የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ 55ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ 55ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ  (ANSA)

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሰብዓዊ መብቶች መከበር ለዓለም ሰላም መሠረታዊ ናቸው አሉ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዓለማችን ለሰው ልጆች የሚደረገው የደህንነት ጥበቃ ‘ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ መምጣቱን’ በማስጠንቀቅ፥ መንግስታት “በሰብአዊ መብት ላይ የተመሰረተ ሰላም እና ደህንነት” ላይ አጥብቀው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ሰኞ ዕለት በተከፈተበት ወቅት፥ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ‘በዓለም ላይ የህግ የበላይነት እና የጦርነት ህግጋት እየተጣሱ ዓለም ‘ከቀን ወደ ቀን ደኅንነቷ እየቀነሰ መምጣቱን’ አስጠንቅቀዋል።

ይህንንም በማስመልከት እንደተናገሩት “ከዩክሬን እስከ ሱዳን፣ ማይናማር፣ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ጋዛ ድረስ ግጭት የሚፈጥሩ አካላት ለዓለም አቀፍ ህግ፣ ለጄኔቫ ስምምነቶች እና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ሳይቀር ዓይናቸውን መግለጥ አቅቷቸዋል” ብለዋል ጉቴሬዝ።

ዋና ጸሃፊው በተለይም ሩስያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ እና እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገችው ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የጋራ አቋም አለመኖሩን ጠቁመዋል።

በምክር ቤቱ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶች “ምናልባትም ለሌሎች ሞት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል” በማስጠንቀቅ፥ ምክር ቤቱ “በአደረጃጀቱ እና በአሠራሩ ላይ ከባድ ማሻሻያ ያስፈልገዋል” ሲሉ አሳስበዋል።

የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ህጎች ግልጽ ናቸው

ጉቴሬዝ በጋዛ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ሁሉም ታጋቾች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ህጎች ግልፅ መሆናቸውን በመጥቀስ፥ “በአንዱ ወገን የሚፈፀመው ጥሰት ሌላውን ከተገዢነት አያድነውም” ብለዋል።

“በዓለም አቀፍ ሰብአዊነት እና የሰብአዊ መብት ህግጋት ላይ የሚፈጸሙ አስደንጋጭ እና ተደጋጋሚ ጥሰቶችን እያየን ዝም ማለት አንችልም” ካሉ በኋላ፥ አክለውም “የዓለም አቀፍ ህግን መጣስ የሰው ልጅ ደህንነትን ከማሳጣት ባሻገር የበለጠ ደም መፋሰስ ያስከትላል” ብለዋል።

የሰብአዊ መብቶችን ማስጠበቅ የእያንዳንዱን ሰው ደህንነት እንደሚያስጠብቅ የገለጹት ጉቴሬዝ፥ “ለሰላም እና ለደህንነት ሲባል፥ የሲቪል፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ በአፈፃፀም እና ተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ በአዲስ ሁኔታ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

በሰብአዊ መብት ላይ የተመሰረተ ሰላም እና ደህንነት

በመሆኑም መሰረታዊ የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካላት "የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል እና ሲፈጸሙም ለመለየት፣ ብሎም ምላሽ ለመስጠት በጋራ ሆነው በአንድነት እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስችል፥ ከሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመተባበር አዲስ የተባበሩት መንግስታት “የመከላከያ አጀንዳ” አስተዋውቀዋል።

በተመሳሳይም በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግስታት በሰብአዊ መብት ላይ የተመሰረተ ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ፥ መጪው ጉባኤ “ይሄንን በድጋሚ ቃል ለመግባት ጥሩ አጋጣሚ ነው” በማለት ጠቁመዋል።

በተለይም በጉባዔው ወቅት ለውይይት የሚቀርበው የሰላም አጀንዳ “ሁሉንም ዓይነት ጥቃት ለመከላከልና ለማስቆም የሰብአዊ መብት ህጎችን ተግባራዊ ያደርጋል” ተብሏል።

ሰብአዊ መብቶች ቋሚ ናቸው

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመጨረሻም፥ “ዓለማችን በአስደናቂ ፍጥነት እየተቀየረች ነው፥ የግጭቶች መበራከከት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስቃይ እያስከተለ ይገኛል፥ እነዚህ ሁሉ መፍትሄ ለመፈለግ ለምናደርገው ጥረት አንድነትን ይሰጡታል፥ ብሎም ሰላም የሰፈነበት ዓለም እንዲኖረን ለምናደርገው ተስፋ መሠረታዊ ናቸው” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።
 

28 February 2024, 13:09