መጋቢት ወር ላይ የወጣ የምርጫ ቅስቀሳ ባነር የወቅቱን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትስን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር መጋቢት ወር ላይ የወጣ የምርጫ ቅስቀሳ ባነር የወቅቱን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትስን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር  

የእስራኤል የጦር ካቢኔ ስልጣን መልቀቅ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ግጭት እየሰፋ መሄዱ ተነገረ

የቀድሞው ጄኔራል ቤኒ ጋንትዝ ከእስራኤል የጦር ካቢኔ አባልነት ራሳቸውን ያገለሉት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እስራኤልን መጎብኘታቸው ተከትሎ መሆኑ ታውቋል። ይህ በእንዲህ እያለ ሄዝቦላህ በሰው አልባ አውሮፕላኖች በሊባኖስ ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እና እስራኤል በዌስት ባንክ ላይ በምታደርገው ወረራ ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እንደተጠበቀው ሁሉ በእስራኤል መንግሥት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ክፍፍል በግልጽ ያሳያል በተባለ ውሳኔ የአገሪቱ የጦር ካቢኔ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱን ለመልቀቅ የወሰኑ ሲሆን፥ ለሚድያ በሰጡት መግለጫ "እንዳለመታደል ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ ወደ እውነተኛ ድል እንዳንሄድ እየከለከሉን ነው፣ ስለሆነም ዛሬ የአስቸኳይ ጊዜ መንግስቱን ለመልቀቅ ተገደናል፥ ውሳኔውንም ‘ቀላል አልነበረም’ ነገር ግን አንጸጸትም” ብለዋል።

ጋንትዝ ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም. እሑድ ዕለት በቴል አቪቭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ሲያሳውቁ እንዳሉት የብሄራዊ አንድነት ፓርቲያቸው ከጥምር መንግስት መውጣቱን አስታውቀዋል።

እርምጃው ለቀናት ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ቤኒ ጋንትዝ የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ማለዳ ላይ ባካሄደው ዘመቻ በጋዛ ሰርጥ መሃል በሚገኘው የኑሴኢራት የስደተኞች ካምፕ አራት ታጋቾችን ካስለቀቀ በኋላ ውሳኔያቸውን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ ወስነው ነበር።

ቤኒ ጋንትዝ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላ የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሃላፊ ኢታማር ቤን ጊቪር በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ጋር ያለውን ጦርነት ለመቋቋም የተመሰረተውን የእስራኤል የአደጋ ጊዜ መንግስት አባል ለመሆን በይፋ ጠይቀዋል።

በአንዳንዶች የእስራኤል ቀጣዩ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ዕድል እንዳላቸው የሚነገርላቸው ጋንትዝ፤ ኔታንያሁ የምርጫ ቀን እንዲወስኑ ጠይቀዋል።

ኔታንያሁ አሁንም 120 መቀመጫ ባለው ክኔሴት (የእስራኤል ፓርላማ) 64 አባላትን በመያዝ አብላጫ ድምጽ ስላላቸው የጋንትዝ እርምጃ የእስራኤልን መንግሥት አያፈርስም ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ድምጽ ይሰጣል

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ሳይገለጽ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ለጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ረቂቅ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲሰጥ ጠይቃለች። እንዲሁም የተባበሩት መንግታት የመካከለኛው ምስራቅ አዲስ ተልዕኮ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ይፋ ተደርጓል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት

አንቶኒ ብሊንከን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ካይሮ በመገኘት ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል። በውይይቱም ተጨማሪ ታጋቾችን ለማስለቀቅ እና ጦርነቱ እንዲቆም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ ለማድረግ ድርድር ይካሄዳል ተብሏል።

የክልላዊ ግጭት ስጋት

ግጭቱ አሁን ላይ በጋዛ ሰርጥ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፥ ጦርነቱ በቀጠናው ከተቀሰቀሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሂዝቦላህ ቡድን በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላኖች ላይ ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎችን የተኮሰ ሲሆን፥ በሌላ በኩል እስራኤል በዌስት ባንክ ባደረሰችው ሌላ ድንገተኛ ጥቃት ሁለት ፍልስጤማውያን መሞታቸው ተዘግቧል።
 

12 June 2024, 15:30