ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን  (AFP or licensors)

ለዘብተኛው ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን የኢራን አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ለዘብተኛ ናቸው ተብለው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን ምርጫውን በማሸነፍ አዲሱ የኢራን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ያሸነፉት የቀድሞው የኢራን ፕረዚዳንት የነበሩት ኢብራሂም ራይሲ በሄሊኮብተር አደጋ መሞታቸውን ተከትሎ ነው።

የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ፔዜሽኪያን በሀገሪቱ የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው አብዛኛውን የፖለቲካ ተንታኞችን ያስገረመ ሲሆን፥ የምርጫው ውጤት ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ የዶክተር ፔዜሽኪያን ደጋፊዎች በቴህራንና ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ሲገልጹ እንደነበር ተገልጿል።

የለውጥ አቀንቃኙ ዶክተር ማሱድ ፔዜሽኪያን ተፎካካሪያቸው የነበሩትን በኒውክሌር ጉዳዮች ላይ ዋና ተደራዳሪ የሆኑት ወግ አጥባቂውን ሳኢድ ጃሊሊን ጋር ባደረጉት ሁለተኛውን ዙር ምርጫ በማሸነፍ ነው የኢራን ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት።

ዶክተር ፔዜሽኪያን ከጠቅላላው ለምርጫው ከተሰጠው 30,573,931 ድምጽ 16,384,402 ያገኙ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ዶክተር ፔዜሽኪያን 53 ነጥብ 3 በመቶ ሲያገኙ፤ ተፎካካሪያቸው ጃሊሊ 44 ነጥብ 3 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ተነግሯል።

የ71 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋና የልብ ቀዶ ህክምና ባለሙያው ተመራጩ ፕሬዚዳንት፤ በአንድ ወቅት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ የኢራን ፓርላማ አባል ናቸው።

ፔዜሽኪያን በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ወቅት ሃገሪቷን ለበርካታ ማዕቀብ የዳረገውን የኒውክሌር ፖሊሲ አስመልክተው ከምዕራባውያን ኃይሎች ጋር ለመነጋገር እና አዲስ የኒውክሌር ስምምነት ለማድረግ፣ በዚህም ስምምነት የተለያዩ ማዕቀቦችን ለማስነሳት ቃል ገብተዋል።

መጪው ዓመት ይካሄድ የነበረው ይህ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሁን የተካሄደው ባለፈው ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የፕሬዚዳንት ኢብራሂም ራይሲ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው በሄሊኮፕተር አደጋ መሞታቸውን ተከትሎ ነው።
 

08 July 2024, 15:59