የዓለም የስደተኞች ቀን፡ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቤታቸውን ለቀው ደህንነትን ፍለጋ አደገኛ ጉዞ ያደርጋሉ። በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በዚህ አስቸጋሪ ሂደት ውስጥ ይሞታሉ።
በዚህ ዓመት እስከ ግንቦት ወር ድረስ ባለው ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስደት፣ በግጭት፣ በአመጽ እና በሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት ከ120 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በግዳጅ ተፈናቅለዋል ተብሎ ይገመታል።
የጄሱሳዊያን የስደተኞች አገልግሎት (JRS) ባልደረባ የሆኑት ዳንየል ቬላ አውሮጳ ውስጥ ገብተው ጥገኝነት የጠየቁ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ስደተኞችን ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።
“ጉዞው በጣም አደገኛ መሆኑን እያወቃችው ለምን ሃገራችሁን ለቃችሁ መጣችሁ?” ሲሉ ስደተኞቹን ዘወትር በሚጠይቁበት ጊዜ፥ መልሳቸው ይብዛም ይነስም ሁሌም አንድ ነው፣ “መሰደድ ስላለብኝ ነው የተሰደድኩት” ይላሉ ብለዋል።
“በተለይ አንድ በጣም የገረመኝ መልስ አለ ያሉት ቬላ፥ ‘ለተሻለ ሕይወት አይደለም... ሕይወትን ለመኖር ብቻ ነው የተሰደድኩት’ ብለው የሚመልሱ አሉ” ሲሉ ለቫቲካን ዜና ተናግረዋል።
የስደተኞችን ድምጽ መስማት ያስፈልጋል
ሰኔ 13 የተከበረው የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች ቀን የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ በጨመረበት ወቅት ሲሆን፥ “በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የስደተኞች ቁጥር 120 ሚሊየን ሊበልጥ ይችላል” በማለት ወ/ሮ ቬላ አስጠንቅቀዋል። ይህንን ቀን ስናከብር ለስደተኞቹ ድምጽ ትኩረት በመስጠት መሆን አለበት ያሉት ሃላፊዋ፥ ትኩረታችን በቁጥራቸው መብዛት ላይ ብቻ ከማድረጋችን በፊት “ይህ በሚሊዮን የሚቆጠረው እያንዳንዱ ሰው ክብር ያለው እና ልዩ ታሪክ ያለው የሰው ልጅ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፥ ብሎም ለክብራቸው፣ ለመከራቸው እና ለተስፋቸው ምላሽን የሚጠባበቁ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል” በማለት አሳስበዋል።
ለስደተኞች መብት የሚሟገቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት
የወ/ሮ ቬላ መልእክት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከሰማነው ከዓለም ታላላቅ የስደተኞች እና የፍልሰተኞች መብት ተሟጋቾች ውስጥ አንዱ ከሆኑት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መልዕክት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፥ ዘንድሮም፣ ቅዱስ አባታችን የዓለም የስደተኞች ቀን ዋዜማ ላይ ባደረጉት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዋቸው ላይ በዓለም ዙሪያ ላሉ ስደተኞች ተማጽነዋል። ብጹእነታቸው ይህ የዓለም የስደተኞች ቀን “ሰላምና ደህንነትን ፍለጋ ቤታቸውን ጥለው ለሚሰደዱ ሁሉ ትኩረት እና ወንድማዊ እይታ የምንሰጥበት አጋጣሚ እንዲሆን” ጠይቀዋል። ዳንኤል ቬላም “በትኩረት እና ወንድማማችነት” ለሚሉት ለብጹእነታቸው ቃላት ትኩረት ሰጥተዋል።
