በሊባኖስ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የእስራኤል የአየር ጥቃት ከደረሰ በኋላ በሊባኖስ በሚገኙ ቦታዎች ላይ የእስራኤል የአየር ጥቃት ከደረሰ በኋላ  (AFP or licensors)

ሂዝቦላህ እስራኤልን በሮኬት ከደበደበ በኋላ በአከባቢው ውጥረት መንገሱ ተነገረ

ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ ሰሞኑን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሮኬት የወሰደው ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ውጥረት ከፍ እንዳደረገው እየተነገረ ይገኛል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዘጠኝ ወር ያስቆጠረው የጋዛ ጦርነት ውጥረቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ከ200 የሚበልጡ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን የእስራኤል ጦር በሚገኙባቸው ስፍራዎች መተኮሱን አስታውቋል።

በኢራን የሚደገፈው ታጣቂ ቡድን እንደገለጸው ከቅዳሜው ጥቃት ቀደም ብለው የተተኮሱ 100 ሮኬቶችን ተከትሎ የተፈጸመው ጥቃት የተካሄደው፣ በደቡብ ሊባኖስ ውስጥ እስራኤል በከፍተኛ የሂዝቦላህ አዛዥ ላይ ለፈፀመችው ግድያ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ገልጿል።

እሁድ ዕለት የእስራኤል ወታደራዊ ሃይል ባወጣው መግለጫ አብዛኛው ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው እንዲወጡ በተደረገበት የሰሜን ድንበር አካባቢ በደረሰው ጥቃት የሞተ ሰው ስለመኖሩ ያስታወቀችው ነገር የለም። ሆኖም በምላሹ በደቡባዊ የሊባኖስ ክፍል ላይ ጥቃት ማካሄዷን ገልጻለች። በዚህም ወደ 100 የሚጠጉ ጄቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የሂዝቦላህ ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን መትተው ማውደማቸውን ተናግረዋል።

ከእየሩሳሌም የወጡ ዘገባዎች አክለውም የእስራኤል ጦር በግዛቱ ላይ ሊሰነዘሩ የታቀዱ “ከፍተኛ የጥቃት” እቅዶችን ማክሸፉን የገለጹ ሲሆን፥ የእስራኤል የመከላከያ ሃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ እንደተናገሩት ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ ለማድረስ ያቀደውን መጠነ ሰፊ ዝግጅት ለይታ ማውጣቷን የገለጹ ሲሆን፥ ብዙም ሳይቆይ ሂዝቦላህ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሚሳኤሎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በእስራኤል ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

የጋዛ ጦርነት መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጀመረ ወዲህ እስራኤል እና የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ አጋር የሆነው ሂዝቦላህ፣ በየእለቱ በሚባል ደረጃ ተኩስ የሚለዋወጡ ሲሆን፥ ይሄ ግጭት ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳያመራ ተሰግቷል።

ይሁን እንጂ እሁድ ዕለት ከጥዋቱ 4 ሰዓት ላይ ሰማዩ ጸጥ እንዳለና ሂዝቦላህ ዘመቻው “በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ” መሆኑን ገልጿል።

ቀደም ሲል የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በመላው እስራኤል ለ48 ሰዓታት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን፥ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትስ በበኩላቸው በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ በፃፉት ጽሁፍ እስራኤል በክልሉ ሁለንተናዊ ጦርነት እንዲጀመር አትፈልግም ብለዋል።

እስራኤል ከፍተኛ የሄዝቦላህ አዛዥ የነበሩትን መሐመድ ናአሜህ ናስርን የገደለችው የሊባኖስ የባህር ጠረፍ ከተማ በሆነችው ጣይር ላይ ረቡዕ ዕለት ባካሄደችው የአየር ድብደባ ነው። እስራኤል በሰኔ ወር ባካሄደችው ሌላ ጥቃት ታሌብ አብዳላህ የተሰኙ ሌላ አዛዥም ገድላ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ቴል አቪቭ፣ ቤን ጉሪዮን አየር ማረፊያ የሚደረጉ እና የሚነሱ በረራዎች ለአጭር ጊዜ ተቋርጠው የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በረራዎቹ እንደወትሮው ሁሉ መቀጠሉ ተነግሯል።

የፖሊዮ ስጋት መኖሩ ተመላከተ
በሌላ ዜና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች የእርዳታ እና ስራዎች ኤጀንሲ (UNRWA) የሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እየዘገየ በሄደ ቁጥር በህፃናት ላይ የፖሊዮ ስርጭት የመጋለጥ እድልን ይጨምራል በማለት ስጋቱን የገለጸ ሲሆን፥ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደገለጸው በጋዛ የ10 ወር ህጻን በፖሊዮ በሽታ ተይዞ ከፊል ሰውነቱ ሽባ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ ሁለት ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎችን ለማካሄድ ለሰባት ቀናት ያህል በጋዛ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሰብአዊ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲያደርጉ ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንደሚሉት የውጊያው ለቀናት መቋረጥ ህጻናት እና ቤተሰቦች በሰላም ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ እና የማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ሰጭ ሰራተኞች ለፖሊዮ ክትባት የጤና ተቋማትን ማግኘት ወደማይችሉ ህጻናት እንዲደርሱ ያስችላቸዋል ያሉ ሲሆን፥ ሰብአዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ካልተደረገ የክትባት ዘመቻው ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም ተብሏል።
 

27 August 2024, 14:38