በጋዛ ሰርጥ ታግተው የነበሩ ታጋቾች ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በወታደራዊ ዘመቻ ከተለቀቁ በኋላ በእስራኤል ከቤተሰቦቻችው ጋር ሲገናኙ በጋዛ ሰርጥ ታግተው የነበሩ ታጋቾች ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በወታደራዊ ዘመቻ ከተለቀቁ በኋላ በእስራኤል ከቤተሰቦቻችው ጋር ሲገናኙ  

እስራኤል በጋዛ ባደረገችው ወታደራዊ ዘመቻ አራት ታጋቾችን ነፃ ማውጣቷ ተነገረ

በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሃማስ ተይዘው የነበሩ አራት ታጋቾች የእስራኤል ወታደሮች ባደረጉት ወታደራዊ ዘመቻ ነጻ መውጣታቸው ተገልጿል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ 

የእስራኤል የጸጥታ ሃይሎች በማእከላዊ ጋዛ በሚገኘው ኑሴኢራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አከባቢ በሚገኙ ሁለት የተለያዩ ቦታዎች በሃማስ ታጣቂዎች ተይዘው የነበሩ አራት እስራኤላዊያን ታጋቾችን ‘የቀን ብርሃን ዘመቻ’ ተብሎ በተሰየመ ወታደራዊ ዘመቻ ነፃ ማውጣታቸውን ገልጸዋል።

ኖአ አርጋማኒ፣ አልሞግ ሜየር ጃን፣ አንድሬ ኮዝሎቭ እና ሽሎሚ ዚቭ የሚባሉት የ22፣ 26፣ 27 እና 41 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አራት እስራኤላውያን በሐማስ የታገቱት የሃማስ ታጣቂ ቡድን መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ወቅት ታድመውበት ከነበረው የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ እንደሆነ ይታወሳል።

በኑሴኢራት መጠለያ ካምፕ አካባቢ ከሚገኙ ሁለት የተለያዩ ሕንፃዎች የእስራኤል ጦር “ከፍተኛ አደጋ ባለው እጅግ ውስብስ” በተባለ ወታደራዊ ዘመቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ገድሎ አራት ዜጎቹን ከሐማስ እገታ ነጻ ማውጣቱ የተገለጸ ሲሆን፥ አራቱም ሰዎች ወዲያው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ እና በአሁኑ ጊዜ ሁሉም በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በዴር አል ባላህ የሚገኘው ሆስፒታል ቃል አቀባይ እንደተናገሩት በወታደራዊ ዘመቻው ቢያንስ 50 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ዝርዝር መረጃውን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን በአየር ድብደባው እና አል-ኑሴኢራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አካባቢ በተደረገ ውጊያ ቢያንስ 210 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ400 በላይ መቁሰላቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የእስራኤል ጦር ለህጻናት ጥበቃ ማድረግ ባለመቻሉ ተከሰሰ

በሌላ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ 2015 ዓ.ም. ለህጻናት ጥበቃ ማድረግ ያልቻሉ ተቋማት ዝርዝር ውስጥ የእስራኤል ጦርን አካቷል።

ውሳኔው አርብ ዕለት እንደተላለፈ የተነገራቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን ውሳኔውን 'አሳፋሪ' ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት እዝራኤል ካትስ በበኩላቸው በኢየሩሳሌም በሰጡት መግለጫ 'የወጣው ዝርዝር ሃገራቸው ከተባበሩት መንግስታት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያስከትል' አክለዋል።

በየዓመቱ በተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ቢሮ በኩል ታትሞ የሚወጣው ይህ ዝርዝር በጦርነት ውስጥ ህፃናትን መግደል እና የእርዳታ አቅርቦት መከልከል የሚሉትን ያጠቃልላል።

ለስምንት ወራት በዘለቀው ግጭት በጋዛ በሚገኙ ሲቪሎች ላይ በደረሰው ጉዳት እና እነዚህን ጉዳቶች ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት በተመለከተ እስራኤል ባለፈው ወር ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ክትትል ሲደረግባት ቆይቷል።

በጋዛ የኮሌራ ወረርሽኝ ስጋት

ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ በጋዛ ሰርጥ ካለው የንጹህ ውሃ እጦት እና በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረው የበጋው ሙቀት መጠን ጋር ተያይዞ የኮሌራ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ሐማስ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ከ1ሺህ 200 በላይ ሰዎችን ገድሎ ወደ 251 ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወቃል። ከእነዚህም መካከል 116 ሰዎች አሁንም በፍልስጤም የሚገኙ ሲሆን፥ የአገሪቱ ጦር ቢያንስ 41 የሚሆኑት ሕይወታቸው ሳያልፍ እንዳልቀረ መግለጹ፣ እንዲሁም ሕዳር መጀመሪያ ላይ በተደረሰ ስምምነት 105 ታጋቾች በሐማስ መለቀቃቸው ይታወሳል።
 

10 June 2024, 14:33