ስደተኞች በፓናማ በሚገኘው የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ ሲደርሱ ስደተኞች በፓናማ በሚገኘው የስደተኞች መቀበያ ጣቢያ ሲደርሱ 

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከዓለም አቀፍ ስደተኞች መካከል ክርስቲያኖች ትልቁን ቁጥር ይይዛሉ ተባለ

በአሜሪካ የሚገኘው የፔው የምርምር ማዕከል አዲስ የወጣ ዘገባ እንደሚያመለክተው በዓለም አቀፍ ፍልሰት ውስጥ የክርስቲያኖች ቁጥር ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝ ያመላከተ ሲሆን፥ በዘገባው መሰረት ከዓለም አቀፍ ስደተኞች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ማለትም 47 በመቶው ክርስቲያኖች መሆናቸውን ያሳያል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የፔው የምርምር ማዕከል እ.አ.አ. በ 2004 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ላይ የተመሰረተ፣ ከዬትኛውም የፓርቲ አስተሳሰብ ነፃ የሆነ የአሜሪካ መንግስት አማካሪ ድርጅት ሲሆን፥ በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በሕዝብ አስተያየት እንዲሁም በስነ-ሕዝብ ላይ ዩናይትድ ስቴትስን እና ዓለምን የሚረዱ ጥናታዊ መረጃዎችን ይሰጣል።

በአዲሱ የዚህ ተቋም ዘገባ ይፋ የተደረገው መረጃ ክርስቲያኖችን በስደት ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ከሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ሃይማኖተኞች መካከል 47 በመቶ ገደማውን የሚሸፍን ትልቁ የሃይማኖት ቡድን እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፥ ይህም በመነሻ እና በመድረሻ ሀገራት በሃይማኖታዊ ስነ-ሕዝብ ቁጥር ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመላክቷል።

እንደ ላቲን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ከሰሃራ በታች ካሉ ክርስቲያናን ከሚበዛባቸው ክልሎች የሚደረገው ፍልሰት ለዚህ ጥናት ውጤት ትልቁን አስተዋፅዖ እንዳደረገም ተገልጿል።

በዘገባው መሰረት ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን ወደ ሌላ ሃገራት አዳዲስ እድሎችንና ደኅንነትን ለማግኘት ለስደት እንደሚያነሳሳቸው ጭምርም ተመላክቷል።

“ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ተለያዩ የዓለም አቀፍ ክፍሎች ይንቀሳቀሳሉ” የሚለው ጥናቱ፥ ከነዚህም ውስጥ ሥራ ለማግኘት፣ ለትምህርት፣ ወይም ከቤተሰብ አባላት ጋር ለመቀላቀል እንደሚሰደዱ በማብራራት፥ ነገር ግን ሃይማኖት እና ስደት ብዙ ጊዜ የተሳሰሩ ናቸው በማለትም ይገልፃል።

በጥናቱ መሰረት የሙስሊሞች ፍልሰት በዓለም አቀፍ ስደተኞች መካከል ሁለተኛው ትልቁ የሃይማኖት ቡድን ሲሆኑ፥ ከጠቅላላው የስደተኞች ቁጥር 29 በመቶውን እንደሚሸፍን ተጠቁሟል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ፍልሰት በተለይም ግጭት ካለባቸው እንደ መካከለኛው ምስራቅ ካሉ ክልሎች በዋናነት የሚነሳው መረጋጋትን እና የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ፍለጋ እንደሆነም ተገልጿል።

አይሁዶች ምንም እንኳን ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የመሰደድ እድል እንዳላቸው እና ከዓለም አቀፉ የአይሁድ ህዝብ ቁጥር 20 በመቶው አካባቢ ከትውልድ አገራቸው ውጭ ይኖራሉ ተብሏል።

“ብዙ ስደተኞች ከሃይማኖታዊ ጭቆና ለማምለጥ ወይም ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር ለመኖር ሲሉ ይሰደዳሉ” የሚለው የፔው የምርምር ማዕከል ዘገባ፥ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሲሰደዱ ሃይማኖታቸውን ይዘው ሲሆን፥ በጊዜ ሂደት አዲስ በተሰደዱበት ሃገር ባለው ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የመለወጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው” ይላል ጥናቱ።

ይፋ የሆነው ጥናት ከዚህም በተጨማሪ “አንዳንድ ጊዜ ስደተኞች ያደጉበትን ሃይማኖት በመተው አብዛኛው ሰው የሚከተለውን የአዲሱ የስደት ሃገራቸውን ሃይማኖት ወይም ሌላ ሃይማኖት መከተል ይጀምራሉ፥ ካልሆነም ሃይማኖት-አልባ ይሆናሉ” ሲል አክሏል።

ይህ ፍልሰት በሁለቱም ማለትም በታሪካዊ ምክንያቶች እና በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ባሉ የአይሁድ ማህበረሰቦች በሚያጋጥሟቸው ወቅታዊ ፈተናዎች ተጽዕኖ ይደረግበታል ተብሏል።

ጥናቱ በተጨማሪም እንደሚያመለክተው ስደት ቀደም ሲል የሃይማኖት ውስንነቶች ወደ ነበረባቸው በተለያዩ የመዳረሻ አገሮች የሃይማኖት ብዝሃነት እንዲኖር በማድረግ፣ ብዙ ጊዜ አዳዲስ ሃይማኖታዊ ማህበረሰቦችን በማስተዋወቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል በማለት ያትታል።
 

21 August 2024, 13:25