የሃይማኖት መሪዎች በቶኪዮ በተካሄደው ጉባኤ ሰላምን ለማስፈን ጠንክረው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ዓለምን እያሽመደመዱ ባሉት ጦርነቶች መካከል፣ ዓለም አቀፉ እና የጃፓኑ ሃይማኖቶች ለሰላም ተቋማት ከተባበሩት መንግሥታት የሥልጣኔዎች ጥምረት ጋር በመተባበር የብዝሃ ሃይማኖቶች የሰላም ጥረት ጉባኤን አዘጋጅተዋል። (‘ሃይማኖቶች ለሰላም’ የዓለምን ሰላም ለማስፈን የተሠማሩ የዓለም ሃይማኖቶች ተወካዮች የተውጣጡበት በ1962 ዓ.ም. የተመሠረተ ዓለም አቀፍ ጥምረት ነው)
ከየካቲት 11-13 2016 ዓ.ም. ድረስ በቶኪዮ በተካሄደው በሁለተኛው ዙር “ከጦርነት ባሻገር እና ወደ እርቅ ጉዞ፡ የሀይማኖቶች ተቋማት የሰላም ድርድር” በሚል መሪ ቃል፥ ተቋማቱ ከ15 በግጭት የተጎዱ ሀገራት፥ አምስት ሀይማኖቶችን የሚወክሉ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት እና የእምነት መሪዎችን ሰብስበው ያላቸውን ዕውቀት ለመለዋወጥ እንዲሁም ሰላምን እና እርቅን ለማስፈን፥ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ሂደቶች እና ተነሳሽነቶች ላይ ተወያይተዋል።
በ 2014 ዓ.ም. ለሶስት ቀናት የተካሄደው የመጀመሪያው ዙር የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ላይ ተሳታፊዎች ስለ ሃይማኖታዊ እና እምነት ተዋናዮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ አካላት እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሰው ህይወት እና ክብር እንዲጠበቅ ያላቸው ሚና አስፈላጊነት ላይ ተወያይተዋል።
የብዝሃ ሀይማኖቶች የሰላም ውይይት ወሳኝ ነው
የዚህ የሁለተኛው ዙር የቶኪዮ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የሰላም ጉባኤ በማጠቃለያው “በጸሎት መትጋት እንደሚያስፈልግ እና ለሕይወት ቅድስና እና ለሰው ልጅ ክብር መሠረት የሆነውን ደህንነትን የሚጋራው የሰላም ባህልን በሃይማኖቶች ውስጥ ለማስፈን ጠንክሮ ለመስራት” ቃል የገቡበት መግለጫ በማውጣት ነበር ያጠናቀቁት።
በመግለጫው ውስጥ በሄይቲ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ማይናማር እና ዩክሬን ጨምሮ በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ ባሉ ሃገራት ሰዎች እየደረሰባቸው ላለው “የማይታሰብ ስቃይ” ጥልቅ ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በግጭት ቀጠና ውስጥ ያሉ በጣም ተጋላጭ ሰዎች
ተሳታፊዎቹ እንደገለጹት “የሰላምና የፀጥታ መሠረቶች በሁሉም የዓለም ክፍሎች አደጋ ላይ መሆናቸውን እንገነዘባለን” ሲሉ ከወቀሱ በኋላ፥ በማከልም “ከሁሉም በላይ በጣም ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች፣ ህጻናት እና የተገለሉ ህዝቦች በከባድ ጥቃት፣ መፈናቀል እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተሰቃዩ ይገኛሉ” ብለዋል።
የሃይማኖት መሪዎቹ በመቀጠል፥ “በየሃይማኖታችን እና በእምነታችን መለኮታዊ አስተምህሮ በመነሳሳት፥ በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ባሉ የሰላም ራዕያችን እና የጋራ ሀላፊነታችን እንደ አገናኝ ድልድይ እና ሰላም ፈጣሪ በመሆን በማገልገል፥ እንዲሁም በጦርነት ለተጎዳው ማህበረሰባችን እርቅ እና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እንጥራለን” ብለዋል።
