ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከሉተራን ወርልድ ፌዴሬሽን የልዑካን ቡድን ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከሉተራን ወርልድ ፌዴሬሽን የልዑካን ቡድን ጋር  (Vatican Media)

የሉተራን ዎርልድ ፌዴሬሽን አባላት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

የሉተራን ዎርልድ ፌዴሬሽን አመራር አባላት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ከተገናኙ በኋላ ዋና ጸሃፊዋ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ በካቶሊክ እና በሉተራን ቤተክርስቲያናት መካከል ስላለው ግንኙነት የተደረገውን ውይይት በማንሳት አብራርተዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሐሙስ ማለዳ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከሉተራን ዎርልድ ፌዴሬሽን የልዑካን ቡድን ጋር ተገናኝተው ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በጋራ ስለሚያደርጉት ክርስቲያናዊ ጉዟቸው ላይ ያሉትን ‘የተስፋ ምልክቶች’ አጉልተው ተወያይተዋል።

ከቅዱስ አባታችን ጋር በተደረገው ውይይት ላይ ከተገኙት የልኡካን ቡድን መካከል የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ እና በኢስቶኒያ ሉተራን ቤተክርስትያን ወንጌላዊት ቄስ ዶ/ር አኔ በርገርት ነበሩ።

ከስብሰባው በኋላ ቄስ በርገርት ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሁን ላይ ባለው የካቶሊክ እና የሉተራን ግንኙነት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

የካቶሊክ-ሉተራውያን ውይይት

በርገርት የሉተራን ቤተክርስትያን ከካቶሊክ ቤተክርስትያን ጋር የምታደርገው ውይይት ዘመናትን ያስቆጠረ እንደሆነ እና ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ እ.አ.አ. በ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ሲደረግ እንደነበረ በመጥቀስ ነበር ቃለ ምልልሳቸውን የጀመሩት።

ዋና ጸሃፊዋ እስካሁን ድረስ አምስት ዙር ይፋዊ ውይይት በካቶሊኮች እና በሉተራኖች መካከል እንደተካሄደ በመግለጽ፥ አሁን እየተደረጉ ያሉት ውይይቶች በሚቀጥለው ዓመት ለሚደረገው እና በሥነ-ምህዳር እና አገልግሎትን መረዳት ላይ በሚያተኩረው ለስድስተኛ ዙር ውይይት ቅድመ ዝግጅት እንደሆነም አብራርተዋል።

ሆኖም “አብረን ልናከብረው የምንችለው ብዙ ነገር አለ” ያሉት ሃላፊዋ በተለይም በ1991 ዓ.ም. ላይ ስለ ቅድስና አስተምህሮ የወጣውን የጋራ ሰነድ በመጥቀስ፥ ይህ ሰነድ “በ16ኛው ክፍለ ዘመን መለያየትን ካስከተሉት ወሳኝ ጉዳዮች መካከል አንዱን ይፈታል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአውስበርግ ኑዛዜ

ቄስ ዶክተር ቡርጋርት የሚቀጥለው ዓመት የሉተራን እምነት መሰረት የሆነውን የአውግስበርግ ኑዛዜ (ወይም 'Confessio Augustana') 500ኛ ዓመት ክብረ በዓል ቅድመ ዝግጅት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

ይህ እ.አ.አ. በ1530 ዓ.ም. የታተመው መጽሃፍ በመጀመሪያ የሉተራንን መንፈሳዊ አስተምህሮ ወይም ቲዎሎጂን በሮማ ካቶሊኮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ ነበር።

ቡርጋርት እንዳሉት የሉተራን ዎርልድ ፌደሬሽን መጽሃፉ በውስጡ የያዘውን “ሁለንተናዊ የክርስትና ግንዛቤ” ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር በጋራ በመመርመር “ይህንን የኑዛዜ ሥራ በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት አይን ለመመልከት” ተስፋ ያደርጋል ብለዋል።

“ካቶሊክ ሉተር”

በቅርቡ ‘ካቶሊክ ሉተር’ ስለ ተሰኘው ነፃ የትምህርት ዕድል እንደገና ስለመጀመሩ የተጠየቁት ዋና ጸሃፊዋ “ሌላ ቤተ ክርስቲያን መፍጠር የሉተር ዓላማ ፈጽሞ አልነበረም” ብለዋል።

ዓላማው ቤተክርስቲያኗን ማሻሻል እና “ወንጌልን እና የእግዚአብሔርን የጸጋ መልእክት ማእከል ማድረግ ነው” ብለዋል።
“ዛሬ ጠዋት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሳዳምጥ፣ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ማዕከል እንደሆነ እና እርሱ ለመለኮታዊ ምህረት ሥጋ የለበሰ ነው’ ብለው ነበር፥ ይህ በማርቲን ሉተር ዘወትር ይነገር ነበር” ሲሉ አክለዋል።

ይህ በእሳቸው አመለካከት፣ ሉተር በአጠቃላይ ለክርስትና ያበረከተው ማዕከላዊ አስተዋፅዖ እንደሆነ ገልጸው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስን እና የእግዚአብሔርን ጸጋ እና ምህረት አስፈላጊነት የእምነታችን ማዕከል ለማድረግ” አበረታች ነው ብለዋል።

ክርስቲያናዊ እድገት

በርገርት በቃለ ምልልሱን ሲያጠቃልሉ፥ ዛሬ በሁለቱ ቤተክርስቲያናት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት “ታላቅ ደስታን” እንደሚፈጥርባቸው አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያናዊ ህብረት በበቂ ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ እንሰማለን፥ ነገር ግን ከ 100 ዓመታት በፊት ሁኔታው ሙሉ በሙሉ የተለየ መሆኑን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነው ካሉ በኋላ፥ “ክርስቲያኖች በእውነት አንድ ላይ ተቀራርበው እና አብረው እየሰሩ መሆናቸውን ማየታችን በጣም ጥሩ ነው” ያሉት በርገርት፥ “የጋራ ድምጽ ዛሬ በዓለም ላይ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው” ብለዋል።
 

21 June 2024, 14:13