አንድ ዩክሬናዊ ወታደር  በሱድዛ ከተማ ውስጥ በጥበቃ ላይ አንድ ዩክሬናዊ ወታደር በሱድዛ ከተማ ውስጥ በጥበቃ ላይ  

ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ በመግባት የምታደርገውን ጥቃት ቀጥላበታለች

ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት በመግባት በተጠናከረ ሁኔታ ወደፊት መገስገሷን የቀጠለች ሲሆን፥ ይሄንንም ያደረገችበት ዋና ምክንያት ሞስኮ በዩክሬን ላይ እያደረገች ያለውን ጦርነት አቁማ “ፍትሃዊ” ውይይቶች ላይ እንድትሳተፍ ለማሳመን ነው ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዩክሬን ጦር 28ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ በኩል የተለቀቀው የቪዲዮ ምስል በሩሲያ ግዛት ውስጥ በምትገኘው የኩርስክ ክልል ውስጥ በዩክሬን እና በሩሲያ ወታደሮች መካከል ኃይለኛ ውጊያ ሲያደርጉ ያሳያል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዩክሬን ኃይል ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ሩሲያ ግዛት 10 ኪሎ ሜትር ዘልቆ መግባት የቻለው ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ሁለት ዓመት ተኩል ባስቆጠረው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ትልቁን ድንበር ተሻጋሪ ወረራ ያደረገችው ኪዬቭ 100 ሺህ ሄክታር የሚሆን የሩስያ ግዛትን መቆጣጠሯን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን አስታውቀዋል።

ሩሲያ እንዳስታወቀችው ከባለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ ከአንድ ሺህ የሚልቁ የዩክሬን ወታደሮች በታንክና ሌሎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ታግዘው ኩርስክ ክልል ገብተዋል። 'ይሁንና በተገቢው ሁኔታ እየመከትናቸው ነው' ይላሉ።

ጋዜጠኞች ዩክሬን በበኩሏ በርከት ያሉ ገጠራማ ከተሞችን መቆጣጠሯን፣ ሱድዛ የተሰኘችውን ከተማም ለመያዝ መቃረቧን እየዘገቡ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ በሩሲያ ከተማ ማእከላዊ አደባባይ ላይ ከቆመው የሶቪየት ህብረት መስራች የሆነው ቭላድሚር ሌኒን ሃውልት ላይ በደረሰ ከባድ መሳሪያ ጥቃት ሃውልቱ መውደሙ ተነግሯል።

“ሩሲያ በራሷ ግዛት መዋጋት ስትጀምር ያኔ ሕዝቡ ስለ ጦርነቱ ግድ ይሰጠዋል። ይህን ጦርነት ለማቆም ግድ የሚላቸው ያን ጊዜ ነው። ወደ ሩሲያ ዘልቆ ማጥቃት ከመቶ የሰላም ጉባኤዎች የተሻለ ወደ ሰላም ስምምነት ያቀርበናል” ሲሉ አንድ የዩክሬን ባለስልጣን ተናግረዋል።

ውጊያው እየተባባሰ በሄደበት በአሁኑ ወቅት የሱድዛ ነዋሪዎች በትምህርት ቤት ህንፃዎች ምድር ቤት ውስጥ ተጠልለው ቀጣይ እጣ ፈንታቸው እየተጠባበቁ እንደሆነ አንዳንድ ምስሎች አሳይተዋል።

የሩሲያ ጦር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛው በሆነው በኩርስክ ክልል ላይ ለደረሰው ጥቃት ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት እስካሁን ድረስ እየታገለ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል።

ይህ የኩርስክ ክልል ጥቃት ሩሲያ በምሥራቅ በኩል ለሳምንታት የዘለቀ ጥቃት ከከፈተችና በርካታ የዩክሬን አካባቢዎች ከተቆጣጠረች በኋላ የመጣ ነው። ተንታኞች እንደሚሉት ምናልባት ዩክሬን የከፈተችው የኩርስክ ጥቃት ሩሲያ በምሥራቅ በኩል የምታደርገውን ግስጋሴ ይገታል።

