የሩስያ ሚሳኤል የቪልኒያስክ ከተማን ከመታ በኋላ የሩስያ ሚሳኤል የቪልኒያስክ ከተማን ከመታ በኋላ 

በደቡባዊ የዩክሬን ከተማ በተፈጸመው ጥቃት በኋላ ከተማዋ ሀዘን ላይ መሆኗ ተነገረ

የሩሲያ ጦር በደቡብ ምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው ቪልኒያስክ ከተማ በፈጸመው የሚሳየል ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ 7 ሰዎች ተገድለው፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸው ከተነገረ በኋላ የአካባቢው ባለስልጣናት እሁድ ዕለት የሀዘን ቀን አውጀዋል። በሌላ ዜና ባለሥልጣናቱ እንዳስታወቁት በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አከባቢዎች ውስጥ ምስራቃዊ ዶኔስክ ክልል እና ደቡባዊ ኬርሰን አካባቢ ከቅዳሜ ጀምሮ በድምሩ 9 ሰዎች ተገድለዋል። እነዚህን የሩሲያን ጥቃቶች ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ምዕራባውያን አገራት ረዥም ርቀት መሳሪያዎችን እና የአየር ክልል ደኅንነት መጠበቂያ ሰርዓት እንዲሰጧቸው ዳግም ጠይቀዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በአውሮፓ የተከሰተው ይህ ከፍተኛ ገዳይ ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰበት መሄዱ እየተነገረ ይገኛል።

ሩሲያ ከወራት በፊት በምስራቅ ዩክሬን በዶኔስክ ግዛት ወሳኝ የተባለችውን አቭዲቪካ ከተማን እና በርካታ መንደሮችን መቆጣጠር መቻሏ ይታወሳል። ዩክሬን እነዚህን ቦታዎች ለቃ የወጣችው የምዕራባውያን ወታደራዊ እርዳታዎች በወቅቱ ባለመድረሳቸው ነው የሚል ምክንያት ሰጥታ ነበር።

በደቡባዊ የቪልኒያስክ ከተማ በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ፣ በደረሰው ጥቃት የሞቱ ሰዎች አስከሬኖች በተለያዩ ብርድ ልብሶች ተሸፍነው እንደሚታዩ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

የቪልኒያስክ ነዋሪ የሆነው ኦሌክሳንደር እንደገለጸው “ይህ ጥቃት የደረሰበት ህንፃ ቀደም ሲል ፈጣን ምግቦችን በማዘጋጀት የሚታወቀው ምግብ ቤትን ጨምሮ ጸጉር ቤት እና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ይገኙበት ነበር። አሁን እነዚህ ሁሉ ዬሉም፥ በርካታ ሰዎችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል” ብሏል።

የአካባቢው አስተዳዳሪ የሆኑት ኢቫን ፌዶሮቭ በበኩላቸው ከሞቱት ሰባት ሰዎች መካከል ሶስት ህጻናት እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ ዜና ከዛፖሬዢያ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ከተማ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሌሎች 31 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።

የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት የሩሲያ ጦር ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ቅዳሜ ዕለት በመላው ዩክሬን በፈጸማቸው የሚሳኤል ጥቃቶች በአጠቃላይ 11 ሰዎች ሲገደሉ 36 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የገለጹ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት የአካባቢው ባለስልጣናት እሁድ ዕለት የሀዘን ቀንን እንዲያውጁ አድርጓል።

ከፍተኛ ጉዳት

የአከባቢው አስተዳዳሪ እንደገለጹት በዚህ የሩስያ የሚሳኤል ጥቃት የተለያዩ ሱቆች፣ የመኖሪያ ሕንፃዎችን እና “ወሳኝ መሠረተ ልማቶች” መጎዳታቸውን አብራርተዋል።

የቪልኒያስክ ከተማ ሩሲያ በ2014 ዓ.ም. ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት ወደ 14,300 የሚጠጋ ህዝብ ነበራት።

