በሰሜን ዳርፉር በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች - የማህደር ፎቶ በሰሜን ዳርፉር በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች - የማህደር ፎቶ  

በሱዳን ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግጋት መከበር አለበት ተባለ

በሱዳን የሚገኘው የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ቃል አቀባይ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዓለም ላይ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለምትገኘው ሀገር ሰብአዊ እርዳታ በተሻለ ሁኔታ እንዲደርስ ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሱዳን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ አድናን ሄዛም “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአሳዛኝ ሁኔታ በየቀኑ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚታገሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን እንዲያስታውሳቸው እንጠይቃለን” ብለዋል።

የእስራኤል - ሃማስ እና በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት የዓለምን ትኩረት የሳበ በመሆኑ ሱዳን፣ የመን እና ሶርያ ውስጥ ያለው አስከፊ ግጭት የመዘንጋታቸው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የጠቆሙት ሔዛም ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደረግ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ከዓለም እጅግ አስከፊ ከሆኑ የሰብአዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የሆነው የሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ፣ በሃገሪቱ ከሚገኙት አጠቃላይ የጤና ማዕከላት ውስጥ 20 በመቶው ብቻ በስራ ላይ እንደሚገኝ እና አብዛኛው ህዝብ በመሰረታዊ አቅርቦቶች እና የምግብ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።

ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ማለትም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝብ አፋጣኝ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በሱዳን ከ17.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ እየተጋለጡ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ 4.9 ሚሊዮን ሰዎች ከባድ የረሃብ ደረጃ እያጋጠማቸው በመሆኑ፥ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው ከባድ ውጊያ የሀገሪቱን መሰረታዊ አገልግሎቶችን እጅግ ደካማ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ወደ 65 በመቶ የሚጠጋው ህዝብ የጤና አገልግሎት የማግኘት እድል የለውም።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በተለይም በጤና አጠባበቅ መስክ፣ አቅርቦቶችን በማመቻቸት እና በርካታ በግጭቱ አከባቢ ያሉትን ሰዎች ለቀው እንዲወጡ በመርዳት እና በመሳሰሉት፣ ለዚህ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በግንባር ቀደምትነት ተሰልፏል።

ከቫቲካን ዜና ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡

***
ጥያቄ፦ አቶ ሄዛም እርስዎ እያገለገሉ በሚገኙበት በሱዳን ያለው ሰብአዊ ቀውስ በእርግጠኝነት በዓለም ላይ ካሉት እጅግ የከፋ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የተዘናጋ ነው... እባኮትን ልምዶትን ያካፍሉን

መልስ፦ አሁን፣ ግጭቱ በሀገሪቱ ከተቀሰቀሰ እና በሚያሳዝን ሁኔታ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተገደሉ እና የቆሰሉ፣ እንዲሁም የጅምላ መፈናቀልን የሚያሳይ አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ካስከተለ 14 ወራት ሊሆነው ነው፣ አሁን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን እያወራን ነው። ለደህንነት እና በጎረቤት ሀገራት መጠለያ ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው የተሰደዱትን በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ጨምሮ ማለት ነው።

“አሁን ስለተፈናቀሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ጨምሮ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እያወራን ነው፣ ለደህንነት ብለው በጎረቤት ሀገራት መጠለያ ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው ስለወጡ ሰዎች ነው የምናወራው”

እነዚህ እየተካሄዱ ያሉት ግጭቶች አስከፊ ውጤቶች ናቸው፣ ዛሬ ላይ እነዚህ ሁኔታዎች በጣም የከፉ ቢሆኑም ለእነዚህ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት ያሉት ፍላጎቶች በእጅጉ ቀንሷል፥ በትክክል ለመናገር፣ ዛሬ ሀገሪቱ የምግብ እና የንፁህ ውሃ አቅርቦትን ጨምሮ ከፍተኛ የግብዓት እጥረት እያጋጠማት ነው። የጤና አጠባበቅ ስርዓቱም በጣም ተጎድቷል ብለዋል።

ይሄን እያልን ባለንበት ወቅት፣ በሀገሪቱ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት የጤና አጠባበቅ ተቋማት አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ አይገኙም፥ በሥራ ላይ ያሉትም በአቅርቦት እና በሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ውስጥ ናቸው። ይህ በተለይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለቆሰሉ እና ለታመሙ ሰዎች የጭንቀት ምንጭ ነው። ሕይወት አድን አገልግሎቶችን እና መገልገያዎችን ማግኘት ፈታኝ ነው፣ ሁልጊዜም ከባድ እና አስቸጋሪ ነው።

ጥያቄ፦ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ወይም ጥሪ ምንድን ነው? ሱዳንን ለመርዳት ምን መደረግ አለበት?