በርካታ ሰው አከባቢውን ለቆ መውጣቱ
የኩርስክ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከ120 ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ያሉ ሲሆን፥ በዩክሬን ኃይሎች በተያዙ አካባቢዎች ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ዜጎች መኖራቸውን ለፑቲን ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ቢያንስ 100 የሩስያ ወታደሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኪየቭ መንግስት ይፋ አድርጓል።

ከድንበሩ 10 ኪሎ ሜትር (6 ማይል) ላይ የምትገኘው ሱድዛ ከተማ ከሃምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከተጀመረው የዩክሬን ወረራ በኋላ በዩክሬን ወታደሮች እጅ የወደቀች ትልቋ ከተማ ነች። ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት 5,000 ሰዎች ብቻ ይኖሩባት የነበረው ከተማዋ ስትራቴጅያዊ ጠቀሜታ እንዳላትም መረጃዎች ያሳያሉ።

የዩክሬን ወታደሮች በሩሲያ ውስጥ የሚያደርጉትን ወረራ ለመቀጠል በሱድዛ በኩል የሚገኙትን ዋና መንገዶችን ማግኘት ይችላሉ የተባለ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ለመካከለኛው አውሮፓ የሚቀርበው በምዕራብ ሳይቤሪያ የሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ በሱድዛ ወረዳ ውስጥ ባለው የመለኪያ ጣቢያ በኩል እንደሚያልፍም ተገልጿል።

ኪየቭ በሩሲያ ላይ የፈጸመችው ወረራ፥ ሩሲያ እየፈጸመችባት ያለውን ሙሉ ወረራ በማስቆም ፍትሃዊ ድርድር እንድታደርግ ለማስገደድ ያለመ ነው ብላለች። ሆኖም ግን፥ እስካሁን ድረስ ሞስኮ ፖክሮቭስክን ጨምሮ ዩክሬናዊያን ዜጎቿ ለቀው እንዲወጡ ጥሪ በተደረገባቸው አከባቢዎች ጥቃቱን ለማቆም ፈቃደኛ አልሆነችም።

የመከላከያ ምሽግ
ፖክሮቭስክ የዩክሬን ዋና የመከላከያ ምሽግ እና በምስራቅ ዶኔትስክ ክልል ውስጥ ቁልፍ የሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሆነችም ይታወቃል።

የፓክሮቭስክ መያዝ የዩክሬንን የመከላከል አቅም እና የአቅርቦት መንገዶችን በእጅጉ እንደሚጎዳ የተነገረ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ሩሲያ መላውን ክልል ለመያዝ ወደ አቀደችው ግብ ያደርሳታል ተብሏል።

በ 2014 ዓ.ም. የሩሲያን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ አውሮፓ በሚያጓጉዙ የኖርድ ስትሪም የጋዝ ማሰራጫ ጣቢያ ቧንቧዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ውስጥ ዩክሬን እጇ አለበት ተብሎ በወጣው አዲስ ዝርዝር መረጃ ምክንያት ዩክሬን ላይ ምዕራባውያኑ ጫና ሲያደርሱባት የነበረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ኪየቭ በጥቃቱ ላይ እንዳልተሳተፈችበት በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።

ይሄንንም በማስመልከት የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ዋና ተጠቃሚ የሆነችው ጀርመን ለአንድ ዩክሬናዊ ተጠርጣሪ የእስር ማዘዣ አውጥታለች።

በዋሽንግተን የሩስያ አምባሳደር አርብ ዕለት እንዳስታወቁት ዩክሬን ያለ “ዩናይትድ ስቴትስ ድብቅ ይሁንታ” በኖርድ ስትሪም ጣቢያ ላይ ጥቃት ታደርሳለች ብለው እንደማያምኑ፣ እንዲሁም ሩሲያ ከጥቃቱ በስተጀርባ ያሉትን ለይታ ትቀጣለች ብለዋል።
 

19 August 2024, 15:45