ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ፍትህ ቀን በጋራ መሥራትን እና ለሁሉ ማሰብን እንደሚያስታውስ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ማኅበራዊ ፍትህ ማለት እኩልነት እና ክብር ለሁሉም ሰው ማለት ነው። ይህ ማለት የሰዎች ምርጫ እንዲከበር አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ደህንነታቸውን በመጠበቅ እንዲያብቡ የሚያስችል ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ማለት ነው።
ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ፍትህ ቀን በየዓመቱ የካቲት 12 ቀን ይከበራል። በየዓመቱ የሚከበረው የዚህ በዓል ዓላማም ፍትሃዊ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ ማኅበረሰብ ግንባታ አስፈላጊነትን ለማስታወስ ነው።
የብዙ ቀውሶች ገጽታ
ዓለም አቀፍ ትብብር ለልማት እና ለአብሮነት የተሰኘ ካቶሊካዊ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዮሴን ጋቲዬር እንደገለጹት፥ “ዛሬ በዚህ ውስጥ እያጋጠመን ያለው ዋነኛ ፈተና ስለ ዘርፈ ብዙ ቀውስ መናገራችን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ለማኅበራዊ ፍትህ በሚደረገው ግንባር ቀደም ትግል ውስጥ ዓለም አቀፍ ትብብር ለልማት እና ለአብሮነት በጋራ የሚሠሩ የካቶሊካዊ ድርጅቶች አንድ ቤተሰብ መሆናቸውን ዋና ጸሐፊዋ ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር ተናግረው፥ ከዚህ በፊት ያስተናገድናቸው በርካታ ቀውሶች እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን ከመመልከት ርቀናል” ሲሉ አስረድተዋል።
"የአየር ንብረት መዛባት፣ አስከፊ ድህነት፣ ብጥብጥ፣ ጦርነት፣ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚነሱ ግጭቶች፣ ፆታዊ፣ ማህበራዊ እና የዘር ልዩነቶች፥ ሁሉም የተከሰቱት በኃይል አለመመጣጠን እና በብክነት ባሕል መሆኑን ገልጸው፥ እነዚህ ችግሮች የተከሰቱት ሰዎች ከተቀረው ፍጥረት ጋር ካላቸው ያልተስተካከለ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ
ዓለም አቀፍ ትብብር ለልማት እና ለአብሮነት የተሰኘ ካቶሊካዊ ድርጅት “CIDSE” ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር እንደተናገሩት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ “የብክነት ባህል” በማለት የሚጠቀሙት ፅንሰ-ሃሳብ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ቅዱስነታቸው በአብዛኛው የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ስልጣናቸው የፍትህ መጓደል መንስኤ የሆነውን ዓለም አቀፍ ግዴለሽነትን ለመዋጋት መወሰናቸውን አስታውሰዋል።
በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እያጋጠመው የሚገኘውን የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ስለ መጠበቅ፣ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከአደጋ መጠበቅ እና በክብር ተቀብሎ ማስተናገድን፥ “የግድየለሽነት ግሎባላይዜሽን” ብለው በሚገልጹት እሳቤ ሥር የበለጸጉ አገሮች ድሆችን ለመርዳት ተጨባጭ እርምጃ እንዲወዱ ማሳሰባቸውን ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር ገልጸዋል።
ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር ስለ ስደት ሲናገሩ፥ ሰዎች ትውልድ አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ በሚገደዱበት ወቅት ለኑሮ ስለማይመች እና የወደፊት ተስፋ ስለሌላቸው መሆኑን ተናግረው፥ በዚህም “የራሳችን የሞራል ቀውስ እየገጠመን ነው” ብለዋል። "በራሳችን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምርጫ ምክንያት ሰዎች ከቤታቸው እንዲሰደዱ በማድረግ እና ድንበር ሲያቋርጡ አጋርነታችንን የሚፈልጉ ከሆነ እንዴት ወደ ኋላ ልንመልሳቸው እንችላለን?" ብለው፥ "ይህም የፍትህ ጉዳይ ብቻ ነው!" በማለት ገልጸዋል።
ያለው ዕድል
ሁሉም ሰው ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ ፍትህ ቀንን እንደ ልዩ አጋጣሚ እንዲመለከተው የጋበዙት ዋና ጸሐፊዋ ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር፥ “ለአፍታ ቆም ብለን አንዳችን ሌላውን እንዴት እንደምናስተናግድ፣ እርስ በእርሳችን እና የጋራ መኖሪያ ቤታችን በሆነች ምድራችን ውስጥ የበለጠ ፍትሃዊ ግንኙነቶችን እንዴት መፍጠር እንደምንችል ማሰላሰል ይገባል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማኅበራዊ ፍትህ እና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ያቀረቡት ጥሪ እንደ ወይዘሮ ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር ገለጻ መሠረት እጅግ ጠቃሚ እና ለፖሊሲ አውጪዎችም እጅግ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ መልዕክት እንደሆነ አስረድተዋል። ፖሊሲዎች ሁል ጊዜ የሰዎችን ሕይወት ማዕከል በማድረግ ከዕለታዊ ሕይወት ጋር በመገናኘት ሥር ሊሰድዱ እንደሚገባ ማመናቸውን ገልጸው፥ “እኛነታችን ሰብዓዊነትን ካላገለገለ እና ሁሉንም በእንግድነት ካልተቀበለ ትርጉም የለውም” ብለዋል።
ወ/ሮ ዮሴን ጋቲዬር በመጨረሻም በጋራ መሥራት እና ለሁሉንም ሰው ማሰብ ጨዋታ ሳይሆን የጋራ ሃላፊነት እንደሆነ አስታውሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ሳይታክቱ ይህን ጉዳይ ዘወትር እንደሚያስታውሱን ገልጸዋል።