ትኩረት እና ወንድማማችነት
‘ትኩረት መስጠት’ ያስፈልጋል፥ ምክንያቱም የዓለም የስደተኞች ቀን ቆም ብለን የምናስብበት እንዲሁም የነበሩበት ሁኔታ ምንም ማድረግ ስለማያስችል የሚያውቋቸውን ሁሉ ትተው ለመሰደድ ስለተገደዱ ሰዎች እንድናስብ ዕድል ይሰጠናል ብለዋል።
ሁለተኛው ነገር ይላሉ ወ/ሮ ቬላ በመቀጠል፥ 'ወንድማማችነት' ነው፣ ምክንያቱም “ይህ የእምነታችን መሰረት ነው፣ ስለ ማህበራዊ ፍትህ ለማወቅ በካቶሊክ አስተምህሮዎች ውስጥ ብንገባ፣ የአንድ ቤተሰብ ልጆች እንደሆንን እናምናለን፣ ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን እናምናለን፣ እናም ለእያንዳንዳችን በእውነት ተጠያቂ እንድንሆን በአንድነት እንደተሳሰርን እናምናለን” ብለዋል።
አስከፊው የሜዲትራኒያን የጉዞ መስመር
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከአሥራ አንድ ዓመት በፊት ወደ ላምፔዱሳ ባደረጉት ጉብኝት “ወንድምህ የት ነው? ደሙ ወደ እኔ ይጮኻል” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ በማስታወስ፥ “ይህ ጥያቄ ለሌላ ሰው የቀረበ ጥያቄ አይደለም፥ ለእኔ፣ ለእናንተ፣ ለሁላችንም የቀረበ ጥያቄ ነው” በማለት ቬላ ገልጸዋል።
ስለ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ስንናገር ለስደተኞቹ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ቦታዎች ለአንዱ ያቀረቡት ጥያቄ ነው። ይህም ስፍራ ከሰሜን አፍሪካ ተነስተው በሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው በሚጓዙበት ወቅት ደቡብ ጣሊያን አከባቢ በምትገኘው ላምፔዱዛ በሚባለው ደሴት በየዓመቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ስደተኞችን ይቀበላል።
ይህንን አስቸጋሪ ጉዞ ከሚያደርጉት እጅግ በርካታ ሰዎች ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩት በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥመው ይሞታሉ።
መንግስታችንን ተጠያቂ ማድረግ አለብን
እ.አ.አ. በ 2023 ብቻ 3,105 ሰዎች በሜዲትራኒያን ባህር አድርገው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች ለመሻገር ሲሞክሩ ህይወታቸውን እንዳጡ ወይም እንደጠፉ መረጃዎች ያሳያሉ። “በዚህ ጉዳይ መንግስቶቻችንን ተጠያቂ ለማድረግ የበለጠ መስራት እንዳለብን አምናለሁ” ያሉት ወ/ሮ ቬላ፥ ችግሩ ያለው ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሚሞክሩት ስደተኞች ሞት ላይ ብቻ አይደለም። መንግስታት ስደተኞቹን ለማዳን የሚጥሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጀልባዎችን ጥፋተኛ በማድረግ እና በባህር ላይ የሚያድኗቸውን ሰዎች እንዲያወርዱ ባለመፍቀድ ተጠያቂዎች ናቸው” ካሉ በኋላ በማከልም “በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወቶችን ለማዳን የሚንቀሳቀሱ የባህር ላይ ጠባቂዎችን በማስቆም፣ የማዳኛ ጀልባዎችን በከፋ ሁኔታ በማዘግየት እና ስደተኞችን ወደ ኋላ በመመለስ የአከባቢው መንግስታት ተጠያቂ ናቸው” ብለዋል።