የቪልኒያስክ ጥቃትን ተከትሎ “በዚህ መሰል የሩሲያ ጥቃት ከተሞቻችን እና የማኅብረሰብ አባላቶቻችን በየቀኑ ለስቃይ እየታደረጉ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ “ይህን ጥቃት ማስቆም የሚቻልበት መንግድ አለ” ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ በይፋዊ የቴሌግራም ገጻቸው ላይ ለምዕራባውያኑ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ሰርዓትን በመጠቀም እና በረዥም ርቀት ሚሳኤሎች የሩሲያን ሚሳኤል ማስወንጨፊያ በማውደም” የሞስኮን ጥቃቶች ማስቆም ይቻላል ብለዋል።

ዘለኒስኪ በሳምንቱ መጨረሻ ሁለት ካህናትን ጨምሮ 10 እስረኞችን ከሩሲያ ለማስፈታት ቫቲካን ስላደረገችው ድጋፍም ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ “ዛሬ በብሔራዊ የጸሎት መርሃ ግብር ላይ ተገኝቼ በግዞት ከታሰሩበት የተፈቱት አባ ቦህዳን ሄሌታ እና አባ ኢቫን ሌቪትስኪ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለው” ካሉ በኋላ በተጨማሪም ህዝባችንን፣ ማህበረሰባችንን፣ ግዛታችንን በዚህ እጅግ አስቸጋሪ የጦርነት ጊዜ እገዛ ስላደረጉልን ሁሉንም የቤተ ክርስቲያን እና የሃይማኖት ማህበረሰብ ተወካዮችን አመሰግናለሁ” ሲሉም አክለዋል።

ሆኖም በቪልኒያስክ እየደረሰ ያለው ውድመት ጦርነቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳይ ሲሆን፥ ከተማዋ በዛፖሪዝሂያ ክልል ውስጥ የምትገኝ፣ ከአካባቢው ዋና ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ እንዲሁም ከግንባር መስመር ደግሞ በስተሰሜን የምትገኝ ሲሆን የሩሲያ ጦር አብዛኛውን የግዛቱን ክፍል መያዙን ቀጥሏል።

የሩሲያ ጦር ከግንባር እስከ 1,000 ኪሎ ሜትር (600 ማይል) ርቀት ላይ ያሉ በርካታ ቦታዎች የዩክሬን ጦርን እያስለቀቁ እንደሆነ እና ሞስኮ ብዙ ጊዜ የኢነርጂ ተቋማትን እና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚያነጣጥሩትን የዩክሬንን የመሳሪያ አቅም ለማሟጠጥ የአየር ድብደባውን አጠናክራ ቀጥላለች ተብሏል።

የዶኔስክ ጥቃት

የአከባቢው ባለስልጣናት እንደተናገሩት የዩክሬን ጦርነት ማዕከል በሆነው ምስራቃዊ የዶኔስክ ክልል ቅዳሜ ዕለት በደረሰው ጥቃት ስምንት ሲቪሎች ሲሞቱ 14 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እንዲሁም በነጋታውም በክልሉ የተለያዩ አውራጃዎች ጥቃቶቹ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

በደቡባዊ ከርሰን ክልል በተመሳሳይ ጊዜ በደረሰ የሚሳኤል ጥቃት አንድ ሰላማዊ ሰው መሞቱ እና አምስት ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

በተጨማሪም በሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት በደረሰ ጥቃት አራት ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር እሁድ እለት በሩስያ ደቡብ ምዕራብ በሚገኙ ስድስት ክልሎች ላይ 36 የሚሆኑ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን ገልጿል።

በሩሲያ ጦር የተመታ አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን በኩርስክ ክልል በሚገኝ መንደር ላይ ወድቆ በአከባቢው የነበረው ህንፃ መስኮቶች እና በሮች መጎዳታቸውም ተነግሯል።

15ቱ ድሮኖች ከዩክሬን ጋር በምትዋሰነው የኩርስክ ግዛት ተመትተው የወደቁ ሲሆን ዘጠኙ ደግሞ በርካታ ኪሎሜትሮች ርቀው በደቡባዊ ሞስኮ የኢንዱስትሪ ዞን በሆነችው ሌፕሴክ ግዛት ላይ መመታታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ዩክሬን ሦስተኛ ዓመቱን የያዘውን የሩስያን ሙሉ ወረራ ለማስቆም በከፍተኛ ሁኔታ እየሞከረች እንዳለ እና በሩስያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ኢላማዎችን እየመታች መሆኗም ተገልጿል።
 

01 July 2024, 14:27