ በጣም ርቆ ከሚገኘው ጋውንዴሬ ከተማ ነው የመጣችው። ሲስተር ክላውዲን እንዳሉት “ወላጆቿ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ሊልኳት አቅም ስለሌላቸው፥ ስለ እኛ ሰምታ ነበርና የልብስ ስፌት ለመማር ለመመዝገብ ወሰነች፥ አንዴ ትምህርቷን ከጨረሰች፥ ወደ ቤቷ ተመልሳ የራሷን ትንሽ ሱቅ በመክፈት ህልሟን ማሳካት ትችላለች፥ ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው አንድ ሰው የልብስ ስፌት ማሽን ቢሰጣት ብቻ ነው ፤ ይህንንም የሲስተርስ ኦፍ ቻሪቲ መነኮሳት በጣም ድሃ ከሆኑ ቤተሰቦች ለመጡ ወጣት ሴቶች የሚያደርጉት ነገር ነው።

የጠንቋዮች ተግዳሮት

በዚሁ አካባቢ የቅድስት ጄን አንቲዳ ቱሬት እህቶች ‘ፔትሮ ፒኮራ’ እና ‘ሳንታ አጎስቲና’ የተባሉ በነርሶች የተደራጁ ሁለት የተመላላሽ ታካሚ ክሊኒኮችን አቋቁመዋል። ከፍተኛ ደረጃ ያልደረሰ የወባ በሽታ ህክምና የሚሰጠውም እዚሁ ነው።

በተጨማሪም ለህጻናት ክትባቶች እና እርጉዝ እናቶችም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል። ሲስተር ክላውዲን ስለነዚህ ክሊንኮች ሲናገሩ፥ “የነዚህ ሁለት ክሊኒኮች መከፈት ምክንያት ብዙዎቹ በዘመናዊ ሕክምና ስለማያምኑ ነው።

ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊት ‘በባህላዊ መድኃኒት’ ወደሚያክሟቸው ጠንቋዮች ይሄዳሉ። ታማሚው የሞት አደጋ ላይ መሆኑን ሲገነዘቡ ብቻ ከመንደሩ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ሆስፒታል ይወስዷቸዋል። በዚህ ምክንያት የሁለቱ ክሊኒኮች መገኘት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ረድቷዋል። ወባ፣ ታይፎይድ፣ ሳንባ ነቀርሳ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አብዛኞቹ ታማሚዎች የሚሰቃዩበት በሽታ ሲሆን፥ አብዝኞቹም ትናንሽ ህጻናት ናቸው። “ህፃናቱ ጥሬ ወተት ብቻ ነው የሚጠጡት” ያሉት ሲስተር ክላውዲን፥ “በቲቢ በሽታ ይያዛሉ፥ እናም እራሳቸውን በበቂ ሁኔታ መመገብ አይችሉም” ብለዋል።

የመድሃኒቶች ጥያቄ

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ እና ነርስ የሆኑት ኔስቶር ሳዶሊ እንደተናገሩት “እዚህ በፒትሮ ፔኮራ ውስጥ የክትባት መርሃ ግብር አለን፥ ከቅድመ ወሊድ ሕክምና እና ከወሊድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንሰራለን፥ የምርመራ ላቦራቶሪዎች አሉን፥ በተጨማሪም በመንደሩ የወባ በሽታ ስላለ ክትባቶችን እንሰጣለን፥ ተቅማጥ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ታይፎይድ፣ ትኩሳት እንዲሁም ለአረጋውያን የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ ህክምና ይሰጣል” ብለዋል።

በጣም አሳሳቢ ከሆኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመድኃኒት አቅርቦት እንደሆነም በአጽንዖት ይናገራሉ።

ሲስተር ኔስቶር ይሄን በማስመልከት ሲናገሩ “መድሃኒቶች እንደልብ ሊገኙ አይችሉም፥ ግን ቢያንስ እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ካሉ በኋላ፥ “በአውሮፓ የሚገኙ አቅራቢዎች አሉን፤ የውጭ ኩባንያዎች ሆነው እዚህ የሚያመርቱም አሉ። እኛ ትዕዛዞችን እንሰጣቸዋለን፥ መድሃኒቶቹን ከሳምንት በኋላ ያደርሱልናል፣ ግን ሁሉንም ነገር ወዲያውኑ ለመክፈል በጭራሽ አንችልም፥ ማድረግ የምንችለው ከታካሚዎች የተወሰነ ገንዘብ ከሰበሰብን በኋላ ነው፥ ከዚህ በስተቀር ታካሚዎቹን የምናስከፍለው ነገር ዬለም” ብለዋል።

የሕንድ ቡድን ሚና

የውሃ ጉድጓድ፣ የስልጠና ማዕከል፣ ሁለት ክሊኒኮች እና የመድሃኒት ግዢ በገዳማዊያኑ ቢደረጉም፥ ባለፉት ዓመታት ብዙ ተስፋዎችን ቢሰጧቸውም ከግዛቱ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው ይናገራሉ።

ይህንን አስመልክተው ሲስተር ክላውዲን ሲያብራሩ “የተለያዩ ቁሳቁሶች፣ ለት/ቤቱ የሚሆኑ የልብስ ስፌት ማሽኖች፥ ይህ ሁሉ የሚመጣው “ግሩፖ ኢንዲያን” ከተባለ እና ማሪዮ ፔሴ በሚባል ጄሱሳዊ የተቋቋመ የእርዳታ ድርጅት ለሴት ልጆች የተሻለ ሕይወት እንድንሰጥ በሚረዳን ዓመታዊ ስጦታ ነው።

ስለዚህ ምንም እንኳን ይህ የህንድ ቡድን ከእኛ በጣም ርቆ የሚገኝ ቢሆንም በየቀኑ በልባችን ውስጥ አለ፥ በየቀኑም እነዚህ ልጃገረዶች ለሚቀበሉት ነገር ይጸልያሉ” ብለዋል።
 

15 February 2024, 13:13