53ኛው የፓሲፊክ ደሴቶች ፎረም የመሪዎች ስብሰባ በቶንጋ 53ኛው የፓሲፊክ ደሴቶች ፎረም የመሪዎች ስብሰባ በቶንጋ  (ANSA)

የዓለም ሙቀት መጨመር ውጤቶች በፓሲፊክ ደሴት ክልሎች ላይ ስጋት መፍጠራቸው ተነገረ

ተራርቀው የሚገኙት የፓስፊክ ውቅያኖስ ደሴት ሀገራት ከ .02% ያነሰ የዓለም ዓመታዊ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ያመነጫሉ፥ ሆኖም ግን እነዚህ በእሳተ ገሞራ የተፈጠሩ አለታማ ደሴቶች ስብስብ የዓለም ሙቀት መጨመር ያስከተለው ጉዳት የመጀመሪያው ሰለባ ናቸው። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ45ኛው ሐዋርያዊ ጉዟቸው ይሄንን አካባቢ ይጎበኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከነሃሴ 17 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በቶንጋ በተካሄደው 53ኛው የፓሲፊክ ደሴቶች ፎረም የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአደጋ የተጋለጡ እና ለመጀመሪያ ጊዜ በባህር ከፍታ መጠን መጨመር እና በውሃ ሙቀት መጨመር እየተጠቁ የሚገኙት የትናንሽ ደሴቶች ችግር እንዲፈታ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቀድመው ወደ ኦሺኒያ የተጓዙት በቶንጋ ለሚካሄደው ጉባዔ ነበር። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከጳጉሜ 1 እስከ 4 ወደ ኦሺኒያ ተጉዘው 18ቱ አባል ሃገራት የሚሳታፉበት የፓስፊክ ደሴቶች ፎረም ላይ ለመገኘት ፓፑዋ ኒው ጊኒን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ላይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በማተኮር ወደ ሲንጋፖር የሚጓዙ ሲሆን፥
ቅዱስነታቸው ቀጥለውም በቅዱስ ፍራንሲስ ዛቪዬር የሱባኤ ማዕከል ከኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር እንደሚገናኙ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ሐሙስ መስከረም 2/2017 ዓ. ም. ረፋዱ ላይ በአገሪቱ ፓርላማ ውስጥ አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ውስጥ ከባለ ሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ከሩብ ላይ በሲንጋፖር ብሔራዊ ስታዲየም የተዘጋጀውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. በቅድስት ቴሬዛ ማዕከል የሚገኙ አረጋውያንን እና ሕሙማንን ከጎበኟቸው በኋላ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ በካቶሊካዊ መለስተኛ ኮሌጅ ውስጥ በተዘጋጀው የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለወጣቶች መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ታውቋል።

ይህ ብጹእነታቸው ለሶስት ቀናት ደቡብ ምስራቅ እስያ ሃገር የሚያደርጉት ጉብኝት ለከተማ ፕላን እና ዘላቂነት አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነም ተገልጿል።

ተጋላጭ የደሴት ሃገራት
ከዚህ የጉዞ መርሃ ግብር ውህደት በተጨማሪ የቅድስት መንበር እና የተባበሩት መንግስታት የሰማያዊ አህጉር ደሴቶች ተጋላጭነት ስጋትን ሲጋሩ ኖረዋል። በባለ ብዙ ወገን ደረጃ፣ ሁለቱ ተቋማት እነዚህ አገሮች የሚበደሩትን ዕዳ እንዲሰረዝ፣ እንዲሁም የበለጸጉ አገሮች ለፓስፊክ ግዛቶች ለማካካስ እና ለመላመድ እንዲረዳቸው ‘የአየር ንብረት ፈንዶች’ ፋይናንስ ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ይጨምራል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት የልማት ዕርዳታ የሚባለው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ለመላመድ እርዳታ በሚል ተተክቷል።

የፓሲፊክ ደሴት ህይወት ታዛቢ እና በፈረንሳይዋ ሙር ከተማ በሚገኘው የደሴት ጥናቶች እና የአካባቢ ጥበቃ ምርምር ማዕከል ሥር የተመሠረተው የፈረንሳይ ብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል (CNRS) የምርምር ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ታማቶአ ባምብሪጅ “እነዚህ ሁሉ መፍትሄዎች ድምር ውጤቶች ናቸው፥ አንዳቸውም ሌሎቹን ያገለሉ አይደሉም፥ በተቃራኒው ደግሞ የተለያዩ የገንዘብ ድጋፍ ዓይነቶችን ማጣመር አለብን” በማለት እነዚህን እርምጃዎች ደግፈውታል።

እነዚህ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ወዲያው አለመታየታቸው ጉዳት መሆኑም የተነገረ ሲሆን፥ 35 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትርን በሚሸፍነው ውቅያኖስ ላይ ተበታትነው ለሚገኙ ነዋሪዎች ግን መጪው ጊዜ አሳሳቢ ነው ተብሏል። የፓስፊክ ውቅያኖስ ውብ ሀይቆች ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች እየጨመረ በመጣው የውሃ ሙቀት ምክንያት ስጋት ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ ይሄ ሁሉ እየተከሰተ ያለው “በሰው ልጅ እንቅስቃሴ ተፅእኖ የተባባሰ የረዥም ጊዜ ልማድ” መሆኑ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ክስተቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አንዳንድ ደሴቶች መሬት እንዲያጡ ሌሎች ደግሞ የውሃ ሽፋናቸው እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ታማቶአ ባምብሪጅ ተናግረዋል። በተለይ የፓስፊክ ደሴቶች ለአደጋ የተጋለጡ ሲሆኑ፥ አማካኙ ከፍታ ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ከባህር ጠለል በላይ እንደሆነ እና 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከባህር ጠረፍ ከአምስት ኪሎ ሜትር በታች እንደሚኖር፣ እንዲሁም ከሁሉም መሰረተ ልማቶች ግማሽ ያህሉ ከባህር 500 ሜትር ያነሰ ርቀት ላይ ይገኛሉ።

