በጃካርታ ካቴድራል አንዲት ሴት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተዘጋጁ ቴምብሮችን ይዛ በጃካርታ ካቴድራል አንዲት ሴት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተዘጋጁ ቴምብሮችን ይዛ  (AFP or licensors)

ኢንዶኔዥያ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ቁልፍ መሪ ሃሳቦችን የሚያሳዩ 'ልዩ ቴምብሮችን' አሳተመች

የኢንዶኔዢያ መንግሥት ከአካባቢው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በመተባበር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በኢንዶኔዥያ እያደረጉት ላለው ሐዋርያዊ ጉብኝት ክብር ተከታታይ የመታሰቢያ ቴምብሮችን አሳትሞ ይፋ አድርጓል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ቴምብሮቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከነሃሴ 28 እስከ ጳጉሜ 1 ድረስ በሚያደርጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ቁልፍ መልእክት የሆነው “እምነት፣ ወንድማማችነት፣ ርህራሄ” የሚለው መሪ ቃል ታትሞባቸዋል።

የጃካርታ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ኢግናቲየስ ሱሃርዮ ቴምብሮቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልዕክት በመላ አገሪቱ ለማዳረስ እንደሚረዳ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ብጹእ ካርዲናሉ በጃካርታ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በሚገኘው በፕላዛ ማሪያ አዳራሽ ውስጥ በተደረገ ስብሰባ ወቅት “በኢንዶኔዥያ ህዝብ መካከል ያለው ማህበራዊ መቻቻል እና ወንድማማችነት ትስስር በተግባር ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፥ ይህም ለሌሎች የርህራሄ መንፈስን ያመጣል” በማለት ስለ መልዕክቶቹ አብራርተዋል።

የኢንዶኔዥያ ኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ባለስልጣናት፣ የኢንዶኔዥያ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ እና የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት አስተባባሪ ኮሚቴ በተገኙበት የተደረገው ይህ ስብሰባ ብጹእነታቸው በኢንዶኔዥያ ባደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነበር።

በኢንዶኔዥያ ኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ውስጥ የፖስታ እና የግንኙነት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ጉናዋን ሁታጋሎንግ “ቴምብሮች ሁል ጊዜ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እንደ አንድ ብሄራዊ ማንነት መገለጫ እንደሆኑ ተደርገው እንደሚወሰዱ እና የእነሱ መኖር የሀገሪቱን ታሪክ ያሳያል” ብለዋል።

አቶ ጉናዋን እነዚህ ልዩ ተከታታይ ቴምብሮች በቡንግ ካርኖ የስፖርት ስታዲየም በሚካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ይባረካሉ” ብለዋል።

በኢንዶኔዥያ ለጳጳሳዊ ጉብኝቶች የመታሰቢያ ቴምብሮችን የማዘጋጀት ባህል የተጀመረው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ እ.አ.አ. በ1970 ሃገሪቷን በጎበኙበት ወቅት ሲሆን፥ በመቀጠልም በተመሳሳይ ሁኔታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሃንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ. በ1989 ጃካርታን፣ ሜዳንን፣ ዮጊያካርታን እና ማሙሬን በጎበኙበት ወቅት ልዩ የማስታወሻ ቴምብሮች ታትመው ወጥተው ነበር።

ዝግጅቱ ተጠናክሮ በቀጠለበት በአሁን ወቅት የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት እና የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ኢግናስዩስ ዮናን የሎጂስቲክስ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዝግጅቱን 800 የሚጠጉ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ተገኝተው እንደሚዘግቡ፥ እንዲሁም የጳጳሱን እንቅስቃሴዎች ለመጠበቅ ከ 9,000 በላይ ሰራተኞችን ማሰማራትን የሚያካትት የደህንነት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተገልጿል።

የጃካርታ ባለስልጣናት በጉብኝቱ ወቅት ቁልፍ በሆኑ መንገዶች ዙሪያ የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር እንዲቻል መመሪያዎችን አውጥተዋል።
 

04 September 2024, 16:25