ፍልስጤማዊው አሜሪካዊ ፕሮፌሰር መሐመድ አቡ ኒመር ፍልስጤማዊው አሜሪካዊ ፕሮፌሰር መሐመድ አቡ ኒመር 

ፕሮፌሰር መሐመድ አቡ ኒመር በሰላም ገንቢነታቸው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት አሸነፉ

የኒዋኖ የሰላም ፋውንዴሽን፥ ፍልስጤማዊው አሜሪካዊ ፕሮፌሰር መሐመድ አቡ-ኒመርን 41ኛው የ2024 (እ.አ.አ) የኒዋኖ የሰላም ሽልማት አሸናፊ አድርጎ መርጦአቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኒዋኖ የሰላም ፋውንዴሽን ማክሰኞ የካቲት 19/2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፥ ፍልስጤማዊው አሜሪካዊ ፕሮፌሰር መሐመድ አቡ ኒመር ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት ከአካዳሚያዊ ዕውቀታቸው በላይ እንደሆነ ገልጿል።

“በሥራቸው እጅግ የሚያስደንቀው፥ ለሰላም ያበረከቱት ሁለንተናዊ አስተዋፅዖ ነው” ሲል የገለጸው መግለጫው፥ ምሁሩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ትምህርትን ከግጭት አፈታት እና ከሰላም ግንባታ ተግባራት ጋር በማቀናጀት፥ በተለይም በእስልምና እምነት ውስጥ በይቅርታ እና በዕርቅ ላይ ባላቸው ጥልቅ ግንዛቤ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጋቸውን መግለጫው አክሏል።

የእስራኤልእና የሐማስ ጦርነት

መግለጫው፥ ፕሮፌሰር አቡ ኒመር በሕይወት ዘመናቸው ለሰላም እና ለሃይማኖቶች ውይይት ያሳዩትን ቁርጠኝነት በመገንዘብ፥ “በትውልድ አገራቸው እስራኤል እና ፍልስጤም መካከል እየተካሄደ ካለው ግጭት እና ቀጣናው እጅግ አውዳሚ ወደ ሆነው ጦርነት ከመሸጋገሩ ሁኔታ አንጻር ለዘንድሮው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት የበለጠ ተገቢ እና ብቁ የሆነ ሰው ሊገኝ አልቻለም” ብሏል መግለጫው።

የኒዋኖ የሰላም ፋውንዴሽን ዓለም አቀፋዊ አመለካከቱን ለመጠበቅ በሚያደርገው የማያቋርጥ ጥረት በዓለም ዙሪያ ምሁራዊ እና ሃይማኖታዊ እውቅና ካላቸው ግለሰቦች እጩዎችን ይመርጣል። ጥብቅ የምርጫው ሂደት ከተለያዩ ሃይማኖቶች እና አካዳሚያዊ ዳራዎች ከተመረጡ ተሿሚዎች እና ድርጅቶች የሚያገኛቸውን ግብዓቶች ያካትታል።

በሃይማኖቶች እና በባሕሎች መካከል የሚደረግ ውይይት

ኃላፊነት ያለባቸው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ኮሚቴ አባላት የዘንድሮውን አሸናፊ ለመምረጥ የሚከተሉትን የፕሮፌሰር አቡ ኒመር አስደናቂ አስተዋጾዎችን በዋቢነት አቅርቧል፡- የፕሮፌሰር አቡ ኒመር በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና የግጭት አፈታት ዘዴ ፕሮፌሰር በመሆን፥ በግጭት አፈታት፣ በአመጽ፣ በሰብዓዊ መብቶች እና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ለምርምር፣ ለትምህርት እና ለተግባር የቆመ “ሰላም” የተባለ ተቋም በመመሥረታቸው፤

በሃይማኖቶች እና በባሕሎች መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ላይ በንቃት በመሳተፋቸው፥ በሰላም ግንባታ እና በተለያዩ የግጭት አካባቢዎች በሚደረጉ ማኅበራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች በመሳተፋቸው እና ልዩነቶችን ለመፍታት ቁርጠኝነታቸውን በማሳየታቸው፤

የሱፊ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አቡ ኒመር፥ እንደ ሰሜን አየርላንድ፣ ስሪላንካ፣ በፊሊፒንስ-ሚንዳናኦ፣ በባልካን አገሮች እና በበርካታ የአፍሪካ የግጭት ቀጠናዎች ውስጥ በመሥራታቸው እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደርጉ ውይይቶችን ሲደግፉ በመቆየታቸው፤

ፕሮፌሰር አቡ ኒመር ከአካዳሚያዊ ዕውቀታቸው ባሻገር በሰላም ግንባታ ውስጥ ምሁራዊ ውይይቶችን ለማካሄድ የሚያግዝ መጽሔትን ለማዘጋጀት እና የሰላም ግንባታ እና ልማት ተቋማት ለመመሥረት ባሳዩት ተነሳሽነቶች መሆኑን የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ኮሚቴ በመግለጫው አስታውቋል።

መግለጫው በማጠቃለያው የፕሮፌሰር አቡ ኒመር ጥረት በብዙ ቦታዎች እና መስኮች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን እና እነዚህን መስኮች በመምራት፣ በማሰልጠን፣ በማመቻቸት እና በመገንባት እጅግ አስደናቂ ታሪክ ያለውን እና በእስልምና ወግ ላይ የተመሠረተ ሰላምን፣ መግባባትን እና ትብብርን ለማጎልበት የሠሩት ሥራ ለዚህ ክብር እንዳበቃቸው አስታውቋል።

የኒዋኖ የሰላም ሽልማት

ለኒኪዮ ኒዋኖ ክብር የተሰየመው የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ፋውንዴሽን ዓላማው በሃይማኖቶች መካከል በሚደረግ ትብብር እና በዓለም አቀፍ ሰላም ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ ለሚያበረክቱት እውቅናን ለመስጠት እና ለማበረታታት እንዲሁም ኒኪዮ ኒዋኖ በሀገሮች መካከል ግጭት ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች እና በማኅበረሰቦች መካከል ሰላም እና ስምምነት እንዲኖር የሚመኘውን እውን ለማድረግ ጥረት ያደርጋል።

የኒዋኖ የሰላም ሽልማት ሥነ-ሥርዓት ማክሰኞ ግንቦት 6/2016 ዓ. ም. በጃፓን ቶኪዮ ከተማ ሊካሄድ የታቀደ ሲሆን፥ ፕሮፌሰር አቡ ኒመር በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከሚሰጣቸው የምስክር ወረቀት በተጨማሪ የሜዳልያ እና የሃያ ሚሊዮን የን የገንዘብ ስጦታ እንደሚሸለሙ ታውቋል።

 

 

 

 

27 February 2024, 15:52