መልስ፦ ይህ አስከፊ ሁኔታ ለሁሉም የማንቂያ ደውል ነው፥ ስለዚህ ግጭት እየተባባሰ ባለበት ወቅት የሱዳን ዜጎች እየደረሰባቸው ያለውን መከራና ፍላጎታቸውን ዓለም ማስታወስ ይኖርበታል።

በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በአሳዛኝ ሁኔታ እየታገሉ ያሉትን ሱዳናውያን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያስታውስ እንጠይቃለን። ለእነዚህ ግዙፍ እና የተለያዩ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት በአከባቢው ላይ እየሰሩ የሚገኙ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በሰብአዊ ጥበቃ፣ ሰብአዊ ዕርዳታ እና መልሶ ማቋቋም ላይ ይበልጥ እንዲሰሩ እንጠይቃለን።

ጥያቄ፦ እርስዎ ችግሩ ባለበት አከባቢ ነዎት። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ብዙ ጊዜ በዓለም ዙሪያ የተረሱ ጦርነቶችን እና ግጭቶችን ያስታውሳሉ፣ እናም አንዳንድ ጦርነቶች እና ግጭቶች ሁል ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ያገኛሉ፥ ሌሎቹ ደግሞ ያነሰ ድምጽ እንዳለቸው እንታዘባለን፣ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ብዙ ጊዜ የማንሰማው ስለ ሱዳን ግጭት ነው፣ እርስዎ እንዳሉት ይህ አስከፊ የመፈናቀልና የስደተኛ ሁኔታ ስላለበት እና በህዝቡ ላይ የተፈፀመው እውነተኛ ዘግናኝ ድርጊት ነው። እርስዎ በቦታው ላይ እንዳለ ሰው ያዩትን አንዳንድ ነገር ማጋራት ይችላሉ?

መልስ፦ ተፈናቃዮቹ ያሉበትን በርካታ ቦታዎችን ጎብኝተናል፥ ከስድስት በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች በአንድ ክፍል ውስጥ ምግብ ሲያበስሉ እና እዛው እንደሚተኙም ጭምር አይተናል። ይህ የብዙዎቹን የተፈናቀሉ ሰዎች የሚያንፀባርቅ ሁኔታ ነው። ይህ በርግጥም በጣም ከባድ እና የከፋ ነው፥ ምክንያቱም ማንም እንደሚገምተው በተለያዩ አከባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች እየተባባሱ በመጡበት ወቅት የበለጠ መፈናቀልን ይፈጥራል።

የዛሬ ሁለት ወር ስለ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች ብቻ ስናወራ ነበር፥ አሁን ላይ ግን ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ስለሆኑ ሰዎች እያወራን እንገኛለንነ። ስለዚህ በዚህች አጭር ጊዜ ብቻ እንኳን የበርካታ ሱዳናውያን ህይወት እንደተነካ መረዳት እንችላለን።

ስለጤና አጠባበቅ ሥርዓቱ ካነሳን በሥራ ላይ የሚገኘው 20 በመቶው ብቻ ነው። የዚህ ተቋም አቅም የሱዳንን አጠቃላይ ህዝብ ፍላጎት እንዴት ሊያሟላ እና ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል መገመት ትችላለህ? እንደ ሰብአዊ ድርጅት ሁኔታው ራሱ ፈታኝ ነው።

ግጭቱ ከጀመረበት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ፣ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ጥበቃ እና እርዳታ የመስጠት ስራውን አሳድጎ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉ ሰዎችን እና ህሙማንን ህይወት ለማስቀጠል እየሰሩ ላሉ ሆስፒታሎች የቀዶ ጥገና ቁሳቁሶችን እና የህክምና መሳሪያዎችን ለማቅረብ እየሞከርን እንገኛለን። በእኛ ጣልቃገብነት እና ምላሽ፣ እንዲሁም ከሱዳን ቀይ ጨረቃ ጋር በመተባበር፣ በተለይ በዚህ አካባቢ፣ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን ለማቅረብ፣ በየቀኑ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የምንችለውን ያህል እንሞክራለን።

