የሰብአዊ እርዳታ ከአየር ላይ ሲወርድ የሰብአዊ እርዳታ ከአየር ላይ ሲወርድ   (AFP or licensors)

ዮርዳኖስ ለጋዛ የሚደረገውን እርዳታ የሚያስተባብር ዓለም አቀፍ ጉባኤ ልታዘጋጅ ነው

ዮርዳኖስ በጋዛ ለደረሰው ሰብአዊ ቀውስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠውን አስቸኳይ ሰብአዊ ምላሽ ለማጠናከር ያለመ ጉባኤ ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ልታስተናግድ እንደሆነ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዮርዳኖስ በጋዛ ሰርጥ ለተከሰተው ቀውስ አስቸኳይ የሰብአዊ ምላሽ የሚያስተባብር ዓለም አቀፍ ጉባኤ ልታዘጋጅ ነው።

ጉባኤው ሰኔ 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ማክሰኞ ዕለት በሙት ባህር አቅራቢያ የሚካሄድ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ግብፅ በጋራ እንደሚያዘጋጁት ተገልጿል።

ስብሰባው በጋዛ ሰርጥ ለደረሰው የሰብአዊ አደጋ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠውን ምላሽ ለማጠናከር መንገዶችን ለመለየት እና ችግሮቹን ለመፍታት የጋራ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም ቅዱስ አባታችን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋዛን ሕዝብ ለመርዳት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ በማሳሰብ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አስቸኳይ እርዳታ እንዲደርስ መፈቀድ አለበት ሲሉ በተደጋጋሚ ሲያሳስቡ እንደነበር ይታወቃል።

ለጋዛ ሰርጥ እርዳታ ማቅረብ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብፅ አየር ሀይል በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል በወታደራዊ አውሮፕላኖች አማካይነት በርካታ የሰብአዊ እርዳታ በፓራሹት ከአየር ላይ ማቅረቧን አስታውቃለች።

በግብፅ እና በጋዛ መካከል ያለው ወሳኙ የራፋህ ድንበር ማቋረጫ ከተዘጋ በኋላ የእርዳታ መኪኖች በጦርነቱ እየወደመ ወደሚገኘው አከባቢ ለመግባት ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥሟቸዋል።

አርብ ዕለት ዩኒሴፍ እንደዘገበው በጋዛ ሰርጥ ተጠናክሮ የቀጠለው ግጭት እና እገዳ፣ ቤተሰቦች የልጆቻቸውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት እንዳይችሉ እንዳደረገ ያሳሰበ ሲሆን፥ እንደ ድርጅቱ ገለጻ ከሆነ ከአስር ህጻናት ዘጠኙ ለከፋ የምግብ እጥረት እንደተጋለጡ ጠቁሟል።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሃማስ ታጣቂ ቡድን ወደ እስራኤል ዘልቀው በመግባት ድንገተኛ ጥቃት በመሰንዘር ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎችን ገድለው፣ ወደ 250 የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ አግተው ከወሰዱ በኋላ እስራኤል በጋዛ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረስ ጀምራ እነሆ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተከሰተው ግጭት ስምንት ወራትን አስቆጥሯል።
 

10 June 2024, 15:13