መራጮች የሴኔጋል ከተማ በሆነችው ምቡር ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የምርጫ ካርዶቻቸውን እየወሰዱ መራጮች የሴኔጋል ከተማ በሆነችው ምቡር ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ውስጥ የምርጫ ካርዶቻቸውን እየወሰዱ  

ሴኔጋል ለወራት ዘግይቶ የነበረውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አከናወነች

በሴኔጋል ብዙዎቹ በሀገሪቱ የተወሰነ መረጋጋትን እንደሚመልስ ተስፋ ያደረጉበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ድምፃቸውን ለመስጠት እሁድ ዕለት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች አቅንተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል ውስጥ ለሚካሄደው ወሳኝ ምርጫ ከ7 ሚሊየን በላይ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል።

ምርጫው መጀመሪያ ላይ ባለፈው ወር እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፥ የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል የምርጫ ቅስቀሳው ሊጀመር ሰዓታት ሲቀረው በድንገት ምርጫው እንዲዘገይ አድርገውታል።

የፕረዚዳንቱ ውሳኔ በሃገሪቷ የብጥብጥ ማዕበልን የቀሰቀሰ ሲሆን፥ የሕገ መንግሥታዊ ምክር ቤቱ ምርጫውን ለማዘግየት የሚደረጉ ሙከራዎችን ውድቅ በማድረግ የፕረዚዳንቱን የስልጣን ዘመን ከሚያዚያ እንዳያልፍ ውሳኔውን አስተላልፏል።

የአሁኑ ምርጫ የተካሄደው ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ምርጫውን ለማዘገየት ካደረጉት ያልተሳካ ጥረት ከሳምንታት በኋላ ነው። በአሁኑ የምርጫ ፉክክር በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ዕጩን ጨምሮ በአጠቃላይ 19 እጩዎች ፕሬዚዳንት ሳልን ለመተካት የተፎካከሩ ሲሆን፥ ሳል በህገ መንግስቱ በተቀመጠው ገደብ መሰረት ለሶስተኛ ጊዜ እንዳይወዳደሩ ታግደዋል።

ይህ ማለት በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝደንት በምርጫው የማይሳተፍ ሲሆን፥ የገዢው የፕረዚዳንት ሳልስ ጥምረት ፓርቲ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ባን በእጩነት አቅርቧል።

በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ስለመሆኑ በተነገረለት በዚህ ምርጫ ከ50 በመቶ በላይ የህዝብ ድምጽ የሚያገኝ ዕጩ እንደማይኖር ተንታኞች ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በዚህም መሰረት ድጋሚ ምርጫ ይደረጋል የሚለው ግምት አይሏል። 

ከዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዶ ባ እና ዕውቁ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኦስማኒ ሶንኮ የሚደግፏቸው የግብር ባለሙያው ባሲሮ ዲኦማዬ ይገኙበታል።

የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች እሁድ ዕለት ማምሻውን ቀድመው እንደተዘጉ እና ጊዜያዊ ውጤቶች በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ እንደሚወጡ የሚጠበቅ ሲሆን፥ አንዳድ የምርጫ ማእከላት ውጤታቸውን እሁድ ዕለት መለጠፍ ጀምረዋል።

የአሁኑ ምርጫ ሴኔጋል እ.አ.አ. በ1960 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ የተደረገ አራተኛው ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
 

25 March 2024, 18:09