ይሁን እንጂ ቁጥሩን እና የችግሩን ስፋት ከተመለከትን፣ አሁንም ትልቅ ምላሽ ያስፈልጋል። በመሬት ላይ ከሚገጥሙን ፈተናዎች አንዱ መዳረሻ አለማግኘት ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ይህ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በሙሉ እኛንም ሆነ ሌሎች ድርጅቶችን ግጭት ወዳለባቸው አካባቢዎች በደንብ እንድንደርስ ድጋፍ እንዲያደርጉልን ጥሪ ያቀርባል። ምክንያቱም ይህ ካልሆነ ሰብአዊ ተልእኮአችንን ማከናወን አንችልም።

ጥያቄ፦ እና ያንን እርዳታ ማን ሊሰጥዎት ይገባል? በተለየ ሁኔታ ጥሪዎትን ለማን ነው የሚያስተላልፉት?

መልስ፦ ያንን እርዳታ እንዲኖረን እየጠየቅን ነው። ብናገኝ ማድረግ የምንችለውን መገመት ትችላለህ፣ ግጭቱ ከጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል፣ በዚህች ትንሽ እድል በመጠቀም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን ንፁህ ውሃ እንዲያገኙ መርዳት ችለናል። ሂደቱ ፈታኝ ነው፣ ነገር ግን ጥሪያችን ተሰምቶ ለተጎጂው ህዝብ የበለጠ ተደራሽ እንደምንሆን ተስፋ እናደርጋለን፣ በተለይ በአልፋሺር ካርቱም ወይም በዋድ ማዳኒ በአሁኑ ሰአት ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ነው። መዳረሻን መልሶ ለማግኘት በጣም ወሳኝ ጊዜ ነው።

ጥያቄ፦ የምግብ እጥረት፣ በሱዳን ብዙ ሰዎች እየደረሰባቸው ያለውን ረሃብ፣ በርካታ ሕጻናትን እያሰቃየ ያለው ችግሮችን ለመቅረፍ ሊደረግ የሚችል ነገር አለ?

መልስ፦ አዎ፥ ከዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ መከበር አስፈላጊነት ነው፥ እኛም ለግጭቱ ተሳታፊዎች የምናቀርበው ጥሪ የዚህ አካል ነው። እነዚህ አካላት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ግዴታ እንዳለባቸው እናሳስባለን፣ ይህ በክልላቸው፣ በእነሱ ቁጥጥር ስር የሚኖር ህዝብ አስፈላጊ ፍላጎቶችን ማሟላት እንዲችሉ፣ ብሎም በቂ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት እንዲኖራቸው እና ያልተደናቀፈ የህይወት አድን ዕርዳታን እንዲያገኙ ማረጋገጥ ነው።

“ከዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ መከበር አስፈላጊነት ነው፥ እኛም ለግጭቱ ተሳታፊዎች የምናቀርበው ጥሪ የዚህ አካል ነው። እነዚህ አካላት የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ግዴታ እንዳለባቸው እናሳስባለን”

ጥያቄ፦ ሌላ ማከል የሚፈልጉት ነገር አለ?

መልስ፦ እንደ ሰብአዊ ዕርዳታ ሰራተኛ ሱዳን ከአሁን በኋላ እንደማትረሳ ተስፋ አደርጋለሁ። ህዝቡን በእርዳታ እና በድጋፍ መልክ ማገዝ ያስፈልጋል። ለዚህ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበለጠ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን። በተለይ አብዛኞቹ ሚዲያዎች ትኩረታቸውን ወደ ጋዛ ወይም ወደ ዩክሬን ባደረጉበት ወቅት በተለየ ሁኔታ ለደቡብ ሱዳን ሽፋን የሚሰጡ ማንኛቸውንም የሚዲያ መድረኮችን አደንቃለሁ፥ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ እንዳለመታደል ሆኖ በሱዳን እና በሌሎች አካባቢዎች እንደ የመን እና ሶሪያ ያሉ ቀውሶች በሚያሳዝን ሁኔታ ተረስተዋል።

“በተለይ አብዛኞቹ ሚዲያዎች ትኩረታቸውን ወደ ጋዛ ወይም ወደ ዩክሬን ባደረጉበት ወቅት በተለየ ሁኔታ ለደቡብ ሱዳን ሽፋን የሚሰጡ ማንኛቸውንም የሚዲያ መድረኮችን አደንቃለሁ፥ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ድረስ እንዳለመታደል ሆኖ በሱዳን እና በሌሎች አካባቢዎች እንደ የመን እና ሶሪያ ያሉ ቀውሶች በሚያሳዝን ሁኔታ ተረስተዋል”
 

19 June 2024, 15:41