በህንድ የሚገኙ ህፃናት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ በህንድ የሚገኙ ህፃናት የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም የተቃውሞ ድምጽ ሲያሰሙ  (AFP or licensors)

‘የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን እናስቁም’ በሚል በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ለመጠበቅ ጥሪ ቀረበ

ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ በርካታ ሕጻናት በአብዛኛው የዓለም ክፍል ለተለያዩ የጉልበት ብዝበዛዎች ይዳረጋሉ። በዚህም መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ10 ህጻናት አንዱ የጉልበት ብዝበዛ እንደሚደርስበት እና በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ቁጥራቸው ከ160 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህፃናት ትምህርት ቤት ሳይሄዱ በጉልበት ሥራ ተሰማርተው እንደሚገኙም የዓለም ፀረ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን ያመላከተ ሲሆን፥ ይህ ዓለም አቀፍ ሥጋት በተለይም እንደ ስደተኞችን፣ ፍልሰተኞችን እና የህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑ ህፃናትን የመሳሰሉትን የተገለሉ ማህበረሰቦችን በእጅጉ እንደሚጎዳም ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ኅዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ በተካሄደው ኮንፈረንስ ንግግር ሲያደርጉ “ማለም የማይችል፣ መጫወት የማይችል ልጅ ማደግ አይችልም። ይህ ልጆችን ከወደፊት ሕይወታቸው እና ስብእናቸው መስረቅ እንደማለት ነው፥ በአጠቃላይ የሰውን ክብር መጣስ ነው” በማለት በየዓመቱ ሰኔ 5 የሚከበረውን የዓለም የፀረ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀንን አስመልክተው መልዕታቸውን አስተላልፈው ነበር።

የፀረ ህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ስምምነት ከፀደቀ ዘንድሮ 25 ዓመታትን ስላስቆጠረ በዚህ ዓመት የሚከበረው የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ቀንን ልዩ ያደርገዋል የተባለ ሲሆን፥ “በገባነው ቃል መሰረት እንስራ፡ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ይቁም!” በሚል መሪ ቃል እንደተከበረም ተገልጿል።

ከ 10 ህፃናት 1

ምንም እንኳን የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን አስከፊ እውነታ ለመዋጋት የተዋቀሩ ስብሰባዎችን እየተደረጉ ቢሆንም፥ አሁንም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ10 ሕፃናት መካከል አንዱ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የሚፈጸምበት ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አማካይነት አደገኛ ሥራ እንዲሠሩ ይገደዳሉ። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ተብራርቷል።

ስለዚህ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምንድነው? የእሱ ሰለባ የሆኑት እነማን ናቸው? ለመከላከል ምን ተሠርቷል? ምንስ ሊደረግ ይችላል? ይሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ተገቢ ነው።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ምንድን ነው?

እንደ ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ማህበር ገለፃ “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ” ማለት ህፃናትን የልጅነት ጊዜያቸውን፣ አቅማቸውን እና ክብራቸውን የሚነጥቅ እና አካላዊ እና አእምሮአዊ እድገታቸውን የሚጎዳ ማንኛውም ድርጊት ማለት ሲሆን፥ በተጨማሪም በአእምሮ፣ በአካል፣ በማህበራዊ ወይም በሥነ ምግባራዊ አደገኛ እና ህጻናትን የሚጎዱ ተግባራትን መፈፀም ወይም ትምህርት ቤት እንዳይገኙ በመከልከል ትምህርታቸውን የሚያውኩ ፣ ከትምህርት ገበታቸው ቀድሞው እንዲለቁ ማስገደድ፣ ወይም ከመጠን ያለፈ እና ከባድ ስራ አሰርቶ ከትምህርት ቤት እንዲቀሩ የማድረግ ተግባራትን ያጠቃልላል።

ምንም እንኳ ሥራው “የሕፃናት የጉልበት ሥራ” ተብሎ ቢፈረጅም እንደ የልጁ ዕድሜ፣ የሥራው ተፈጥሮና ሰዓት፣ የሥራ ሁኔታ እና የየሃገራቱ የተለዩ ግቦች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን ይህም በተለያዩ አገሮች እና ዘርፎች ውስጥ ይለያያል።

ተጎጂዎቹ እነማን ናቸው?

እንደተለመደው የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ሰለባ የመሆን ስጋት ያለባቸው የተገለሉ ማህበረሰቦች አካል የሆኑ ህጻናት ናቸው። እንደ ዩኒሴፍ ዘገባ ከሆነ እነዚህ ስደተኞችን እና ተፈናቃይ ህጻናትን የሚያጠቃልሉ ሲሆን፥ ብዙዎቹም በግጭት፣ በአደጋ ወይም በድህነት የተፈናቀሉ ናቸው። በተለይ ለብቻቸው የሚሰደዱ ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መደበኛ ያልሆነ የስደት መንገድ የሚጓዙ ከሆነ ወደ ሥራ ሊገቡ አልፎ ተርፎም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋ ይጋለጣሉ።

እንደዚሁም በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ ሕፃናት ብዙውን ጊዜ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ሰለባ ሲሆኑ ለጥቃት፣ እንግልት እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይዳረጋሉ፥ በሴቶች ላይ የጾታዊ ብዝበዛ ስጋት ከፍተኛ ነው፣ ከዚህም ባለፈ ወንድ ልጆች ደግሞ በታጣቂ አማፂያን ለውጊያ ይታደናሉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በዓለም ዙሪያ በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ ተመልምለው ያለ እድሜያቸው በውትድርና ላይ ይሳተፋሉ።

ከ 1997 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ምንም እንኳን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ እጅግ የላቀ ነው ተብሎ ቢታመንም፣
ከ105,000 በላይ ህጻናት ለትጥቅ ትግል ተመልምለው መጠቀሚያ እንደሆኑ ተረጋግጧል።

ማንኛውም ልጅ መብት አለው...

እንደ ዩኒሴፍ እና ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ያሉ ተቋማት ሁሉም ህፃናት ከጥቃት እንዲድኑ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማደግ እንዲችሉ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ።

“ህፃናት ከትምህርት ቤት መቅረት የለባቸውም ወይም የህክምና ዶክተር ጋር ለመቅረብ መፍራት የለባቸውም። የመጡበት አከባቢ ከየትም ይሁን መገለል የለባቸውም። እራሳቸውን ዬትም ያግኙ ወይም ቤታቸው የትም ይሁን ባሉበት ቦታ ቤታቸው እንደሆኑ ሊሰማቸው ይገባል” ሲል ዩኒሴፍ በድረ ገጹ ላይ ጽፏል።

የቤተክርስቲያን ድምጽ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንዲቆም ያለማቋረጥ ድምጿን ታሰማለች። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ደጋግመው ልጆች እንደ ልጆች መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል። ይህንንም አስመልክተው ጥር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “መጫወት በሚገባቸው እድሜ ላይ ያሉ ልጆች እንደ ትልቅ ሰው ለመስራት ይገደዳሉ፥ ፣ ለመግዛት ወይም ለመሸጥ ጠቃሚ ነገር ፍለጋ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ የሚኳትኑ ስለ እነዚያ ምስኪን ትንንሽ ልጆች እናስብ” ካሉ በኋላ፣ “ሁላችንም የአንድ ትልቅ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባላት ስለሆንን ጉዳዩ እያንዳንዳችንን እንደሚነካ ከማሳሰብ ውጪ ምንም ማድረግ አልችልም” በማለት ለልጆቹ እንድንራራ አደራ ብለዋል።
 

13 June 2024, 08:08