ልጆች ቤሩት ውስጥ በሚገኘው በኤጀንሲው የሚመራ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጆች ቤሩት ውስጥ በሚገኘው በኤጀንሲው የሚመራ ትምህርት ቤት ውስጥ   (AFP or licensors)

በተቋረጠው የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት 2 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ያለ ዕርዳታ ቀርተዋል ተባለ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃማስ በእስራኤል ላይ መስከረም 26 በፈጸመው ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ (UNRWA) ሰራተኞች ተሳትፈዋል የሚለው ክስ እያጣራ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎ በአውሮፓ የሚገኙ የኤጀንሲው ተወካይ እንደገለጹት፥ ኤጀንሲውን በገንዘብ ይረዱ የነበሩ ሃገራት ድጋፉን በማቆማቸው ምክንያት፥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የህይወት አድን ዕርዳታ እንዳያገኙ ያደርጋል ብለዋል ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ የአውሮፓ ተወካይ ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ው/ሮ ማርታ ሎሬንዞ ይህን አስመልክተው ሲናገሩ፥ “ለጋሾች የእገዳቸውን ውሳኔ እስካልቀየሩ ድረስ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ከ 2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች የህይወት አድን እርዳታ መስጠት አንችልም” ብለዋል።

ሃላፊዋ በርካታ ለጋሽ ሀገራት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ የሚያደርጉትን ድጋፍ ካቋረጡ በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ሁኔታ በመገምገም አቅርበዋል።

በኤጀንሲው ሰራተኞች ላይ በቀረበው ክስ የተደረገ ምርመራ

መስከረም 26 ሐማስ እስራኤል ላይ በፈጸመው መብረቃዊ ጥቃት፥ የዚህ ኤጀንሲ ሠራተኞች ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም እሰራኤል ማውጣቷ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጄኔራል ፊሊፕ ላዛሪኒ እንደተናገሩት፥ መስከረም 26 በደረሰው የሐማስ ጥቃት ተሳትፈዋል የተባሉት ዘጠኝ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ ሰራተኞች ሥራ ማቆማቸውን እና በክሱ ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ከኤጀንሲው 1.16 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት ውስጥ፥ 546 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያደርጉትን አሜሪካ እና ጀርመንን ጨምሮ፥ ቢያንስ አስራ ስድስት ሀገራት ለኤጀንሲው የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ ማቆማቸው ተነግሯል።

በኒው ዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የውስጥ ቁጥጥር ቢሮ ውስጥ፥ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ ነፃ በሆነ አካል ምርመራው እየተካሄደ መሆኑን ወይዘሮ ማርታ ሎሬንዞ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ማርታ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድርጅት እንደመሆናችን መጠን ለእንዲህ ዓይነቱ ክስ ምንም ዓይነት ትዕግስት እንደሌለን ለማሳወቅ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በጋዛ ለሚደረገው የሰብአዊ ዕርዳታ የጀርባ አጥንት ነው

ይህ የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲ በዌስት ባንክ (ምስራቅ እየሩሳሌም ጨምሮ) በጋዛ ሰርጥ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ እና ሶሪያ ውስጥ የፍልስጤም ስደተኞችን በትምህርት፣ በጤና እንክብካቤ፣ በእርዳታ እና በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የካምፕ መሠረተ ልማት እና ማሻሻያ፣ ማይክሮ ፋይናንስ፣ እና የአደጋ ጊዜ እርዳታ በመስጠት ትልቅ ሥራን እየሰራ እንደሚገኝም ይታወቃል።

በመሆኑም ለኤጀንሲው የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ሲቆም፥ ጋዛ ውስጥ ለሚገኙ 2.2 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን የሚሰጠውን የሰብዓዊ ዕርዳታ እና የትምህርት ድጋፍ እንደሚያዳክመው ተገልጿል።

ወይዘሮ ማርታ ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ሲያስረዱ፥ “በእኛ ማቆያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለው ስለሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች እየተነጋገርን ነው፥ እኛ በጋዛ ውስጥ ለሚደረገው የሰብአዊ ዕርዳታ የጀርባ አጥንት ነን” ካሉ በኋላ፥ “ከዚህም በላይ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት መሆናቸው ነው ፤ ግጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ብዙ የተራቡ ሰዎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ፥ ይህ ትልቅ ተጽእኖ ነው” በማለት ገልጸዋል።

በመላው መካከለኛው ምስራቅ መረጋጋትን ማምጣት

ሃላፊዋ እንደተናገሩት፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ በቀጠናው ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ ስለሚገኝ፥ በመካከለኛው ምስራቅ መረጋጋትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ማርታ በማከልም፥ “ስለ ትምህርት ስናወራ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ህጻናት ትምህርትን ስለማዳረስ ነው፥ ማህበራዊ አገልግሎት ስንል፥ በቀን ከ1.80 ዶላር ባነሰ ገቢ ስለሚኖሩ የድሃ ድሃ ሰዎች እያወራን ነው” ብለዋል።

ወ/ሮ ማርታ ሮሬንዞ ሲያጠቃልሉ፥ “የእኛ ስራ ከጋዛም ባሻገር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፥ የክልሉን መረጋጋት ለማስጠበቅ በጣም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ እና ስራ ኤጀንሲ እ.አ.አ. ታህሳስ 8 ቀን 1949፥ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ንዑስ አካል ሆኖ የተቋቋመ እንደሆነ ይታወቃል።
 

07 February 2024, 13:07