አፍጋኒስታዊያን ሴቶች አፍጋኒስታዊያን ሴቶች  (ANSA)

የአፍጋኒስታን ሴቶች ፊታቸውን ሳይሸፈኑ መንቀሳቀስን እና በአደባባይ ንግግር ማድረግን ተከለከሉ

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊ የሆኑት ቮልከር ቱርክ አፍጋኒስታንን እያስተዳደረ የሚገኘው የታሊባን መንግስት “ሴቶችን ወደ ጥላነት ለመለወጥ የሚሞክሩትን” ህጎች በአስቸኳይ እንዲሰርዝ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ይሄንን ያሉት ባለፈው ሳምንት በአፍጋኒስታን ውስጥ ሴቶች ፊታቸውን እንዳያሳዩ ወይም በአደባባይ እንዳይናገሩ የሚከለክሉ አዳዲስ ህጎችን ማፅደቃቸውን ተከትሎ ነው።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ቮልከር ቱርክ ባለፈው ሳምንት በታሊባን መንግስት የተላለፈው አዲሱ የሥነ ምግባር ህጎች የሴቶችን በአደባባይ መገኘትን ሙሉ በሙሉ የሚነፍጉ፣ ድምፃቸውን እንዳያሰሙ የሚገድብ እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶቻቸውን የሚነፍጉ፣ ፊት የለሽ እና ድምጽ አልባ ጥላ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚሞክሩ አሳሪ ፖሊሲዎች ናቸው በማለት ተችተዋል።

ታሊባን ሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሴቶች ፊታቸውን ሳይሸፍኑ መሄድን ከሚከለክለው እና ድምፃቸውን በህዝባዊ ቦታዎች እንዳያሰሙ በሚከለክለው አዲሱ “የሥነ ምግባር ጉድለት እና በጎነት” ህጎች ላይ የተባበሩት መንግስታት ያቀረበውን ስጋት እና ትችት ውድቅ አድርጓል።

የታሊባን መንግስት ዋና ቃል አቀባይ የሆኑት ዛቢሁላህ ሙጃሂድ በሰጡት መግለጫ “ትዕቢተኞች” ብለው የጠቀሷቸውን እና የእስልምናን የሸሪዓ ህግጋት የማያውቁት በተለይም ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች የሚያሰሙትን ስጋት እና ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አስጠንቅቀው፥ ታሊባን ህጎቹን ያወጣው መጥፎ ድርጊትን ለመከላከል እና በጎነትን ለማራመድ እንደሆነ፣ እንዲሁም ለእስልምና እሴቶች አክብሮት እንዲሰጥ በማሰብ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለመቋቋም የማይቻሉ ገደቦች
በሀገሪቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮ ኃላፊ ሕጎቹ ለአፍጋኒስታን የወደፊት ዕጣ ፈንታ “አሳዛኝ ራዕይ” ይዘው እንደሚመጡ የገለጹ ሲሆን፥ ሃላፊዋ እንዳሉት ሕጎቹ በሴቶች እና ልጃገረዶች መብት ላይ “ቀድሞውንም ሊቋቋሙት የማይችሉትን ገደቦች” እንደሚያራዝሙ ገልጸው፣ “የሴት ድምጽ እንኳን ሳይቀር” ከቤት ውጭ የሥነ ምግባር ጥሰት ተደርጎ ይቆጠራል ብለዋል።

አዲሶቹ ህጎች የጸደቁት የታሊባን ቡድን በተባበሩት መንግስታት የተሾመውን ልዩ ዘጋቢ ሪቻርድ ቤኔት አፍጋኒስታን እንዳይገባ ከከለከለ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን “የምዕራባዊያን ፕሮፓጋንዳ ያሰራጫል” ሲል ከከሰሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

ቤኔት ታሊባን ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የአፍጋኒስታንን የሰብአዊ መብት ሁኔታን እንዲከታተል በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በ 2014 ዓ.ም. መሾሙ ይታወሳል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአፍጋኒስታን ሴቶች እና ልጃገረዶች በሁሉም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚገድቡ አሳሪ ድንጋጌዎችን ሲታገል የቆየ ሲሆን፥ እነዚህም አሳሪ ህጎች የተገደበ የመዘዋወር ነፃነት፣ የተገደበ የአለባበስ ሥርዓት፣ ከጥቃት ራስን መከላከልን የሚገድቡ እና የግዳጅ ጋብቻን ያካትታሉ።
 

28 August 2024, 15:52