ከዚህም በላይ ፈራሚዎቹ “የሕይወትን ቅድስና እና ሰብአዊ ክብርን የማስከበር የተቀደሰ መርህ መጣሱን በመገንዘብ” ጦርነትን እና ሁከትን አጥብቀው አውግዘዋል።
ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች
የኃይማኖት ተቋማቱ የሰላም ራዕያቸውን በተሻለ መንገድ ለማሳካት፥ የእምነት መሪዎች ተከታታይ የሆነ የጋራ ተግባራትን ዘርግተዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ ‘ማንም ሰው ወደኋላ እንዳይቀር’ ተባብረው መሥራትን፣ ከባድ ጥቃትን፣ መፈናቀልን እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመፍታት የጋራ እርምጃን በሚያበረታታ መልኩ በጋራ መሥራትን ይጨምራል።
በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ሃብቶቻቸውን እና ማህበረሰቦቻቸውን በማሰባሰብ በጦርነት ለተጎዱ ማህበረሰቦች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እና በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ እና ድጋፍን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የሃይማኖት መሪዎቹ ከጉዳቱ ለማገገም እና እርቅን ለማግኘት ዘላቂ የሆኑ ዕቅዶች ላይ ቁርጠኛ እንደሆኑ በመግለፅ፥ ‘ጦርነት እና ሁከት እንዳይደገም እና እንዳይቀጥል’፥ በግጭቶች እና በጦርነት በተጎዱ እና በተለያዩ ቤተሰቦች እና ማህበረሰቦች መካከል አንድነት እና መረጋጋትን ለማበረታታት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ተወካዮቹ ከማጠቃለላቸው በፊት “መተማመንን ለመፍጠር፣ መለያየትን ለመፈወስ እና ለበለጠ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ሁሉን አቀፍ ማህበረሰቦች ይቅርታና ሰላም ለመፍጠር” በሚል መሪ ቃል የሀይማኖቶች የሰላም የድርድር መድረክ መጥራታቸውን ገልፀው፥ “በመካሄድ ላይ ባሉ ጦርነቶች እና ብጥብጦች ለሚሰቃዩ ሁሉ ልባዊ ጸሎታቸውን እና የማይናወጥ አጋርነታቸውን አቅርበዋል።
ተጠያቂነት 2 ቢሊየን ለሚሆኑ የዓለም ህፃናት
አዲስ የተሾሙት ‘የኃይማኖቶች ለሰላም’ ዋና ጸሃፊ ዶ/ር ፍራንሲስ ኩሪያ ካገማ የሃይማኖት መሪዎችን ድምጽ አንድ ላይ ማሰባሰብ አስቸጋሪዎቹን ግጭቶችን እና ጦርነቶችን ለመፍታት አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
ይህ በንዲህ እንዳለ፣ የኬልቄዶን ሜትሮፖሊታን እና ‘የኃይማኖቶች ለሰላም’ ተባባሪ አወያይ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኢማኑኤል አዳማኪስ በበኩላቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላምን ለማስፈን ለረዥም ጊዜ የእርቅ ግቦች ቁርጠኞች መሆናቸው ምን ያህል ‘አስፈላጊ’ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የህንዱ ሻንቲ አሽራም ተቋም ፕሬዝዳንት እና ‘የኃይማኖቶች ለሰላም’ ተባባሪ አወያይ የሆኑት ዶ/ር ቪኑ አራም በተመሳሳይ በሰጡት አተያየት ሴቶችን እና ህጻናትን በጥረቶቻቸው ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ በመግለጽ፥ በጃፓን ዋና ከተማ ተሰብስበው የተሻለች ዓለም እንዲኖረን ጥረት የሚያረጉትን ሁሉ “ሁለት ቢሊዮን ለሚሆኑ የዓለም ህፃናት ተጠያቂነት አለብን” ብለዋል።
"ሁሉም ባለድርሻ አካላት የረጅም ጊዜ የእርቅ ግቦችን ለማሳካት በቁርጠኝነት መፈጸም እና የብዝሃ ኃይማኖቶች የሰላም ውይይት መቀጠል ሰላምን ለማስፈን ወሳኝ ነው"