ለተፈናቀሉ ሰዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት የምትሰጥ ሐኪም ምስል ለተፈናቀሉ ሰዎች ነፃ የሕክምና አገልግሎት የምትሰጥ ሐኪም ምስል  (REUTERS)

አሜሪካ የጋዛ የሰላም ንግግሮች መሻሻሎች እንዲያሳዩ ፍላጎቷ እንደሆነ ገለጸች

ዩናይትድ ስቴትስ የጋዛ የሰላም ድርድር በታቀደው መሰረት እንዲጓዝ ያላትን ፍላጎት ገልፃለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዩናይትድ ስቴትስ የጋዛ የሰላም ድርድር በታቀደው መሰረት ተካሂዶ የተሻለ ውጤት እንደምትጠብቅ ገልፃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ሃማስ መጪው ሐሙስ በአሸማጋዮች በተጠራው ስብሰባ ላይ የመገኘቱ ጉዳይ እርግጠኛ አለመሆኑን በመግለጽ፥ ሆኖም ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ሊኖር እንደሚችል ተስፋ እናረጋለን ብሏል።

እስራኤል የሰላም ስምምነቱን ልትቀበል እንደምትችል ተስፋ የጣለችው አሜሪካ፣ ለዕቅዱ መደናቀፍ ዋናው ምክንያት ሐማስ መሆኑን ትገልጻለች፡፡ በዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ከርኪ እንደሚሉትም፣ ሐማስ በዕቅዱ ከተስማማ እስራኤል ዕቅዱን ልትቀበል እንደምትችል የአሜሪካ ተስፋ ነው።

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ ለጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት አዲስ ድርድር ላይ ከመሳተፍ ይልቅ ቀደም ሲል በተደረጉ ንግግሮች ላይ የተመሰረተ እቅድ እንዲያቀርቡ እሁድ እለት ሸምጋዮችን ጠይቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በጋዛ የፖሊዮ ወረርሽኝ በቅርቡ ሊከሰት ይችላል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

ባለፈው ሳምንት እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን አከባቢውን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ማስተላለፏን ተከትሎ ወደ 60,000 የሚጠጉ ጋዛዊያን ወደ ምዕራባዊ ካሃን ዩኒስ መንቀሳቀሳቸው ተነግሯል።

የብሪታንያ ቀይ መስቀልን ጨምሮ ብዙ የእርዳታ ኤጀንሲዎች በአከባቢው ረሃብ እያንዣበበ እንደሆነ እና የጤና አጠባበቅ ስርዓቱ መዳከሙን እየገለጹ ይገኛሉ። ይባስ ብሎ ባለፈው ወር የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ በከፍተኛ ሁኔታ ተላላፊ የሆነው የፖሊዮ ቫይረስ ሊነሳ ይችላል ብሎ ስጋቱን ገልጿል።

በቅርብ ጊዜ በተደረገው ክትትል በቆሻሻ ውሃ ውስጥ በተገኙ ምልክቶች ቫይረሱ ሊሰራጭ እንደሚችል ይታመናል።ከንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ ከቆሻሻ አወጋገድ እና ከጤና ስርዓቱ ጋር በተያያዙ ትላልቅ ችግሮች የተነሳ የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ነውም ተብሏል።

በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ ሽንት ቤት የሚጋሩ ሲሆን፥ እያንዳንዱ ሰው በቀን ከሁለት ሊትር ያነሰ ውሃ ብቻ እንደሚደርሰው ተገልጿል። 

በእስራኤልና ሃማስ በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በጋዛ ከ39 ሺሕ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ በእስራኤል በኩል ደግሞ 1,200 መሞታቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ። 
 

14 August 2024, 14:29