ከጋዛ የተነሱት ህፃናትና እና አስታማሚዎቻቸው ለህክምና ጣሊያን ገብተዋል ከጋዛ የተነሱት ህፃናትና እና አስታማሚዎቻቸው ለህክምና ጣሊያን ገብተዋል  

በጋዛ ጦርነት ምክንያት የታመሙ እና የቆሰሉ ህጻናት ለህክምና ጣሊያን መግባታቸው ተነገረ

በእስራኤል-ሀማስ ጦርነት ምክንያት በጋዛ ሰርጥ ስቃይ ውስጥ ካሉ በርካታ ህፃናት ውስጥ የተወሰኑ የታመሙ እና የቆሰሉ ህጻናት በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ከተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እና እንክብካቤ ለማግኘት ጣሊያን እንደገቡ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም ሊሆን የቻለው በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት በአባ ኢብራሂም ፋልታስ የግል ጥረት እና በጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በከባድ የቦምብ ድብደባ እና ውጊያ የተጎዱትን የመጀመሪያዎቹን 11 ህጻናት ከጋዛ ሰርጥ ልዩ በረራ በማድረግ ወደ ሮም ቺያምፒኖ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ሰኞ አመሻሹ ላይ ተጓጉዘዋል።

እነዚህ ህፃናት በጋዛ ቢቆዩ ኖሮ በቦታው ላይ የሚደረገው ሕክምና በጣም አነስተኛ ስለሆነ በህይወት የመቆየት እድላቸው ጠባብ እንደሆነም ተገልጿል።

ህፃናቱ መጀመሪያ ድንበር ተሻግረው ወደ ግብፅ ከገቡ በኋላ ከዚያ ተነስተው ወደ ጣሊያን በሚሄዱ አውሮፕላኖች እንደተሳፈሩ እና ከእነሱም ጋር ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ወጣት እንዳለም ተነግሯል።

እነዚህ ህጻናት በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የህፃናት ሆስፒታሎች ውስጥ የሚታከሙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ በቫቲካን የሚተዳደረው እና በሮም የሚገኘው የመጀመሪያውን አቀባበል እና ምደባን የሚያከናውነው ባምቢኖ ጌሱ ሆስፒታል አንዱ እንደሆነ ተገልጿል።

በተጨማሪም በጄኖዋ በሚገኘው ጋስሊኒ ሆስፒታል፣ ቦሎኛ የሚገኘው ሪዞሊ ሆስፒታል እና በፍሎረንስ ከተማ የሚገኘው ሜየር ሆስፒታል ህፃናቱ የሚታከሙባቸው ሆስፒታሎች እንደሆኑም ተመላክቷል።

ጣሊያን በጋዛ ጦርነት ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ዘመቻ በመክፈት የመጀመሪያዋ አውሮፓ አገር ነች።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል ያለው ትብብር

“በሚቀጥሉት ቀናት” ይላሉ ጄኔራል ፍራንቸስኮ ፓኦሎ ፊግሊዩሎ በተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች መካከል ስላለው ‘የተቀናጀ እንቅስቃሴ’ ሲናገሩ፥ “በአሁኑ ጊዜ በግብፅ የባህር ዳርቻ ላይ ቆማ የምትገኘው ‘ቮልካኖ’ ተብላ የምትጠራው እና የሆስፒታል አገልግሎት የምትሰጠው መርከብ ወደ ጣሊያን ጉዞ የምትጀምርበት ጊዜ ነው” ብለዋል።

ጥር 22 ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ታዳጊዎች በመርከብ ለመጓጓዝ ዝግጁ እንደሆኑ እና ከ4-5 ቀናት ውስጥ ልጆቹ በሚታከሙበት ቦታ ላይ በመመስረት ማዕከላዊ ወደሆነ ወደብ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሚቀጥለው ወር ላይ በአሁኑ ጊዜ በካይሮ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ህጻናትን የተለያዩ አውሮፕላኖች ወደ በርካታ የጣሊያን ሆስፒታሎች መውሰድ እንደሚጀምሩም ተገልጿል። ባለፈው ምሽት የፔሩጂያ ዩኒቨርሲቲ እና የሳን ማሪኖ ሆስፒታሎችም ለዚህ አገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

