የኬንያ ወታደሮች የሄይቲ ብሄራዊ ፖሊሶች ከወረበሎቹ ጋር የሚያደርገውን ትግል ለማግዝ ሄይቲ ሲደርሱ  የኬንያ ወታደሮች የሄይቲ ብሄራዊ ፖሊሶች ከወረበሎቹ ጋር የሚያደርገውን ትግል ለማግዝ ሄይቲ ሲደርሱ   (ANSA)

የኬንያ ፖሊሶች በተባበሩት መንግስታት ለሚደገፈው የጸጥታ ተልዕኮ ሄይቲ ገቡ

ለበርካታ ጊዜያት የዘገየውና የፍርድ ቤትም ጭምር እክል የገጠመው፣ የኬንያ መንግስት ፖሊሶችን ወደ ሄይቲ የማሰማራቱ ዕቅድ፣ በስተመጨረሻ እውን ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈው 200 የኬንያ ፖሊስ ሃይል አባላት በሄይቲ ውስጥ ለጠፈጠረው እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እያሽመደመደ ያለውን የጎዳና ላይ ወረበሎችን ወረራ ለማስወገድ እና ለማረጋጋት ለስምሪት መዘጋጀታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሄይቲ እያሽመደመዳት ያለውን የወሮበሎች ጥቃት ለመመከት የውጭ ኃይሎች ወታደራዊ እርዳታ እንዲያደርጉላት መማጸኗ የሚታወስ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርያል ሄንሪ አገራቸውን “ከተጋረጠባት ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ” ለመታደግ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት እንዲጠይቁ የሄይቲ መንግሥት ፍቃድ ሰጥቷቸዋል።

ይህንን ተከትሎ ነው የኬንያ መንግስት የሃገሪቱን የፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው ለመላክ የወሰነው።

እነዚህ ለስምሪት ዝግጁ የሆኑት የኬንያ ፖሊስ አባላት ዜግነታቸውን እና ሥልጣናቸውን የሚገልጹ መለያዎች በክንዶቻቸው ላይ የተለጠፉ ሲሆን፥ በጣም የታጠቁም ናቸው ተብሏል። ሆኖም ግን የሄይቲ ዋና ከተማ የሆነችውን ፖርት አው ፕሪንስ ከተማን አብዛኛውን ክፍል እና በጣም ድሆች የሆኑ የሃገሪቱ ህዝብ የሚኖርበትን የምዕራብ ንፍቀ ክበብ የተቆጣጠሩት እነዚህ አስፈሪ የጎዳና ላይ ወሮበሎች ጥምረት የኬንያን ፖሊሶች በቁጥር እጅግ እንደሚበልጥ ተገልጿል።

የኬንያ ፖሊሶች በጣም የተደራጀ የወንጀል ጥቃት ተከትሎ ለሦስት ወራት ያህል ከተዘጋ በኋላ በግንቦት ወር ላይ እንደገና በተከፈተው የሄይቲ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ መድረሳቸው የታወቀ ሲሆን፥ አየር ማረፊያው በወሮበሎቹ ቁጥጥር ሥር በነበረበት ወቅት፣ ወንጀለኞቹ ሁለት ደርዘን የሚሆኑ ፖሊስ ጣቢያዎችን ይዘው እንደነበር እና ከሁለት ዋና ዋና እስር ቤቶች ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ እስረኞችን አስለቅቀው እንደነበር ይታወሳል።

ሄይቲን ማረጋጋት ሰብዓዊ ግዴታ እንደሆነ የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ደጋግመው ሲገልጹ ቆይተዋል።

በቃ!

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋሪ ኮኒል ከኬንያ የፀጥታ ሚኒስትር ሞኒካ ጁማ ጋር በመሆን እንደተናገሩት “ሄይቲ በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ነች። አሁን ይበቃል። አገሪቷን እንደገና በቁጥጥር ሥር ለማድረግ ቀስ በቀስ መሥራት እንጀምራለን፥ እንዲህ ባለው አነስተኛ ቁጥር የኬንያ ፖሊስ በዋና ከተማው የሚገኘውን በተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰበት እና በወንበዴዎች እንዲዘጋ የተደረገውን ወደብ ጨምሮ የመንግስት ተቋማትን እና ቁልፍ ቦታዎችን ደህንነት ያጠናክራል” ብለዋል።

ከጃማይካ፣ ባርባዶስ፣ ከባሃማስ፣ ባንግላዲሽ፣ ቤኒን እና ቻድ ተጨማሪ ፖሊሶች ይቀላቀላሉ ተብሎም ይጠበቃል፥ ነገር ግን በትክክል መቼ እንደሆነ ለማወቅ አልተቻለም። ከዚህም ባለፈ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን ለመደገፍ ቃል ቢገቡም እስካሁን ምንም ነገር አለመስጠታቸው ተነግሯል።

ሄይቲ በዓለም ላይ ድሃ ከሚባሉ አገራት ውስጥ የምትመደብ ስትሆን በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ትገኛለች።
ከእነዚህም ውስጥም ባለፈው ዓመት ፕሬዝዳንቷ ከተገደሉ ከወር በኋላ 2200 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው የመሬት መንቀጥቀጥ ተጣቃሽ ነው።

ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ነው

ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የፕሬዝዳንት ጁቬኔል ሞይስ በኮሎምቢያ ቅጥረኞች መገደላቸውን ተከትሎ በሄይቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወሮበላዎቹ እንቅስቃሴ በመላው ሃገሪቷ ተንሰራፍተዋል። ይህ የኬንያ እርምጃ በሄይቲ አራተኛው ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት እንደሆነም ተገልጿል።

ከዚህን በፊት እ.አ.አ. ከ2004 – 2017 ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች በሄይቲ በነበራቸው ቆይታ በበጎም በመጥፎ የሚነሳ ነው። በአገሪቱ ተቀስቅሶ 10 ሺህ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው የኮሌራ በሽታ መቀስቀስ ሰላም አስከባሪዎቹ በከፊል ኃላፊነት ወስደዋል።

ይህ አዲስ እና በቁጥር አነስተኛ የሆነው የኬንያ የፖሊስ ሃይል የሄይቲ ባለስልጣናት ሀገሪቱን ከትርምስ እና ወረርሽኝ አፋፍ ለማዳን የሚያረጉትን ጥረት ለመርዳት የሚሞክር ሲሆን፥ በጣም ጥቂት ነገር ግን ከበርካታ ሃይል ጋር ይጋፈጣልም ተብሏል።
 

27 June 2024, 15:37