የአየር ንብረት ለውጥን መላመድ
የአየር ንብረት ለውጥን መላመድ በእነዚህ ቦታዎች ለሚሰጠው ምላሽ ቁልፍ ጉዳይ ነው። ያለ አየር ንብረት ለውጥ መላመድ ከባድ ዝናብ ወይም ከባድ ድርቅ፣ ወደ ተላላፊ ወይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጨመር የሚወስድ ማንኛውም ከባድ ክስተት፣ የምግብ ክምችት መቀነስ፣ ወይም ምግብን የማምረት ወይም ከውቅያኖስ ውስጥ የማውጣት ችሎታ መቀነስን ያስከትላል በማለት ተመራማሪው ተንብየዋል።

የደሴቶቹ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም በገንዘብ እጥረት ምክንያት አሁንም በቂ አይደለም፥ ለዘመናት በቆየ ጥበብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይሄንን በማስመልከት ተመራማሪው አቶ ታማቶአ “የአየር ሁኔታን እና ሰማዩን እንዴት ማንበብ እንዳለብን እና በአየር ሁኔታ ላይ ለውጦችን እንዴት መገመት እንደሚቻል ባህላዊ እውቀት አለን” በማለት እንደ ግድብ ፕሮጀክቶች ያሉ የአጭር ጊዜ መፍትሄዎች እንደማያዋጡ አስጠንቅቀዋል። ግንባታቸው እየጨመረ የመጣውን የባህር ከፍታ ለማካካስ ታስቦ ነው፥ ነገር ግን በባህር ዳርቻው ላይ አደገኛ መሸርሸር እያደረሱ ነው ያሉ ሲሆን፥ “እኛ የግድ ሁሉም ሰው ከባህር ጠለል በላይ በሦስት ሜትር ርቀት እንዲኖር ለማድረግ እየሞከርን አይደለም፥ ነገር ግን የከተማ ማዘጋጃ ቤቶችን በሳይክሎኒክ ደረጃ መመዘኛዎች እየገነባን ነው፥ ስለዚህም ቢያንስ መላው ህዝብ ሁኔታው እጅግ በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜ እዚያ መጠለል ይችላል” ብለዋል።

ውቅያኖሶች አንድ ላይ ተሳስረዋል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ 2,000 ሰዎች ተቀብረው በሞቱበት የመሬት መንሸራተት አደጋ እየተሰቃየች ያለችውን ፓፑዋ ኒው ጊኒን በሚጎበኙበት ወቅት፥ ለመላው ደቡብ ፓሲፊክ ስለ ፍጥረት ጥበቃ ሰፋ ያለ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በጉዞዋቸው ዋዜማ ላይ ነሐሴ 24 የታተመው እና ለአካባቢያዊ አደጋ ሰለባዎች በሙሉ ባደረጉት ጸሎት “ምድራችን ትኩሳት አለባት” እናም “ታምማለች” ብለዋል።

ውቅያኖስ የፖለቲካም ሆነ የባህል ድንበር የሌለው ሰማያዊ የተንጣለለ ሃብት ነው ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚህ ጥበቃ ውስጥ ልዩ ቦታ አላቸው ያሉት ተመራማሪው፥ “በአማዞን፣ ደቡብ እስያ እና ኦሺኒያ ባህላዊ ማህበረሰቦች ውስጥ አንድ የተለመደ ነገር በተፈጥሮ እና በባህል መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩ ነው። ተፈጥሮ እራሱን በባህል ይገልፃል፥ በተቃራኒው ባህል የተፈጥሮ አካል ነው” ብለዋል።

ታማቶአ ባምብሪጅ ከዚህም በተጨማሪ የኦስትሮኒያ ቋንቋዎች ተፈጥሮን በትክክል የሚገልጽ “ምንም ቃል” እንደሌላቸው ጠቅሰው፥ በአንፃሩ የሜላኔዥያ፣ የፖሊኔዥያ እና የማይክሮኔዥያ የደቡብ ፓስፊክ ዓለማት ለአካባቢያቸው ያላቸው አቀራረብ ፍፁም ሁሉን አቀፍ እና ሰብዓዊ እንደሆነ፣ እንዲሁም መሬት እና ባህርን ከሰው ልጅ ጋር የሚያገናኝ ነው ብለዋል።

“ኦሺያዎች ላለፉት 3,000 ዓመታት ውቅያኖሶችን ተቆጣጥረውታል ፣በነዚህም ወቅት ከዋክብትን በመጠቀም አቅጣጫን የሚጠቁሙበት የራሳቸውን የመለኪያ መሳሪያዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል፥ ውቅያኖስ አህጉራትን ከመለያየት ይልቅ እንደሚያገናኝ አንድ አካል ተደርገው ይወሰዳሉ፥ ይህ ውቅያኖስ ሰዎችን እንደሚያቀራርብ አካል ተደረጎ የሚታየው ባህላዊ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጫወተው ሚና እንዳለው ተመራማሪውን አፅንዖት ሰጥተው የገለጹ ሲሆን፥ ልክ እንደ ሜዲትራኒያን ባህር፣ የፓስፊክ ውቅያኖስም የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከተጋረጠባቸው ትንቢታዊ ቦታዎች አንዱ ነው ብለዋል።
 

02 September 2024, 17:09