“የምንችለውን ሁሉ ወደ ሆስፒታሎች ለማድረስ እንጥራለን” ሲሉ ጀነራል ፍራንቺስኮ ፊልዩሎ አረጋግጠዋል።

የአባ ፋልታስ ተግባራት

የጋዛ ህፃናት ወደ ኢጣሊያ ሄደው አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያገኙ ያስቻለው ይህ ተነሳሽነት ከመጀመሪያ ጀምሮ በኢየሩሳሌም የሚገኙት የቅድስት አገር ተንከባካቢ ካህን የሆኑት የአባ ኢብራሂም ፋልታስ ያላሰለሰ ድጋፍ እንደነበረው በቅርቡ ላ’ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ከሚባለው የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰርጡ ውስጥ ከሚኖሩ ቤተሰቦች ጋር ስለሚሰሯቸው ሃዋሪያዊ ሥራ ባብራሩበት ወቅት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

አባ ፋልታስ በዚህ ቃለ ምልልስ ወቅት ለቆሰሉ ወይም ለታመሙ ህጻናት ምን ማድረግ እንደሚችሉ ሲጠየቁ “መጀመሪያ ከጣሊያን መንግስት መዋቅሮች ጋር በቅርበት በመገናኘት ጥያቄያችንን ያቀረብን ሲሆን፥ ወዲያውኑ ደስ የሚል ይሁንታን አግኝተናል” ብለው ነበር።

ባለፉት ዓመታት ለተቋቋመው ጥብቅ የግንኙነት መረብ ምስጋና ይግባውና አባ ፋልታስ ‘እስራኤላውያንን፣ ፍልስጤማውያንን እና ግብፃውያንን ያካተተ ጠንካራ የሽምግልና ሥራ’ ለመጀመር ችለዋል።

አባ ፋልታስ ትናንት አመሻሽ ላይ የበረራ ቁጥር 31 በሆነው የአየር ኃይል አውሮፕላን የተሳፈሩትን ሕፃናት በመጠባበቅ ላይ እያሉ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት “ይህ የመጀመሪያው የሰላም ምልክት ነው፥ መደማመጥና ትህትና የሚፈልግ ሰላም” ሲሉ ስሜታቸውን ገልፀዋል።

ፍራንቺስካዊያኑ ካህን ለጣሊያን ህዝብ ምስጋናቸውን በድጋሚ በመግለፅ፥ “ምክንያቱም ጣሊያን ምንም ህክምና ያልነበራቸውን ህፃናት ከጋዛ በመቀበል ከአውሮፓ የመጀመሪያዋ ሀገር በመሆኗ ነው፥ ጣሊያን ሁል ጊዜ ለዚህ ጉዳይ ቅርብ ነች፥ መጀመሪያ እኛ ጠየቅን ከዚያም ወዲያውኑ ጥያቄያችንን ተቀበሉ። ህፃናቱ ህክምናቸውን ጨርሰው ሲድኑ ወደ አገራቸው መመለስ ይችላሉ” ብለዋል።

አቶ ታጃኒ፡ ‘ይህ የገባነው ቃል ኪዳን ነው’

በቺያምፒኖ አየር ማረፊያ የተገኙት የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በበኩላቸው ለቫቲካን መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት “ከእስራኤል ባለስልጣናት፣ ከፍልስጤም ብሄራዊ ባለስልጣናት እና ከግብፅ ባለስልጣናት ጋር ጠንክረን ሰርተናል። ባለፈው ሐሙስ ድርድሩን እስራኤል ውስጥ አጠናቀናል። ይህ የገባነው ቃል ኪዳን ነው” ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም “ጣሊያን ሰለባ ለሆኑት ንፁሀን ያላትን አጋርነት መግለጿን ትቀጥላለች” ብለዋል።

በጣሊያን የፍልስጤም አምባሳደር የሆኑት አቢር ኦዴህ ለጥረቱ ጥልቅ የሆነ ‘ምስጋንን’ በማቅረብ፥ በጋዛ አሰቃቂ ጥቃት ለደረሰባቸው ህጻናት በተደረገላቸው አቀባበል ‘በጣም መነካታቸውን’ ገልፀዋል።

አምባሳደሩ በማከልም “የጣሊያን መንግስት የተጎዱ ህፃናቶቻችንን ስለረዳ እናመሰግናለን። ወደፊት ብዙ ህጻናትን እንደሚቀበሉም ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
 

01 February 2024, 12:59