ይህም ሆኖ ግን ይላሉ ዳንዬል ቬላ፥ በምንም መልኩ የአውሮፓ ህብረት የባህር ኃይል አባላት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሰዎችን ማዳናቸውን መርሳት ዬለብንም በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል።
ነገር ግን ስደተኞችን ወደ ኋላ መመለስ ማለት “ስደተኞችን በባህር ውስጥ እንዲሰጥሙ ማድረግ ብቻ አይደለም፥ ከዚያም ባለፈ ጭካኔያዊ ተግባር እና የግዳጅ ሥራ ወደሚደርስባቸው፣ ብሎም ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ወደሚሆኑበት ቦታዎች እንዲመለሱ መግፋት ነው” በማለት አስረድተዋል።
በተጨማሪም ስደተኞቹን ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ስለሚያስገድደው ከሊቢያ ጋር ስላለው ስምምነት በማንሳት፥ “ሁላችንም እንደምናውቀው በዛ አከባቢ ባሉት በማቆያ ማዕከላት ውስጥ አሰቃቂ አያያዝ ይደርስባቸዋል” በማለት ተናግረዋል።
የፍርሃት ፖለቲካ ይቁም
‘በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በጦርነት በተመሰቃቀለ ዓለም ውስጥ የስደተኞች ቁጥር ይጨምራል። በዚህ የዓለም የስደተኞች ቀን፣ ሁላችንም ማድረግ የምንችለውን ማሰብ አለብን’ ያሉት ዳንዬል ቬላ፥ የተዛባ አመለካከትን መጠቀም ማቆም አለብን፥ ስደተኞችን የሚያሳፍር ሰብአዊነት የጎደላቸው ንግግሮች ብዙ ጊዜ ከፖለቲከኞች እና ከመገናኛ ብዙኃን ይደመጣሉ’ በማለት አሳስበዋል።
ብዙውን ጊዜ ስደተኞችን እንደ ሸክም ወይም አስጊ ነገር ሲገለጹ እንሰማለን፥ ይህ ሁሉ ስደተኞችን በተመለከተ በህዝቡ ዘንድ የጥላቻ አስተሳሰብን እና አከባቢን ይፈጥራል። እንዲያውም የበለጠ እንድንፈራ የሚያደርገን የፍርሃት ፖለቲካ ነው” በማለት ቬላ ስለሁኔታው አስጠንቅቀዋል።
ለአንድ የጋራ ሰብአዊነት የወጣ 'ማኒፌስቶ'
ወ/ሮ ቬላ እንደሚሉት ይህን በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመዋጋት፣ “ብዙውን ጊዜ ስደተኞችን በመጀመሪያ ደረጃ ለስደት እንዳይዳረጉ ማድርግ ብቸኛው ነገር ነው” ብለዋል።
የጀሱሳዊያን የስደተኞች አገልግሎት ከካሪታስ ኢንተርናሽናሊስ፣ ከዓለም አቀፉ የበላይ ተቆጣጣሪዎች ህብረት እና ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን በዚህ የዓለም የስደተኞች ቀን ለአንድ የጋራ ሰብአዊነት የሚል ሰነድ አስተዋውቀዋል። ቬላ ከዚህ ሰነድ ወይም ማኒፌስቶ በስተጀርባ ያለው ዓላማ “ሁሉም ሰው በስደተኞች ላይ ያለውን ጎጂ አመለካከት እንዲቃወም ማበረታታት፣ እንዲሁም የባለቤትነት እና የጋራ የመግባቢያ ቦታዎችን ማስተዋወቅ ሲሆን፥ ስደተኞች መጀመሪያ ላይ እንግዳ ቢሆኑም ቆይቶ ግን ጓደኛ ሊሆን ይችላሉ ብለዋል።
እንክብካቤ በሚያደርጉ ሰዎች መበረታታት
ወ/ሮ ቬላ በመጨረሻም እንደ እድል ሆኖ ስደተኞቹ እራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው እና ስደተኞቹ ደህንነትን እንዲያገኙ እና ከነዋሪው ጋር እንዲዋሃዱ ለመርዳት የቆረጡ ወዳጆች አሏቸው ካሉ በኋላ፥ “በእነዚህ ሰዎች ድርጊት ተነሳስተን እኛም የበኩላችንን እናድርግ፥ ‘እኛ ለራሳችን የምናደርገውን ለሌሎችም ማድረግ’ የሚለውን ወርቃማ ህግ በሚያበረታታው በእነዚህ ሰዎች ድርጊት እንመራ። ሁሉም ሰው የሚኖርበትን ፍትሃዊ እና ሩህሩህ ማህበረሰብ ለመገንባት በተቀሩት ስደተኞች ተስፋ እንመራ” ብለዋል።