የዩክሬን ፕሬዝዳንት ከአስከፊው የሆስፒታል ጥቃት በኋላ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ኪየቭ በሚገኘው የኦክማትዲት ትልቁ የህፃናት ሆስፒታል ላይ በደረሰው የሚሳየል ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ የነፍስ አድን ሠራተኞች ፍርስራሹን እየቆፈሩ መሆኑን እና የተጎጂዎች ቁጥር እስካሁን በትክክል እንዳልታወቀ፣ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ ገልጸዋል።
ዘለንስኪ ወደ ኔቶ ወታደራዊ ህብረት ስብሰባው አዳራሽ ሲገቡ የጀግና አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ባደረጉት ንግግር እውነተኛዎቹ ጀግኖች የሩሲያን ቀጣይ ወረራ ለመመከት በየግንባሩ ላይ እየተፋለሙ ያሉት ናቸው ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በህዳር ወር ከሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት የሩሲያን ጥቃት ለመመከት ወሳኝ እርምጃ መወሰድ አለበት ብለዋል። “እርምጃ ለመውሰድ እና ጠንከር ያሉ ውሳኔዎችን ለመወሰን ህዳርን ወይም ሌሎች ወራትን መጠበቅ አያስፈልግም” ያሉት ዘለንስኪ፥ ከዝምታ ውስጥ ለመውጣት ጊዜው አሁን ነው፥ እኛ ሁላችን አንድ ላይ በመሆን ጠንካራ እና የማናወላውል መሆን አለብን” ሲሉ በአፅንዖት ገልጸዋል።
በዩክሬን ትልቁ የህፃናት ሆስፒታል ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት የቆሰሉ ህጻናት ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ወደ ሌላ ስፍራ የተዛወሩ ሲሆን፥ በሕይወት የተረፉትን ለማግኘት አሁንም የህንፃው ፍርስራሽ ስር ፍለጋው እንደቀጠለ ተነግሯል።
የከተማዋ ባለስልጣናት እንዳሉት፣ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ሩሲያ በኪዬቭ ላይ ከወሰደቻቸው ጥቃቶች ይሄኛው እጅግ የከፋ መሆኑን በመጥቀስ፥ በመዲናዋ ከሚገኙት አስር ወረዳዎች ውስጥ ሰባቱ ላይ ጥቃት መድረሱንም አመላክተዋል።
በጥቃቱ ምክንያት የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና የተቋረጠ መሆኑ እና ወጣት የካንሰር ህሙማን ህክምናቸውን ሌላ ቦታ ሄደው እንዲከታተሉ ያስገደደው ይህ በኦክማ-ትዲት የህጻናት ሆስፒታል ላይ የደረሰው ጥቃት ዓለም አቀፍ ውግዘትን አስከትሏል።
ባለ 10 ደብር የሆነው የህጻናት ሆስፒታሉ በጥቃቱ ወቅት ለ627 ህሙማን አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፥ የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ጥቃቱን አስመልክተው እንደተናገሩት “ምንም እንኳን ሕንፃው ሙሉ በሙሉ ቢወድምም፥ በጣም ትልቁ ኪሳራ የሆነው የሰዎች ህይወት መጥፋቱ ነው” ካሉ በኋላ፥ “እንደ አለመታደል ሆኖ ለህፃናት ጤንነት በጣም የሚተጋ እና ብዙ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ስፔሻሊስት ዶክተር አጥተናል። በተጨማሪም ሌላ ወጣት እና ብቁ ስፔሻሊስት አጥተናል” ብለዋል።
ሩሲያ ስህተት መስራቷን ክዳለች
ይህ በእንዲህ እያለ ንግግራቸው በአስተርጓሚ የተሰማው በተባበሩት መንግስታት የሩስያ አምባሳደር ቫዚሊ ኔቤንዛ አገራቸው ለጥቃቱ ተጠያቂ ናት የሚለውን ክስ በማስተባበል፥ “ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ተቋማትን እንደማትመታ ብዙ ጊዜ ገልፀናል” ካሉ በኋላ፥ “በዩክሬን ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች እና አየር ማረፊያዎች ላይ ስለተፈጸሙት የሩሲያ አየር ሀይል ጥቃቶች መናገር ይቻላል” ብለዋል።
ሆኖም የተባበሩት መንግስታት መርማሪዎች እንደሚናገሩት የቪዲዮ ምስሎች እና ግኝቶች እንደሚያሳዩት ሆስፒታሉ “የሩሲያ መንግስት እንደገለፀው ሚሳየሉ ሆን ተብሎ ተጠልፎ ሳይሆን ሆስፒታሉ በቀጥታ መመታቱን ያሳያሉ” ያሉ ሲሆን፥ በተጨማሪም የሩስያ ስሪት የሆነው Kh-101 ክሩዝ ሚሳይል ሆስፒታሉን ሳይመታ አይቀርም ብለዋል።
በሄግ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መርማሪዎች የጦር ወንጀል ክስ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ማክሰኞ ዕለት ሆስፒታሉን የጎበኙ ሲሆን፥ ሆስፒታሎች በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ጥበቃ ሊደረግላቸው ከሚገቡ ቦታዎች መካከል አንዱ መሆኑም ተነግሯል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሆስፒታሉ ጥቃት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል።