በደርቤንት የሚገኘው የተቃጠለው ምኩራብ ቅሪት በደርቤንት የሚገኘው የተቃጠለው ምኩራብ ቅሪት 

በቤተክርስቲያናትና ምኩራቦች ላይ ከተፈጸመው የሽብር ጥቃት በኋላ የዳግስታን ግዛት ሀዘን ውስጥ ናት

በሩሲያ የዳግስታን ግዛት ውስጥ በሚገኙት ማካችካላ እና ደርበንት በተባሉ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ቤተክርስቲያናት እና ምኩራቦች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት ከ19 በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች እና ንፁሀን መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን በዚህም ምክንያት የሶስት ቀናት ሃዘን መታወጁ ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥቃቱ በአካባቢው ተዘጋጅቶ በነበረው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ፌስቲቫል ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የግዛቱ አስተዳዳሪ ሰርጌይ ሜሊኮቭ ገልፀው፤ በተጨማሪም ሁለት አብያተ ክርስቲያናት እና የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ የጥቃቱ ዒላማ እንደነበሩ ተናግረዋል።

የክልሉ ትልልቅ ከተሞች በሆኑት ማካችካላ እና ደርቤንት በሚገኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የአምልኮ ሥፍራ እና የጥንት የአይሁድ ማህበረሰብ ምኩራቦች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አካባቢው ሰኞ እለት ሀዘን ውስጥ ወድቋል።

የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የወንጀል ምርመራ ኤጀንሲ የሆነው የምርመራ ኮሚቴ አምስቱም አጥቂዎች የተገደሉት ከአሰቃቂ የተኩስ ልውውጥ በኋላ መሆኑን ገልጸው፥ ከተገደሉት 19 ሰዎች ውስጥ 15ቱ ፖሊሶች እንደሆኑም ጭምር ኮሚቴው ገልጿል።

ከሟቾቹ መካከል በደርቤንት ከተማ የሚገገኘው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቄስ የሆኑት ኒኮላይ ኮተል-ኒኮቭ የተባሉት የ66 ዓመት አዛውንት እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል። የአካባቢው ባለስልጣናት እንደተናገሩት አጥቂዎቹ ቤተክርስቲያኑን ከማቃጠላቸው በፊት ቄሱን እንዳረዷቸው ገልጸው፥ ጥቃቱ የደረሰው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የሥላሴ እሁድ ተብሎ የሚታወቀውን የጴንጤቆስጤን በዓል እያከበሩ በነበረበት ወቅት መሆኑንም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ አጥቂዎቹ በደርቤንት ከተማ የሚገኘውንም ኬሌ-ኑማዝ ተብሎ የሚታወቀውን የአይሁዶች ምኩራብንም ማቃጠላቸው ተነግሯል።

ጥቃቶችን ማስፋፋት

በደርቤንት ከተማ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ታጣቂዎች በአቅራቢያው በሚገኘው ማካችካላ ከተማ በሚገኘው የፖሊስ ጣቢያ ላይ ባደረሱት የተኩስ ጥቃት 15 ፖሊሶችን እንደገደሉ የተዘገበ ሲሆን፥ አጥቂዎቹ በልዩ ሃይሎች እየታደኑ ከመገደላቸው በፊት በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና በምኩራብ ላይ አስከፊ ጥቃት ሰንዝረዋል።

በዳግስታን ከተማ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ 13 ፖሊሶችን ጨምሮ 16 ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን እና ከነዚህም ውስጥ አራት መኮንኖች በከባድ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት በሰሜን ካውካሰስ አካባቢ አክራሪ ሙስሊሞች በብዛት እንደሚገኙ የአከባቢው ባለሥልጣናት መግለጽ ከጀመሩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መሆኑም ተዘግቧል።

በሞስኮ ከተማ ዳርቻ ላይ በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው 145 ሰዎች ከሞቱበት ከመጋቢት ወር ወዲህ ይህ በሩሲያ ውስጥ የደረሰው እጅግ አስከፊው ጥቃት እንደሆነም ተገልጿል።

በመጋቢት ወር ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ሃላፊነቱን የወሰደው በአፍጋኒስታን የሚገኘው የእስላማዊ መንግስት ቡድን በዳግስታን ከተማ የደረሰውን ጥቃት በማወደስ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፥ ጥቃቱ የተፈጸመው “በካውካሰስ ውስጥ ባሉ ወንድሞች” መሆኑን ጠቅሶ፥ “እነዚህ ወንድሞች አሁንም ጠንካራ መሆናቸውን ያሳዩበት ጥቃት” ነው ብሏል።

መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው የጦርነቶች ጥናት ኢንስቲትዩት “ውስብስብ እና የተቀናጀ” ሲል የገለጸውን ጥቃት ያደረሰው የእስላማዊ መንግስት ቡድን የሆነው እና የሰሜን ካውካሰስ ቅርንጫፍ ‘ቪላያት ካቭካዝ’ ሳይሆን አይቀርም ሲል መላ ምቱን አስቀምጧል።

የዳግስታን ገዥ የሆኑት ሰርጌይ ሜሊኮቭ በውጪ ሃይሎች የሚመሩ እስላማዊ “ህቡእ ህዋሶች” አባላትን ከመውቀስ ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም።

'ፍርሃትን መዝራት'

አቶ ሰርጌይ አጥቂዎቹ ዓላማቸው “ሽብርን እና ፍርሃትን መዝራት” እንደሆነ ጠቅሰው፥ ጥቃቱን ሞስኮ በዩክሬን ላይ እየወሰደችው ካለው ወታደራዊ እርምጃ ጋር ለማገናኘት ሞክረዋል ያሉ ቢሆንም ለዚህ አባባላቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ አልሰጡም።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መጋቢት ወር ላይ ለደረሰው ጥቃት የእስላማዊ መንግስት ቡድን ሃላፊነቱን ቢወስድም ዩክሬንን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ ኪየቭ በጥቃቱ ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳልነበራት አጥብቃ በመግልጽ ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።

እነዚህ ጥቃቶች የተከሰቱት ሩሲያ በቅርብ ጊዜ ከሚታወሱት እጅግ የከፋ ፀረ ሴማዊ ክስተቶች ጋር እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት መሆኑም ተገልጿል።

የዳግስታን ከተማ መነጋገሪያ መሆን የጀመረችው ባለፈው ዓመት መነሻቸውን ከእስራኤል ያደረጉ አይሁዳውያን ተጓዦች በአካባቢው በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ሲያርፉ በተደረገባቸው ወረራ እና የዘረፋ ሙከራ በኋላ መሆኑ ይታወቃል።

በሌላ ዜና ሩሲያ በሚያዝያ ወር ላይ በሞስኮ በሚገኘው ምኩራብ ላይ ሊደርስ የነበረውን ጥቃት በተሳካ ሁኔታ ማክሸፏን ገልፃለች።

አንዳንድ ተቺዎች እንደሚሉት በዛሪስት ዘመን የነበረውን የአይሁዶችን ስደት የሚያስታውሰው ጥቃት እና ብጥብጥ መነሳት የጀመረው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባደረገችው ሙሉ ወረራ እና የእስራኤል - ሀማስ ጦርነትን ተከትሎ እንደሆነ፥ ብሎም የእነዚህ ጦርነቶች ውጤት ፀረ-ሴማዊ ስሜትን በእጅጉ እንደሚያነሳሳ ይገልፃሉ።
 

25 June 2024, 14:03